ወዳጄ (ከአርቲስት ሰርካለም ተፈሪ)

 

አንተ የወንዜ የዋህ

ከአንደበቴ የማ’ጠፋው

ብትተወኝ የማልተውህ

ብትቆርጥ እንኳን የማልቆርጠው

በሆዴ ጉድህን ይዤ

በደስታህ ደስ ሲለኝ

በክፋትህ ተክዠ የምኖረው

ሆዳምም ሆንክ ወሬኛ

ክፉም ሆንክ ቀማኛ

በውስጤ ብልጫ አለህ

አፌ እንኳን ሰላምታ ቢነፍግህ።

እናም ወዳጄ አንተ የዋህ

እጅህን በጅህ አትንከስ

አትፍተለው እስኪበጠስ።

አንተም ለወገንህ አድላ፤

ለባእዳን አታስቀድም

የደበከውን ፍቅር አውጣው፤

ከውስጥ ከልብህ ግርግም

የሗሊት ከመገስገስ የደጋጎችን ስም ይዘን፣

እስቲ በጎ በጎ እናስብ

ትንሽ እንኳን ቅን እንሁን።

ክፋት ምን አቅም አለው

ያው ክፍት ነው ምሱ

መከፋፈል፣ መጠላላት፤ መጨራረስ እርስ በርሱ

ጸብም ፍቅርም ድሮም አለ፤

አሁንም ቅኝቱ አንድ ነው

አንጀት እየቆረጠ ቢሄድም ክፉ ስለት እየሳለው።

እናም ወዳጄ አንተ የወንዜ የዋህ

እያማኸኝ የምኖረው ተደብቄ ከጉያህ

እጅህን በእጅህ አትንከስ አትፍተለው እስኪበጠስ

አሳልፈህ አትስጠኝ

ባስከፋህም ገስጸኝ፤

እኔስ ካላንተ ማን አለኝ።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ