Poet Laureat Tsegaye Gebremedhinያግኝ ከበሬታ

“ያለፈው ጥረታችንን፣ ሳስታውሰው ትዝ ሲለኝ፣

ከሠራነው ነገር ይልቅ፣ ያልሠራነው ነው የሚቆጨኝ!”

ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድኅን

ማትያስ ከተማ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አቤት የቀን መሮጥ የወራት ችኮላ፣

ፀጋዬ ካረፈ አራት ዓመት ሞላ።

ጥበብም ልብሶቿን ጠቅልላ ከሄደች፣

ይኸው ከሱ ጋራ ቀናት አስቆጠረች።

አፍሪካም ታሪኳን ቅድመ ተፈጥሮዋን፣

ዞራ መመልከቻ አጥታ ቀረች ዓይኗን።

ኢትዮጵያም እንዲሁ ክብሯ ተዛነፈ፣

እማማ የሚላት ፀጋዬ ካረፈ።

 

ከታሪክ ተለየ ትውልድም ተጎዳ፣

ወደፊት ላገሩ ሊሆን ነው እንግዳ።

ሁሉን አጎደለ የፀጋዬ ሞቱ፣

ብርሃን ነበረ ላገር ለምድሪቱ።

አይቸር ሆኖበት አያበደር ዕድሜ፣

“ወይኔ!” እንዳለ ቀረ እያዘነ አዳሜ።

ደረትን ደልቆ እንባ አፍስሶ መግባት፣

ሁሉም ሙያ አረገው አጣ ሌላ ብልሃት።

ሆኖም ከመቼውም ያሁን ጊዜ ከፋ፣

ደህና ሰው ተለቅሞ ካገሪቷ ጠፋ።

ሠላም እንዲህ ስትርቅ እውነት ስትመነምን፣

ሰው ጠፍቶ ቁጭ አለ ሀገርን የሚያድን።

ሟችስ አንዴ ሞተ እፎይታ ነው ለሱ፣

ቆሞ እንደኛ መንደድ ቀረለት መጨሱ።

ስለዚህ አንጩህ ለብላቴን ጌታ፣

እንግዲህ ለሀገር ለራስ ነው ኡኡታ! …

አንዴ ነው ሞታችን አትበሉ ዳግመኛ፣

ከመከራችን ጋር ሁለቴ ነው የኛ።

 

ሞትስ እሱ እንዳለው ይሙት ምናባቱ፣

ጥፋቱ በርክቷል ልክ ነው ሎሬንቱ።

የስለት ልጅነት አርጎት ሆደ ባሻ፣

ላይመለስ ሄደ እስከመጨረሻ።

ትቶልን ግን ሄዷል ትልቅ ጋቢ ፈትሎ፣

አደራ ብሎናል እኛን ቋጩት ብሎ።

የሀገር መቀጨጭ የዕድገት ደረጃ፣

አስመሰለው እንጂ ቀጤማውን ሙጃ

አደላህ ባትሉኝ ባይመስልብኝ ጉራ፣

ከሱ የበለጠ ሼክስፒር ምን ሠራ።

በዓለም ደረጃ ሊቆች ሲቆጠሩ፣

ከፍተኛ ቦታ ተቀምጧል ወንበሩ።

ስለዚህ ይሄ ሰው መች ሞተ ብትሉኝ፣

ቃሉ ቢከብደኝም ምንም ቁጭት የለኝ።

 

አይወድም አውቃለሁ አበሻ እጅ መስጠት፣

ብዙም አይደንቀኝም “አልሞተም” ብትሉት።

ነገር ግን በብርቱ አትከራከሩ፣

የለም ታላቁ ሰው ቢቆምም ተግባሩ።

 

“ሞትም ይሙት” ያለው በፊት በጽሑፉ፣

ባድራጎቱ ጠልቶት አይደል ወይ መንቀፉ።

እንዳፉ ቢያደርገው ሞት እራሱን ቀብሮ፣

ምናለበት ነበር እሱ ቢኖር ኖሮ።

ምናለበት ነበር በሞት መቃብር ላይ፣

አበባ ሲያስቀምጥ እሱ ቆሞ ቢታይ

አዎ! አልሞተም በሉ በቃ ምን ታደርጉ፣

ዓርማዋ ሲጠፋ ያገር ወግ-ማረጉ።

የታሪክ አባቷ ያገር ክብሯ ሀብቷ፣

ተቆርቋሪ ልጇን ስታጡት ከቤቷ።

አልከራከርም አልሞተም ብትሉ፣

እውነቱ ቢላላም ቢከብደኝም ቃሉ።

ስለዚህ ይሄን ሰው ሞቱንም ብትክዱ፣

ውሸት አይባልም ያስኬዳል መንገዱ።

ሆኖም በአካል ቢኖር ከሀገር ባይጠፋ፣

ለዚህ ችግር ግዜ ይሆን ነበር ተስፋ።

ባይሞትማ ኖሮ ባይጫነው አፈር፣

አያጣም ነበረ ላሁን ሰዓት ምክር

ባይሞትማ ኖሮ መቃብር ባይውጠው፣

ያረካን ነበረ ተናግሮ ስንሰማው።

በቃኝ ይሄ ቁጭት ስለሌለው ጥቅም፣

ጽሑፌን ልቋጨው ወደ መዝጊያ ላዝግም

ፈጣሪ በምድር ላይ የሰጠውን ማዕረግ፣

ወደሱ ሲመጣ በሰማይም ሳይነፍግ

ከደጋጎቹ ጎን ከጻድቃኖች ተርታ

ነፍሱን ያኑርልን ያግኝ ከበሬታ።


 

ማትያስ ከተማ ከስዊድን This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

የካቲት 2002 ዓ.ም.

(ለሎሬት ፀጋዬ ገ/መድኅን አራተኛ ሙት ዓመት መታሰቢያ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ