«እኔ ላንቺ ብዬ …» (ወለላዬ)
«እኔ ላንቺ ብዬ …»
ወለላዬ ከስዊድን (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)
እኔ ላንቺ ብዬ ላንቺ ግርማ ሞገስ
ዝናሽን ሳወራ ስምሽን ሳወድስ
ተፈጥሮ በሰጠሽ ውበትና ጸጋ
ስደሰት ስደነቅ አስሬ ሳወጋ
ስዘምር ስጠራሽ በየአውራ መንገዱ
ልጅነቴ አለፈ ጃንሆይ ወረዱ።
እኔ ላንቺ ብዬ ለውጡስ መቼ ደላኝ
ደርግን እንቢ ብዬው ቀጥቅጦ ለቀቀኝ
ያንን ሁሉ ችዬ በአጥንቴ ቆሜ
ስጽፍ አሳለፍኩት ስምሽን በደሜ
ገጽታሽን ሳልኩት እስከነ ታሪክሽ
አካሌ ሞራ ላይ በሀሞቴ ፈሳሽ
ሳነሳሽ ስጥልሽ ጠፍቶኝ መላቅጡ
መንግሥቱ ሄዱና አቶ መለስ መጡ
ምስቅልቅሉ ወጣ ተገለባበጠ
የነበረው ሁሉ መልኩ ተለወጠ
እኔ ግን አለሁኝ እዛው ተቸክዬ
ፍቅርሽን ታቅፌ መከራሽን ችዬ
ቢርበኝም እንኳን የምልሰው ባጣ
እኔ ላንቺ ብዬ አይቀጡም ብቀጣ
አለጥፋት ቢያስሩኝ ብገባም ጨለማ
ቢቀጠቅጡኝም ብቆስልም ብደማ
አቤቱታ ሰሚ አጋዥም ባላገኝ
አይዞህ ብሎ ደራሽ መመኪያም ባይኖረኝ
እልቤ ቋጥሬ ያንን ያንቺን ፍቅር
እደጅሽ ታዛ ስር ደጃፍሽ በማደር
አለዛም ወጥቼ እርቄ በርሬ
ከስቃይ ላድንሽ እኔ ተቸግሬ
የትም ቦታ ብደርስ ጨርሶም ብጠፋ
በሕይወት ለመኖር ባይኖረኝም ተስፋ
ባንቺ ግን አምናለሁ አትሞቺም ጨርሰሽ
መቃብር ብወርድም መጠሪያ ስሜ ነሽ
ለዚህ ሁሉ እውነት ለተናገርኩት ሐቅ
መስክሩልኝ ሳልል ማንንም ሳልጠይቅ
እኔ ላንቺ ብዬ ላንቺ ግርማ ሞገስ
እጓዛለሁ ገና እስከዛ ጫፍ ድረስ።
ወለላዬ ከስዊድን (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)



