እንቅልፍ ለምኔ?! (አሥራደው - ከፈረንሣይ)
እንቅልፍ ለምኔ?!
አሥራደው (ከፈረንሣይ)
ጎጆዬ ሲቃጠል ደጄ ጩኸት ሞልቶ፤
አንድ ጣሳ ውሃ ይለግሰኝ ጠፍቶ፤
እሳቱ ሲጠብሰኝ፤
ወላፈን ሲገርፈኝ፤
እንቅልፍ ለምኔ? ለመቼ ሊሆነኝ?!
ትኋን ደሜን ሲመጥ፤
ስተኛ ስቀመጥ፤
ቁንጫ ሲበላኝ፤
ቅማል ሲያላምጠኝ፤
እንቅልፍ ለምኔ? ለመቼ ሊሆነኝ?!
ውሻ ሲቦጭቀኝ፤
ጅብ ሲሰለቅጠኝ፤
ነብር ሲያፈጥብኝ፤
አህያ ሲረግጠኝ፤
እንቅልፍ ለምኔ? ተኝቼ ምን ላገኝ!
ሙጃሌ ቦርሳ አርጋው እግሬ ሲውተረተር፤
መጠለያ ሆኖ ብብቴ ለመዥገር፤
እያከኩ ከምኖር፤
ስመጠጥ ከምኖር፤
እንቅልፍ ለምኔ? ቆሜ ከዘብ ልደር!!
አንጀቴ ሲላወስ ኮሶ ትል ተጣብቶኝ፤
ሳልበላ እንደበላ ቅልሽልሽ ሲያረገኝ፤
ወዘናዬ ጠፍቶ አመድ ተሸክሜ፤
ዊን ዊን እያልኩኝ በደከመ አጥሜ፤
እንቅልፍ ለምኔ? ልደር እንጂ ቆሜ!
ዝንቦቹ ሲወሩኝ፤
ትንኝ ሲያሾፍብኝ፤
ወባ ሲያስጨፍረኝ፤
እስክታ ሲያስመታኝ፤
በሳቄ አሳዝኖ ባዘኔ ሲያስቀኝ፤
እንቅልፍ ለምኔ? እንኳንስ ለሥጋ ለነብሴም አልበጀኝ!
ውሃ ጥም ሲያጋየኝ፤
ችጋር በስለቱ ሲያርደኝ ሲያላምጠኝ፤
በሽታ በርግጫ በካልቾ ሲለጋኝ፤
ብርድና ፀሐዩ ሲፈራረቅብኝ፤
እንቅልፍ ለምኔ? ለመቼ ሊሆነኝ?!
ሰማይ ላይታለብ ምሎ ተገዝቶ፤
መሬቷ መክና የሚበቅል ጠፍቶ፤
ፀሐይ ፈገግ ላትል ጥቁር ጭንብል ደፍታ፤
ጨረቃ እርም ብላ ከሱባዔ ገብታ፤
እንቅልፍ ለምኔ? ማሸለብ መኝታ!
እንቅልፍ ለምኔ? መጋደም መኝታ!
አንድ ቀን
በችግር ለሚማቅቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ መታሰቢያ ይሁን!



