አይ የኔ ዲያስፖራ (ታሪኩ ይገርማል)
አይ የኔ ዲያስፖራ
ታርኩ ይገርማል (ሳን ሆዜ - ካሊፎርኒያ)
ታሪከ ብዙ የኔው ዲያስፖራ፣
ጆሮህን ስጠኝ ትንሽ እናውራ፣
መጥቷል ክፉ ቀን የሚያስፈራራ፣
ላገር ለወገን ለኛ እማይራራ፣
መቼም አይደክምህ ዝም ብለህ አውራ፣
ታሪክ አጣቅሰህ ለጉራ፣
ባያቶች ገድል ስትኩራራ፣
ስንት ዓመት ሆነህ ፋይዳ ሳትሰራ፣
እየተጎነጨህ ውስኪና ቢራ፣
ዓርባ ዓመት ሆነህ ሥትንጠራራ፣
ውል ያለው ነገር ላገር ሳትሠራ፣
ፀጉርህ ነጎደ ሆነልህ በራ፣
የኔው ዲያስፖራ።
አልኩ ባይ ወሬኛ የወረቀት ነብር፣
ፀጉር ስትሰነጥቅ ስታወጣ አቃቂር።
ንገሩኝ ባይ ሆነህ በጊዜ ተጫወትክ፣
በዶላር ታውረህ ጮማህን እያኘክ።
አዬ መፍረድ ስትችል እንዲህ ይሁን ስትል፣
ከሞቀ ቤት ሆነህ ደሀ ስትጎነትል።
አንዳችም ሳትሠራ ሁሌ ስታወራ፣
ነቀዘች ሀገርህ በሽፍታ ተወርራ።
ወንዶቹ እየሣቁ ግባቸውን መቱ፣
እያርበደበዱ ሰውን እያገቱ፣
እየለቃቀሙ ሁሉን ከየቤቱ፣
ሃያ ዓመት አለፈ በህዝብ ሲጫወቱ።
አንተ ግን ለትዝብት ዛሬም ትጽፋለህ፣
ከሞቀ ታዛ ሥር ብዙ ታወራለህ፣
አትደራጅና ሸሚዝክን ሠብስበህ፣
መቀበሪያ ሰኔል እራፊ ታጣለህ።
የሰው አውሬ መጣ ጭራ ቀንድ አብቅሎ፣
በዘዴ በተንኮል ማህለቁን ጥሎ፣
ለቃቅሞ ሊያጠፋህ አናት ራስ ብሎ፣
ከዘረጋ ቆየ መረቡን ከጣለ፣ ዘራፍ ብሎ ምሎ።
ሁሉን ተቆጣጥሯል፣
ማን አለብኝ ብሏል፣
ኣንኳንስ ወገንክን ዲፕሎማትም ያስራል፣
በሃያ አራት ሰዓት ሀገር ልቀቅ ይላል፣
አውቀህ አታሳውቅ፣ መላ መፍጠር አትችል፣
ስትክብ ስታፈርስ ለሥልጣን ስትቸኩል፣
እኔ ያልኩት ይሁን ሌላውን አልስማ፣
መች ሰው ነው እከሌ እንዲህ ነው እሱማ።
ጓዳ ጎድጓዳውን አጥርተን ስናውቀው፣
እያልክ ስትከፋፍል ወኔውን ስትሰብረው።
ወይ ሠርተህ አታሳይ ወይ ሰው አታሠራ፣
አርባ ዓመት አለፈህ ስትጮህ ስታወራ።
እስኪ ቁጠርልኝ ድርጅቶችህን፣
ዘራፍ ብለው መጥተው በነው የጠፉትን።
እየለዋወጥህ ስሙን ስታወጣ፣
እምነት ሣትገነባ ስትል እናዋጣ።
መቻቻሉን ትተህ ሰው መምረጥ እረስተህ፣
አሠሡን ገሠሡን ጉድፉን አግበስብሰህ፣
ሠርገው እየገቡ እየበታተኑህ፣
የድርጅት ሥራ ምስጢሩ ሳይገባህ፣
እንደ ዛፍ ላይ ቁራ ዋ ብለህ የቀረህ፣
አሁንም አታፍርም ብዕር ታነሳለህ፣
ቆራጦችን ስታይ ኪስህን ደብቀህ፣
አዋጣ ያሉ እንደሁ ምክንያት ደርድረህ፣
ጉደኛው ዲያስፖራ ትፈላሰፋለህ፣
አንተ ምን ጎሎብህ ላውስ ምን ቸግሮህ፣
ሁለት ጉንጭ አቁተህ ሆድክን ትሞላለህ፣
በቃኝ ልባልግ ነው ሞልጬ ልሰድብህ፣
በጠርሙስ ጋጋታ ማታ ማታ አውርተህ፣
ምን አልኩኝ? ትላለህ ነገ ሲጠይቁህ፣
ምን ቀረኝ ትላለህ ምንስ ሀገር አለህ?።
ፋብሪካህ ተሸጠ፣ ወደብህ ተሰጠ፣
ያገርህም መልኳ ቅርጿም ተለወጠ።
ደም እንደጎርፍ ፈሶ አጥንት ተከስክሶ፣
ያ ግዑዝ ተራራ ተሰጠ መልሶ።
ወርቅ ማውጫው ሳይቀር የተቸበቸበው፣
ለም መሬቱ ጭምር ባዳ እጅ የገባው፣
እውን ካንተ መሀል ገበሬ ታጥቶ ነው?
ያገሬ ገበሬ ችጋር የሚነጨው፣
ደረቅ መሬት ይዞ ዘር የሚለምነው፣
ለም መሬት ተነፍጎት የሚያርሰው አጥቶ ነው።
በልቶ ለበይ ሠጪ አባላሽን መንግሥት፣
ወኔህን ሰልሎ ፀባይህን ገምግሞት፣
ዲያስፖራ ምን ሊያደርግ ያውራ ይላል ተዉት፣
ካገር ቤት ብቅ ያለ ዕድል ገጥሞት ድንገት፣
ሕንፃው ተገትሮ ሀብታሞች የሠሩት፣
እያለ ያወራል ሀገር አማረበት፣
ያንን ደሀ ረስቶ ሲንቃቃ ለምፅዋት፣
ካሜራ እንዳያጎድፍ እሱን መች አንስቶት።
ምስኪኑን ለማኙን ወደ ጎን አግልሎ፣
ልመና ሮሮውን ጆሮ ዳባ ብሎ፣
በረንዳ አዳሪውን አንጓሎና ዘሎ፣
ሕንፃ አንስቶ መጥቶ ሀገር ቀናች ብሎ፣
ማፈሪያ ዲያስፖራ ዩ ቲዩብ ላይ ሰቅሎ፣
በሙዚቃ አጅቦ ደስ ብሎት ፎልሎ።
ሊያሳይ ሊመፃደቅ ፈረንጅ ሊያታልል፣
ኢትዮጵያን ሊያሳየው ምን እንደምትመስል፣
ሀገር አለኝ አትበል እረፍና ሸቅል፣
ቅብጫናህን ሞልተህ ራስህን ደልል።
ሀገሬን ላገሬው ለደሀው ተዉለት፣
ሀገር አለኝ አትበል በቁም ረስተሀት።
ውስኪህን ተግተህ ያንተን አድማስ ፈጥረህ፣
በሞቅታ መንፈሥ ሠንጋ ፈረስ ጋልበህ፣
ተዝናና ተኮፈስ እኔ እከሌ እያልህ፣
ስትሞት ተገንዞ እስኪላክ ሬሣህ፣
በመዋጮ ገንዘብ አይቀርም መግባትህ፣
ያችው መከረኛ ጉድክን ቻይ ሀገርህ፣
ብትረባም ባትረባም መልሳ እስክትውጥህ፣
እንደ ወጣህ ብትቀር አሻፈረኝ ካልህ፣
መቼ እሷን ጎዳሀት ሸክሟን አቀለልህ።
አትደራጅና ቁምነገር አትሥራ፣
ወይ ላገር ሣትሞት ፍትህ ሣታበራ፣
ሃያ ዓመት አለፈህ ወሬ ስታወራ፣
ዘጠና በመቶው ሆዳሙ ዲያስፖራ፣
ተቀምጦ ያወራል እየጠጣ ቢራ።
አሥራ አምስ ሚሊዮን ወገኑ ተርቦ፣
ፈረንጅ ሲመፀውት ሲያግዝ ተረባርቦ።
ከጎን ሆኖ ያያል ወገኑ ሲረግፍ፣
መተባበር ጠፍቶ አዋጥቶ እሚደግፍ፣
ስንት መሥራት ሲችል ማኅበር መስርቶ፣
ሕጻን አዛውንቱ በችጋር ተቆልቶ፣
እያየ ተራቁቶ፣
ፀሐይ ላይ ተሰጥቶ፣
አለቅጥ ተከፍቶ፣
ህልውናውን ስቶ፣
አንገቱንም ደፍቶ፣
እንባውን ረጭቶ፣
ባምላኩም ተረስቶ።
አይ የኔው ዲያስፖራ፣
አንተው መርምር ያንተን ሥራ፣
ትግልህ አይሰምር አያንሰራራ፣
ስትሰበሰብ ስትጠራራ፣
እኮ ንገረኝ አርባ ዓመት ሙሉ ምን ተሠራ?
ግማሹን ዕድሜ ልማርህ፣
ወደ ሃያ ዓመት ልቀንስልህ፣
የሚሠራውን ግፍና በደል እያወቅህ!!
እንዴት ይህን ያህል ጊዜ ፈጀብህ?
ባንድ ኃይማኖት ተከፋፍለህ፣
መቻል መቻቻል ተስኖህ፣
አንድነት መፍጠር አቅቶህ፣
ፍቅርን መመስረት አዳግቶህ፣
እርስ በርስህ ተራኩትህ፣
አታፍርም ሀገር ወዳድ ነኝ ትላለህ፣
ሀገር ብቻውን፣ ያለ ሰው ምን ሊያደርግልህ፣
በጋራ ጠላት ካልዘመትህ፣
በሽምግልና ካልመከርህ፣
ጥበብ መዋደድ ካልሰበክህ፣
እኮ ነገረኝ ምንድን ነህ?
ወንበዴ በልጦህ ድክመትክን አውቆ፣
እያስፈራራህ ክላሽን ሰብቆ፣
ወንድ የለም ሲል ህዝብህን ንቆ፣
ቀምበር ሠርቶልህ ብረት ማነቆ፣
የናትክን ቀሚስ ባዋጅ አውልቆ፣
ያን ሁሉ ወቴ ሀፍረት አስታጥቆ።
የምንስ ጣሊያን የምንስ ናዚ፣
ከኛው መካከል እያለ አጋዚ።
ወንድም እህትክን ባደባባይ ላይ፣
በጥይት ባሩድ ይዞ ሲያደባይ።
ጉድ አንድ ሰሞን ብለው እንዳሉት፣
ያንተን ዋይ ዋይታ ሙዚቃ አድርጎት፣
ፉርሽካነትክን ቀድሞ ታዝቦት፣
ጀግና እኔ ብሏል የዓለም ጠበብት፣
በቀን ሺ ቢሞት እሱን ምን ገዶት፣
ለምንዛሪው አንተ አለህለት፣
ታጥቆ እስካንገቱ መሣሪያ፣ ውሸት።
የዌስተርን ሙቪ ተንኮል መማሪያ፣
ሆኗል ሀገርህ ፋብሪካው እዚያ።
እያመቻቸ ሸር ተንኮሉን፣
አንጎል መርዞ ማሳሳቻውን፣
መረጃ ብሎ በፊልም ያየውን፣
እግር ብረቱን ስቦ ምላጩን።
እዩ ጉድ ይላል ዘሬን ሊያጠፉት፣
ሕገ መንግሥቴን ሲጫወቱበት።
አንተም ተነስተህ መያዣው ጠፍቶህ፣
መሳቂያ ሆንህ ሃያ ዓመት ጮኽህ።
ይህን ገምቶ ያራኩትሀል፣
ሠላዩን ልኮ ዱሮ ቀድሞሀል፣
አምነህ ተወቀስ በእውቀት በልጦሀል፣
ራስክን ባትዋሽ ምን ይመስልሀል?
ከማን ጋ እንዳለህ መች መርምረሀል?
ከግር እስከ ራስ ከጥንት ወሮሀል፣
በደብል ኤጀንት ያጣድፈሀል፣
ስንት ገንብተህ ስንት አፍርሰሀል፣
ንቃ ዲያስፖራ ተው ይሻልሀል።
ኤጭ ወዲያልኝ ወዲያ ዲያስፖራው ወንድሜ፣
እኔም ያንተ ወዳጅ አለቀብኝ ዕድሜ።
አንተን ተማምኜ በተስፋ ጭላንጭል፣
ከዘበኛ አቅሜ ያለኝን ሳካፍል፣
አራት ወር ቀረችኝ ጡረታ ልገለል።
የለመደ ፀባይ አብሮ ያረጅና፣
ሲያሰፍረን ሲውል ወሬውን በቁና።
ልታስብለኝ ደረስክ ወሬኛው ነፍጠኛ፣
እንደ ወጣ ቀሪ ምስኪን ስደተኛ።
ደፋ ቀና እያለ ሕይወቱን ለሰጠ፣
ከመቶው ሲሠላ ካሥር ላልበለጠ።
ለሣተናው ኩሩ ያያቱን ላልረሣ፣
እዚሁ እኛው መሀል ለሚያየው አበሣ፣
ወቀሳው ሲበዛ ዲያስፖራ ሲነሣ፣
ማለፍ አልፈልግም ክብሩን ሳላወሣ።
ታሪኩ ይገርማል
ሳን ሆዜ - ካሊፎርኒያ



