የሽማግሌ ያለህ! (ይነጋል በላቸው)
ይነጋል በላቸው
ድሮ የምናውቀው፣ ወጉ የሽምግሌና
በደልን የሚያረክስ፣ የጎበጠውን የሚያቃና
ነበር ብቃት ያለው፣ የሞራል ልዕልና።
ዛሬ-ዛሬማ! ለስሙ ነጭ ጸጉር ያበቀሉ
ቆብ የደፉ፣ ነጠላ ያንጠለጠሉ
ስብዕናችሁን አዋርዳችሁ፣ ለምኑ የሚሉ
የሽምግልና ሚዛኑን ያዛቡ፣ ጭነቱን ያቃለሉ
ኧረ ምን ጉዶች በቀሉ - ተፈለፈሉ።
ለጉልበተኛ ያደሩ፣ ለግፈኛ የሰገዱ
ላለው እጅ የነሱ ያጎበደዱ
የዘመን ውርጃ ጭንጋፎች
የባርነት ጋሻ-ጃግሬዎች
ክብረቢስ ለማኞች
ባደባባይ መኮፈስን የመረጡ
በብርሃነ-መስኮት ለመታዬት የቋመጡ
ኧረ እንዴት ከወዴት መጡ።
ሊያደርጉን የተነሱ ውዳቂ፣ ትቢያ፣ እራፊ
የውርደት ማቅ ለባሽ፣ አንገት ደፊ ቀራፊ
በዙሪያችን የተዘሩ ፍላጻ፣ እሾህ፣ አሜኬላ
የሆኑብን የደህንነታችን መንገድ ኬላ
ሊያሸክሙን የተነሱ የመከራ አበሳ
የማይሽር የሕሊና ቁስል ጠባሳ።
መሄጃ መድረሻ ሳያሳጡን
ጭራሹን ሳያጠፉን
ጎበዝ! ወጊዱ እንበላቸው ጥፉ ከፊታችን
ይሻላልና እርዛት ጥማት
እስራትና ግርፋት፣ ብሎም የክብር ሞት
ትውልድ ከሚጠፋ፣ ላይመለስ አገር ከሚወድም
ከዓለም ለዘላለም!!!
ይነጋል በላቸው
ነሐሴ 21 ቀን 2004 ዓ.ም.
ለፍትህ ሲሉ በግፍ ለታሰሩና ለተጋዙ