ለኛኮ ነው!

(በብርቱካን ሚደቅሳ ስም፣ በመላ አገሪቱ ለሚገኙ የፖለቲካና የኅሊና እስረኞች)

ጌታቸው አበራ (ጳጉሜን 2002 ዓ.ም./ሴፕቴምበር 2010)

ኢትዮጵያዊነት ማተብ ነው - ቃልም የዕምነት ዕዳ፣

እንደ ወርቅ በእሳት የሚፈተን - የመስዋዕትነት ፍዳ፤

ለምዕታት የዘለቀ - አገር-ምድሩን ያዳረሰ፣

እማያቋርጥ ጅረት ... ለትውልዶች ... የፈሰሰ፣

ቋት መከራው የደም ግብር - ስንት ጀግና ያሰየፈ፣

ልምላሜው ላገር ክብር - ዝና፣ ኩራት፣ ... ያተረፈ፤

ኢትዮጵያዊነት ማተብ ነው! በደም-ሥር ውስጥ የሠረጸ!

 

... እናም ታዲያ "ማነሽ" ሲላት - "ባለሣምንት፣ የወር ተራ" ...፣

ለቀጣዩ ህልውና - ችቦ ለኳሽ ባላደራ ...፣

አንዲት የዋህ - መንፈሠ-ርግብ፣

"ቃሏን" ሰጠች ልትወክል ግፉዓን ህዝብ!

 

ያንዲት ልጇን ፍቅር ትታ፣

ድሎት፣ ምቾት፣ ... ኑሮን ረስታ፣

ጨለማ ቤት መቆለፏ - ስቃይ፣ ሕመም፣ ምጥ ማትረፏ፣

ዕለታትን ...፣ ዐውደ-ዓመትን፣ ... በዝግ ብረት ማሳለፏ፣

ለኛ'ኮ ነው! - ለነዋሪው ለክብራችን፣ ለቀጣዩ ኩራታችን፤

 

እንጂማ'ኮ ላንድ ራሷ - ምን ገዷት ነው ላንዲት ነፍሷ?!

አቡናዊነት ነው ተግባሯ - ጴጥሮሳዊነት ዓርኣያ፣

ውጉዝ ከመ-አርዮስ - ዘረኝነት በኢትዮጵያ!

 

አንገት ደፍተን ላንታረድ፣ - ደረት ነፍተን ልንራመድ፣

እንድንችል በናት አገር፣ - በነፃነት ለመኖር፣

ለኛ'ኮ ነው! መታሰሯ!

እመ-ክብር ባላደራ!!


ጌታቸው አበራ ጳጉሜን 2002 ዓ.ም. (ሴፕቴምበር 2010)

* በሚያራምዱት እምነት ሳቢያና በሃሳብ በመለየታቸው ብቻ እንደጠላት ታይተው፣ ከጉራንጉር ማጎሪያዎች እስከ ታላላቅ ወህኒ ቤቶች፣ ያለፍትህና ያለፍርድ በመላ አገሪቱ ለታገቱና ለታሰሩ ያገሬ ልጆችና የስቃዩ ተካፋይ ለሆኑ ቤተሰቦቻቸው በሙሉ፤ መልካም አዲስ ዓመትን እመኛለሁ! አዲሱ ዓመትም ከቸሩ እግዚአብሔር ዘንድ ፍትህን የሚያገኙበት ይሁን! አሜን!!

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ