ዜጎች እና መሪ - ቺሊ

አንዱዓለም በቀለ (ከስዊዘርላንድ)

አልፎም አይረሳ ኖሮም ለታሪክ ነው፣

የአምላክ ጥበቡ ሁሌም እንግዳ ነው፣

ብቻ የሚገርመው ሁሌ ሚያሳዝነው፣

የሰው ልጅ ከዚህም አለመማሩ ነው።

 

በዛች በላቲኗ በዛች ትንሽ ሀገር፣

ድንገት በደረሰ አይነተኛ ችግር፣

ዓለም ጉድ ተሰኘ ታየ ብዙ ነገር፣

ታየ ድንገት መጥፋት ታየ ዳግም መኖር፣

በሰባ ቀናቶች ታየ ብዙ ነገር፣

የሰው ጥንካሬ የአምላክ ተዓምር፣

የባንዲራን ትርጉም የሀገርን ፍቅር፣

የመሪነት ሚና የዜጎችን ክብር።

 

እንዲህ ነው ኃላፊ እንደዚህ ነው መሪ፣

ሀገር የሚያስጠራ ዜጎቹን አክባሪ።

ዜጋው ሲጎዳበት እንቅልፉን የሚያጣ፣

ከገባበት ገደል ቆፍሮ ሚያወጣ፣

ሲደሰቱ ስቆ ሲያዝኑ አብሮ አዝኖ፣

በረሃ የሚያድር የሆኑትን ሆኖ፣

እንደዚህ ነው ጎበዝ የወገኑ ፋኖ።

 

ግብዝ ዜጎች ገድሎ ሬሳ ሲከምር፣

ሌላው አንድ ሊያድን ሲጨነቅ ሲዳክር፣

ስንቱን ጉድ ታቀፈች አቤት እቺ ምድር!

ምናለ እነመለስ ከነዚህ ቢማሩ፣

በቀራቸው ዕድሜ ቁም ነገር ቢሠሩ፣

ከልፈታቸው በፊት አንድ ቀን ቢኖሩ!

በዚህ በጎ ሥራ ምናለ ቢቀኑ፣

ከኮሪያ ገዝተው ዶክተር ከሚሆኑ፣

ለተንኮል ለጥፋት እንዲህ ከሚፈጥኑ፣

በህዝብ ተወደው መኃይም በሆኑ፣

ወይም ቺሊ ሄደው ፍቅርን ባጠኑ።


አንዱዓለም በቀለ (ከስዊዘርላንድ)

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ