Eyanguwalele ... Witch Tamerat Geletaእያንጓለለ (የምርጫ ጭውውት)

ዳግማዊ ዳዊት This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

እያንጓለለ …

ያ ገብስማ ዶሮ - ዘንድሮስ ምን አለ?

 

ሊቀ መኳስ ቆመ - አራት ኪሎ ላይ

ትናንት መለስ መለስ …

ዛሬም መለስ መለስ …

ነገም መለስ መለስ - መለስ መለስ ባይ።

 

ሀገር አሳደጉ

ሠላም አወረዱ

ይህን አድርገዋል - ስሙ ያልሰማችሁ

ተገቢ ነውና - በሙሉ ድምፃችሁ

ለዘንድሮው ምርጫ - እነርሱን ባትመርጡ

ትዝብት ነው እንጅ - ምንም አታመጡ።

 

ኩኩሉ አለ ዶሮ

የምን ምርጫ ነው ዘንድሮ

ውጤቱን ያወቅነው ገና ዱሮ

መለስ ሊመረጥ ዞሮ ዞሮ

 

እያንጓለለ …

ያ ገብስማ ዶሮ - ዘንድሮስ ምን አለ?

 

መሪው ሊቀ መኳስ - አጭር ሰው መላጣ

“ላሌ ላሌ” እያለ - ይኸውና መጣ።

 

“ቂ ... ቂ …

ልደቱ ልደቱ - እያሉ ሲያለቅሱ

እነኃይሉም መጡ - ከእኔ ሊቋደሱ”

 

ኩኩሉ አለ ዶሮ

ማን ነው የሚገደል ዘንድሮ

ማን ነው አስገዳይ ዘንድሮ

 

እያንጓለለ …

ያ ገብስማ ዶሮ - ዘንድሮስ ምን አለ?

 

ያዝ ልደቱ …

አውቄ ነው እንጅ ድሮም ስግደረደር

እኔስ ለአድዋው ሰው - አሽከር ሆኘ ልደር

እንደምን ነው ስሜን - ወገብ ለወገቡ

እንደምን ነው ትግራይ - ወገብ ለወገቡ

የእነአዜብዬ ሀገር - የእነአይጠገቡ

አላማጣ ውዬ - መልሸ አላማጣ

ሽህ ሰው ይተላለቅ - እናንተን ከማጣ

እኔስ በመለስ ላይ - ክፉም አላመጣ።

 

ኩኩሉ አለ ዶሮ

ምን ተደግሶልናል ዘንድሮ

 

እያንጓለለ …

ያ ገብስማ ዶሮ - ዘንድሮስ ምን አለ?

 

ያዝ መለስ …

ብለነው ብለነው - የተውነውን ነገር

አምና ኃይሉ ሰምቶ - ታንቆ ሊሞት ነበር

ዘንድሮ መምጣቱ - መስማማቱ ላይቀር

ልደቱን መውቀሱ - ተገቢም አልነበር።

 

ሀገራችን ትግራይ - ወንዛችን ተከዜ

ማነው እምቢ የሚል - ምርጫ ባልን ጊዜ።

 

እያንጓለለ …

ያ ገብስማ ዶሮ - ዘንድሮስ ምን አለ?

 

ኩኩሉ አለ ዶሮ

ኃይሉስ ምን አለ ዘንድሮ

 

በእስር በእንግልቴ - ሁሉ እማስብሽ

እኔም ልመጣ ነው ፓርላማ እንዴት ነሽ?

ኤልያስ የሚሉት - የሻዕቢያ ምላስ

መለስ ጠላት ብሎ - ህዝብን ሲቀሰቅስ

እኔም ወንድነቴ - ነሸጥ አድርጎኝ

ፓርላማ መግባቴ - ውርደት ነው አልኩኝ

ያ ክፉ ባለጌ - አሳሳተኝና

ባለፈው ባልመጣ - ባላይሽ ታችሃምና

ዘንድሮ ቁርጥ ነው - እንገናኛለን

እንዲህ ተለያይተን - መች እንቀራለን

መልክ ሰጠኝ እንጅ - ሲሉ እሰማ ነበር

ሙያ ከልደቱ - ይኸው ጀመርኩ መማር።

 

እኔም ላሞግሰው - ልነሳ አደግድጌ

የአድዋው ሰውዬ - ባይሆን አብሮ አደጌ

አክብሮ ጥሪዬን - እጀን ሲጨብጠኝ

ከእራሴ ጀምሮ - ወገቤን ነዘረኝ።

 

ደጋፊ አስፈልጎኝ - በጋሪ ስገፋ

መለስን ስጨብጥ - በሽታዬ ጠፋ።

 

ይኸው መፎከሬ - “መለስ ይውረድ” ቀርቶ

ሠላም ሠላም ሆኗል - የዘንድሮው ሞቶ።

 

እኔ ፍራሽ ሆኘ - ልደቱ ትራስ

እንጠብቃለን - አልጋህ እንዳይፈርስ።

 

እያንጓለለ …

ያ ገብስማ ዶሮ - ዘንድሮስ ምን አለ?

 

ኩኩሉ አለ ዶሮ

በየነስ ምን አለ ዘንድሮ

 

ዓመት አስር ዓመት - የደነስኩብሽ

አንች ዉቧ ቆንጆ - ፓርላማ እንዴት ነሽ

ህዝቡ ቢቃወመኝ - አትግባ ቢለኝም

እመኝኝ ፓርላማ - ከአንች አልለያይም።

 

ዘጠና ሰባትን - ጠፍቶ እሚገድብ

ቅንጅት ተፈጥሮ - ወጣና ከህዝብ

ለጥቂት ተረፍኩኝ - ዱላ ከሚመዝ

ዳግመኛ እንዳይመጣ - ያን መሳይ መዘዝ።

 

ወያኔ ስትዳር - ጎጆ ስትቀልስ

ያን ጊዜ ጀምሮ - እስካሁን ድረስ

ታማኝ ተቃዋሚ - ሆኘ ለመለስ

መልካም ተብሎ ለእኔ - ህዝብም ተዘናግቶ

ያልፈኛል ሁልጊዜ - እንዳላዬኝ አይቶ።

 

ኩኩሉ አለ ዶሮ

ምን መዓት ይመጣል ዘንድሮ

 

እያንጓለለ …

ያ ገብስማ ዶሮ - ዘንድሮስ ምን አለ?

 

ያዝ ኃይሉ …

አድዋ ላይ ሆኖ - መለስ ቢደነፋ

ብርሃኑ ነጋ - ሀገር ጥሎ ጠፋ

ድሮም በእጀ - ያልኩት መስፍንን አምኘ

ያኔ እርሱን ማመኔም - ፍፁም የዋህ ሆኘ

“በብልቃጥ ተረግዞ - መስታወት ተወልዶ”

ድርጅት መባሉም - ወይ ነዶ ወይ ነዶ

እንግዲህስ በቃኝ - መስፍን የለ ሌላ

ጠቃሚ ላይሆኑ - የኋላ የኋላ

ፓርላማው ሰፊ ነው - ቧ ያለው መንገዱ

ሥነ ምግባር ብቻ መፈረም ነው ኮዱ።

 

ቀብቸ አሽሞንሙኘ - ከላይ ባረግሽ

አምባገነን ብለሽ - ስሜን አጠፋሽ

በገዛ ምላሷ - በገዛ አንደበቷ

ቃሊቲ ገብታለች - ከዘላለም ቤቷ

አትሳቂ እያልኳት - ባህር ማዶ ስቃ

አመጣችው እስሩን - ነቅንቃ ነቅንቃ።

 

ኩኩሉ አለ ዶሮ

በችግር ላይ ችግር ሆኖ የእኛ ኑሮ

 

እያንጓለለ …

ያ ገብስማ ዶሮ - ዘንድሮስ ምን አለ?

 

ያዝ ብርሃኑ …

ስሙልኝ ይኸን ሰው - እዩት ስም ሲያጠፋ

ምርጫ ውሸት ነው ብል - አለኝ ጥሎ ጠፋ

እኔስ ያከበርኩህ - በሽምግልናህ ነው

አመራር ሲመጣ- ጉድክን ሳስተውለው

አምባገነንነት - ፍፁም መለያህ ነው

 

እነ መለስ ዜና - ሰይጣን መርቋቸው

ተቃዋሚ ጀባ - ብለው በጫታቸው

አንገዋለለና - ልደቱን ሰጣቸው

አንገዋለለና - በየነን ሰጣቸው

አንተን በምራቂ - ይኸው ጨመራቸው

 

እያንጓለለ …

ያ ገብስማ ዶሮ - ዘንድሮስ ምን አለ?

 

ያዥ ብርቱካን …

ዓለም ዓለም … ዓለም ዓለምዬ

እሽሩሩ ስቃይ - ውረድ ከጀርባዬ

ደብተራው የማነ - አረጋሽ እህቴ

አብረው የሚኖሩ - ቤታቸው ከቤቴ

የእግዜር ፈቃድ ሆኖ - ቢሰማ ፀሎቴ

ለፍች ያብቃችሁ - ከዓላማችሁ ግብ

አምላክ ያውርድና - የሠላም ድባብ።

 

ዛሬ በመልዓኩ - በገብርኤል በበዓሉ

ወዲ መለስ ዜና - መሸረብ ጀመረ አሉ

ኃይሉ መላጣ ላይ - ሽሩባ ጎንጉኖ

“እኔን እኔን ሥራኝ” ይላል ልደት አብሮ

ፀጉር እንዲህ ይሠራል - ከክዳን ጀምሮ።

 

ተወኝ አላልኩም ወይ - ይህን ዓመልህን

ልክ እንደልደቱ - አንተም መክዳትህን

ልደቱስ ቢያንስ እንኳን - ይሂድ ይመለሳል

ምርጫ መጣ ሲሉት - መለስን ይወቅሳል።

 

እያንጓለለ …

ያ ገብስማ ዶሮ - ዘንድሮስ ምን አለ?

* * * * * * * * *

ኩኩሉ አለ ዶሮ

አራት ኪሎ አስመራን ምን ይላል ዘንድሮ

 

ያዝ መለስ …

ከሰማዩ በላይ - ያለኸው ሰማይ

ወዲ አፎም በጤናው - ዘግቶኝ ቀረ ወይ

ደግሞ በዚህ ምርጫ ያደናቅፍ ወይ?

የቀይ ዳማ ረጅም - ጎራዴ ታጣቂ

ልግደልህ እያለኝ - እኔ እርሱን ናፋቂ

 

እያንጓለለ …

ያ ገብስማ ዶሮ - ዘንድሮስ ምን አለ?

 

ኩኩሉ አለ ዶሮ

ኢሳያስ ምን ይላል ዘንድሮ

 

ልቤ አብጦ ጀግኘ - አንበሳ ነኝ ስል

ጦር አዘመትክና - አደረከኝ ድል

አስራ ሁለት ሌሊት - አስራ ሁለት ቀን

ከትግራይ ተነስትህ - ልትይዝ አስመራን

ጉዴ ፈልቶ ነበር - ክሊንተን ባይኖር

 

ያስጎራሃል አሉ - በየአምስት ዓመት

ደም የለመደ እጅህ - ሲሻ መስዋዕት

ሲሉ ሰምታ ሆኖ - ሆነና ነገሩ

ምዕራብ ያለው ሁሉ - ይመስልሃል ጥሩ።

 

ምርጫ ምርጫ - ብለህ ብትፈጥር ግርግር

እኔ ጌታህ ሆኘ - ካልሆንከኝ አሽከር

ውጊያ መቀስቀሱ - ምንጊዜም አይቀር።

 

እያንጓለለ …

ያ ገብስማ ዶሮ - ዘንድሮስ ምን አለ?

 

ያዝ መለስ ...

ጠያቂው ቢያስጨንቀኝ - ስለኤርትራ ሁኔታ

አልወዳትም አልኳቸው - እንዲያገኙ ፋታ።

ቁርጡማ ሲመጣ - አስመራ ልትያዝ

የኔ ተግባር ነበር - እነስየን ማዘዝ

አልጀርስ ሳገኝህ - ውል ልትፈራርም

አልነበረምና - እኔ ያልኩኝ ጥምጥም

ይናፍቃል ለካስ - እንደዚያ ወንድም።

 

እያንጓለለ …

ያ ገብስማ ዶሮ - ዘንድሮስ ምን አለ?

 

ያዝ ስዬ …

ተወኝ አላልኩም ወይ - ይህን አመልህን

ጫት እንዳዬ ጀዝባ - አስመራን መዞርክን

ጫትን ያዬ ቃሚስ - ቅሞ ይመለሳል

የአንተ ሁኔታ ግን - ግራ ነው እሚያጋባን።

 

እያንጓለለ …

ያ ገብስማ ዶሮ - ዘንድሮስ ምን አለ?

 

ኩኩሉ አለ ዶሮ

ህዝባችን ምን አለ ዘንድሮ

 

የሚመጣው ምርጫ - ምኞታችሁ መክኖ

የፍትህ አካላት - ፕሬስ ነፃ ሆኖ

ገለልተኛ ሆኖ - መከላከያችን

ገለልተኛ ሆኖ - የምርጫ ቦርዳችን

በነፃ እንዲሰማ - እንደ ህዝብ ድምፃችን

በዘር በኃይማኖት - መጋጨት ትታችሁ

ኤርትራና ትግራይ - አማራ ኦሮሞ ማለቱን ትታችሁ

አብዮት - አብዮት ማለት አቁማችሁ

ሁላችንን በእኩል - ሕጉ እንዲመዝነን

የሥልጣኑ ምንጮች - እኛ ህዝቡ እንሁን።


ዳግማዊ ዳዊት This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

ጥር 2002 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ