የዱር ዝንጀሮ (ታሪኩ ይገርማል)
የዱር ዝንጀሮ
ታሪኩ ይገርማል - ከሣን ሆዜ (ካሊፎርኒያ)
ያገሬ ጫካ ዝንጀሮ አፍርቶ፣
ህዝቡ ሲጨነቅ ያን ተመልክቶ።
ነገሩን ፈርተው የጠረጠሩ፣
ካካባቢ አጥፉ ብለው መከሩ።
አገሬው ነቅቶ ስላልጠበቀ፣
ገባ ወጣ ሲል እየሰረቀ።
አልተወሰነም በጫካ ጎሬው፣
ሀገር ወረረ ክፉ ነው አውሬው።
ሠለጠነና የዱር ዝንጀሮ፣
አርሶ ሊበላ መሬት ቆፍሮ።
ሊሆን ገበሬ ሀገር ሊያለማ፣
ህዝብ ሰብስቦ አለ እንስማማ።
የሚገርም ነገር ሠሚ እሚያዳግት፣
ዝንጆሮን አይተው ሲሳለቁበት፣
ዳገት ሜዳውን ሀገሩን ወሮት፣
ቦታ አልበቃ አለው ፎገለለበት።
ሰዎች አድምጡ ይህንን ነገር፣
ከጫካ ወጥቶ ሊያርስ ሊቆፍር፣
መጣ ዝንጀሮ ሊያለማ ምድር፣
ጀምሯል አሉ አዝመራ ዘር፣
ብቅ ብቅ ሲል ለመመንጠር።
ሲወራ ዱሮ ያውም በተረት፣
ከዝንጀሮ ቁፍር እሸት ተበልቶለት።
መቼ ታግሶ አዝመራ እስኪደርስ፣
ማልዶ ተነሣ ቡቃያ ሊያፈልስ።
ግርማ ሞገሱ ሲያዩት ያስፍራል፣
ፈሪማ ካየ አሽትቶ ያውቃል፣
እህል በንጭጩ ይሸመጥጣል።
እንኳን ፊት አይቶ መንገድ ሰጥተውት፣
ዱሮም እንዲያ ነው ዝንጆሮ ሲሉት።
እሱው ሰርስሮ እሱው ቆፍሮ፣
ራሱ ምሶ ራሱ ቀብሮ።
እኛም አውቀናል ዱሮም ጮኸናል፣
ሰሚ ጠፋ እንጂ ብዙ ብለናል።
የጫካ አራዊት ምን ቢሰለጥን፣
ለምንም አይበጅ ምንም አይመጥን።
ለማዳ መስሎ ገራም እንሰሳ፣
ሀገር አጠፋ አበዛ አበሳ።
ችላ ብለውት ዝንጀሮን ንቀው፣
ለማየት በቃን ሲያስጨንቃቸው፣
እንቅልፍ ነስቶ ሲያራውጣቸው፣
ሰብሉን አውድሞ በራብ ፈጃቸው።
በወቅቱ ጀግና አዳኝ ሰው ጠፍቶ፣
ውሎ እያደረ ጉልበት አግኝቶ፣
መሃል ከተማ ዘው ብሎ ገብቶ፣
አጃቢዎቹን አደረጃጅቶ፣
ሀገር አጠፋ እንደ ሰላቶ።
አንበሣ ዝሆን ጦጣም በረረ፣
ካገር አስወጣው ነብሮም አልቀረ፣
ጅቦም ተስማምቶ ለሆዱ አደረ፣
ማነው ወንድ አለ ተወጣጠረ።
ዝንጀሮ ከፋ አንበሣ ሆነ፣
ዘር እያጠፋ እያመከነ።
በሰሜን ጥጉ ባናት የገባው፣
መሠረት ናደ አተራመሰው።
ጫካ ለጫካ ሲያደፍጥ ኖሮ፣
መዓት አፈላ የዱር ዝንጀሮ።
ነክሶ ጨረሰን ሰብሉ መች በቃው፣
በቁም ሲግጠን ብዙ ታገስነው፣
ሀገርክን ሲቀብር ቆመህ አትየው፣
አዳኝ ተነሣ ከበህ ጠዝጥዘው።
ታሪኩ ይገርማል - ከሣን ሆዜ (ካሊፎርኒያ)



