በእውነቱ መንገድ (ሣለህ ኦምራን)
በእውነቱ መንገድ
ሣለህ ኦምራን
በእውነቱ መንገድ ሀቅን በሚያወርሰው፣
ልራመድ በቀናው ጸጸት በማይለብሰው።
በእውቀት መንቃቴ ደስታ ቢነሳቸው፣
ቢነሱ ሊያፈርሱኝ ባሰት ምላሣቸው፣
የመልካሙ ግብሬን ዋጋ ቢያሳንሱት፣
ኃያሎች ቢጋፉኝ ሃቄንም ቢያስቀሩት።
በእውነቱ መንገድ ሀቅን በሚያወርሰው፣
ልራመድ በቀናው ጸጸት በማይለብሰው።
አገር የሌለው ነው ባይተዋር ደካማ፣
ጉልበት የለው ኃይል ቢጮህ አይሰማ፣
ቀን ሰጥቶኣቸው በኔ ላይ አዛዦች ቢሆኑ፣
ሥርዓት ባጣ መልክ ዘንተው ቢወስኑ።
በእውነቱ መንገድ ሀቅን በሚያወርሰው፣
ልራመድ በቀናው ጸጸት በማይለብሰው።
በሕመም በስቃይ ጤና ባጣም እንኳን፣
ጎጆየ ፈርሳብኝ ባጣ ትንሽ ዱንኳን
አለኝታየ ያልኳቸው ጓዶቼ ቢሸሹኝ፣
ዘመድ ያልኩት ሁሉ ባይተዋር ቢያረገኝ
በእውነቱ መንገድ ሀቅን በሚያወርሰው፣
ልራመድ በቀናው ጸጸት በማይለብሰው።
ያላማየ ድጋፍ ምሶሶው ቢናጋ፣
አንጻሮቼ ቆመው ቢሉኝ የለው ዋጋ
የቀን ውድቅት ቢሆንብኝ ጊዜው፣
የዕድል ነገር ሆኖ ኑሮን ባያቃናው።
በእውነቱ መንገድ ሀቅን በሚያወርሰው፣
ልራመድ በቀናው ጸጸት በማይለብሰው።
ሆዴ ቢራብብኝ ጎድሎበት ማዕዱ፣
ሞልቶ ማቅረብ ባይችል ልክ እንደ ልማዱ፣
ማጣት እጄን ይዞ ቢያስረኝ በገመዱ፣
ከከጀለ የሰው እጅ ኑሮየ በግዱ።
በእውነቱ መንገድ ሀቅን በሚያወርሰው፣
ልራመድ በቀናው ጸጸት በማይለብሰው።
ሹመት ለኔ ሁኖ ባድግ ብመነደግ፣
አዛዥነት ስፍራ ብሆን ባለማዕረግ።
ወንጀለኛን ከተጠርጣሪ የመፍረድ ግዳጅ፣
ለመቅጣት ለመማር ቢያደርገኝም ፈራጅ።
በእውነቱ መንገድ ሀቅን በሚያወርሰው፣
ልራመድ በቀናው ጸጸት በማይለብሰው።
ቢትረፈረፍ ሃብቴ ብሆን ባለጸጋ፣
ያሻኝን ለመግዛት ሳያሳሳኝ ዋጋ።
ለመስጠት ለመንሳት እንደመጣልኝ፣
ወስኘ የማዝበት ሃብት ቢያሸክመኝ።
በእውነቱ መንገድ ሀቅን በሚያወርሰው፣
ልራመድ በቀናው ጸጸት በማይለብሰው።
በመልካሙ መንገድ ቅኑ በሚባለው፣
ልራመድ በእውነት ድካምም ቢኖረው።
በጸጸት ከምጋይ አይምሮየ ነዶ፣
ውስጤን ከማቀብል ለመንፈሴ መርዶ።
ሣለህ ኦምራን This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



