አገሬ

አሥራደው (ከፈረንሣይ)

(ግጥሙን በፒ.ዲ.ኤፍ. አስነብበኝ) 

Hagere 

ሰንፎብኛል ልቤ በስደት ተቀጣ፤

ባንደኛው ሲናፍቅ ባንደኛው እያጣ፤

ጊዜ እያንገላታ ያለንን ሲነጥቀን፤

ውሃውን!፤

አንቺ የቀዳሽውን፤

አንቺው ጠጭው ብለን፤

ከአገር አምልጠን፤

ጥለንሽ ኮብልለን፤

ምኑ ተቀበለን?!

ምን ዕድል ገጠመን?!

ምን ዕውቀት ገበየን?!

ምን ንብረት አፈራን?!

 

ልንገርሽ እምዬ፤

አገር ገበናዬ፤

ማረፊያ ጎጆዬ፤

ፍቅሬን እህህ … እያልሽ … ፍቅርሽን እርቄው፤

ናፍቆትሽን በጉያ በልቤ ሸሽጌው፤

ሆዴም እንዳይባባ በቂጣ ደልዬው፤

ሃዘን ብስጭቴን በጥርሴ ሸፍኜው፤

እኖራለሁ ኑሮ የኑሮ ተላላ፤

በወግ ያልታመሰ በወግ ያልተቆላ።

 

ይኸው በኔ ብሶ … ሁሌ እባዝናለሁ፤

ጉልበቴን ጨርሼ ሸንበቆ ሆኛለሁ፤

አጥንቴን ከስክሼ እንገዳገዳለሁ፤

ስጋዬን ዘልዝዬ በደሜ አጠቅሳለሁ፤

ዕድሜዬን ጋግሬ ሳልበላው አልፋለሁ።

 

እናም!

ልንገርሽ አገሬ፤

መመኪያዬ ክብሬ፤

ፍቅርሽን ተርቤ፤

ናፍቆትሽን ደርቤ፤

ሰንደቅሽን አንግቤ፤

ካንቺ የራኩበት ቢረዝምም ጊዜያቱ፤

አሁንም አልቀረ ባንቺ መመካቱ፤

ልቤ አንቺን መራቡ ላንቺ መባባቱ።


አሥራደው (ከፈረንሣይ)

ነሐሴ 28 ቀን 2002 ዓ.ም. (Septembre 3/2010)

ከእናት አገራቸው ኢትዮጵያ በስደት ርቀው ለሚንገላቱ ወገኖቼ መታሰቢያ ትሁንልኝ።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ