ሁለት ዓብይ ነገር፤ እናትና ሃገር (ኃይለጊዮርጊስ ደስታ)
ኃይለጊዮርጊስ ደስታ
ከነገሮች ሁሉ ሚዛን የሚደፉ፤ ሁለት ዓብይ ነገር፣
ወደ ላይ ቢወጡ፤ ወደ ታች ቢወርዱ፣ በዚች ዓለም ምድር፤
ተምሳሌት፣ እኩያ፣ ወደር የሌላቸው፤ እናትና ሃገር።
“የኔቢጤም” ብትሆን መንገድ ዳር ኑሮዋ፣ ሰምበሌጥ፣
ፕላስቲክ፣ ከሰኔል ቢሰራ መኖሪያ ጎጆዋ፣ አልያም
ንግሥቷን ዙፋን ላይ ተቀማጭ የሥልጣን እጣዋ፣
እናት ያው እናት ነች። በሌላ አይተኳትም በእናትነት ክብሩዋ። (2)
ለም አፈርም ይሁን መላጣ፤ መረሬ፣ ኩርንችት፣ አሸዋ፣
መደበቂያ ዋሻ ፣ ምሽግ ለዱር አውሬ፣ ወይ ፈረስ
ማቆሚያ፤ ግጦሽ ለአንድ በሬ፣
አልያም ለዶሮ፤ በጓሮ ማቆያ እየሰጡ ጥሬ፣
ሃገር ያው ሃገር ነው፤ አይፍቁትም ስሙን፣ አይንቁትም ክብሩን፣
ምን! ቢያወዳድሩት፤ ቢለኩት በሚዛን፤ ከአደጉት ጋር ዛሬ። (2)
ሲበርድ በጉያዋ፤ በእቅፏ ታቅፋ፤ ሲርብ ጎንን ዳሳ፤
ሲጨንቅም ተጨንቃ፤ ሲያለቅሱ አብራ አልቅሳ፣
ሲደሰቱ ስቃ፤ ሲከፉ ተከፍታ፤ ሆዷን ሆድ-አስብሳ፣
ደብቃ፣ ከልክላ፣ ከጠላት ከክፉ፣
አሳዳጊ እናት ነች፤ ሌላ ማንም የለም ቢወጡ ቢለፉ። (2)
ሃገር ነው፤ ወንዝ ነው፤ ለጀግናም ኩራቱ፣
አባጣ-ጎርባጣው፤ ዳገት ቁልቁለቱ።
እንደ እናት ከለላው፤ እንደ እናት ምሽጉ፣
የክፉ ቀን መውጫው፤ ዘር፣ ቋንቋን ሲላጉ፤ ሥቃይን ሲዋጉ። (2)
የሃገር ማንነት፤ የሃገር ትርጉሙ፣
መለኪያ መስፈርቱ፤ ተቀዳሚ ቃሉ፤
ብዙ ነው ትርጉሙ፣ ሃያል ነው ምስጢሩ፣ ንገሩን ለሚሉ። (2)
የሃገር ማንነት፤ የሃገር ትርጉሙ፣
መለኪያ መስፈርቱ፤ ተቀዳሚ ቃሉ፤
በእምነት ሲተሳሰር ወንድም ከወንድሙ። (2)
በቋንቋ ሲዋሃድ፤ ድንበር ከድንበሩ፣
ጎሳ ከጎሳ ጋር፤ ብሄር ከብሄሩ።
እጅና ጓንት ሆኖ በአንድ ላይ ሲሠሩ፣ ለአንድ
አቋም ሲያብሩ፤ ለአንድ ሃገር ሲኖሩ፣
የሃገር ማንነት ያኔ ነው ትርጉሙ፤ ገሃዱ ምስጢሩ። (2) ጋራ
ሸንተረሩ ብቻ አይደለም ሃገር ዳገት ቁልቁለቱ፣ ሕዝቦቿም
“ሃገር” ነው፤ ስፋቱ፣ ልማቱ፤ በቁጥር ውልደቱ። እምነትም
“ሃገር” ነው፤ ባሕልን ጨምሮ፣
አንጡራ ሃብታችን፤ የሚለየን ከዓለም “ረቂቅ-ቋጠሮ”።
ሙዚዬም፣ ገዳማት፣ አፈሩ፣ ፀበሉ፣
ዋልያ፣ ኒያላ፣ የአማርኛው ቁጥር፣ መለያው ፈደሉ፣
ይሕ ሁሉ “ሃገር” ነው፤ የአንድምታ ትርጉሙ ምስጢራዊ-ቃሉ። (2)
እንኳንስ ነፍስ ያለው ሕያው በአካል ቆሞ፣
“አርዲና ድንቅነሽ” የተገኙ አጥንቶች ከዚሕ በፊት ቀድሞ፣
ምስክሮች ናቸው፤
ለሃገር ትርጉሜ፤ ያስጠራሉ አገርን፤ ተለይተው ደግሞ። (2)
“የኔቢጤም” ብትሆን መንገድ ዳር ኑሮዋ፣ ሰምበሌጥ፣
ፕላስቲክ፣ ከሰኔል ቢሰራ መኖሪያ ጎጆዋ፣ አልያም
ንግሥቷን ዙፋን ላይ ተቀማጭ የሥልጣን እጣዋ፣
እናት ያው እናት ነች። በሌላ አይተኳትም በእናትነት ክብሩዋ። (2)
ለም አፈርም ይሁን መላጣ፤ መረሬ፣ ኩርንችት፣ አሸዋ፣
መደበቂያ ዋሻ ፣ ምሽግ ለዱር አውሬ፣ ወይ ፈረስ
ማቆሚያ፤ ግጦሽ ለአንድ በሬ፣
አልያም ለዶሮ፤ በጓሮ ማቆያ እየሰጡ ጥሬ፣
ሃገር ያው ሃገር ነው፤ አይፍቁትም ስሙን፣ አይንቁትም ክብሩን፣
ምን! ቢያወዳድሩት፤ ቢለኩት በሚዛን፤ ከአደጉት ጋር ዛሬ። (2)
ስለዚሕ፤
ለኔ ምድር ማለት፤ ለኔ ሃገር ማለት፤ ለራሴ ትርጉሙ፣
እምነትና ባሕል፤ ታሪክና ቅርሱ፣ ብራናው ቀለሙ፣
አፈሩ፣ ፀበሉ፣ ገዳማት፣ አዝርዕቱ፣ ሰብልና ቅመሙ፣
ጋራ ሸንተረሩ፣ ወንዝና ዳገቱ፣ የብሔር ጥምሩ፣
የጎሳው ውሕደት፤ ሕብር ስብጥሩ፣
በአንድነት ልዩነት፤ ግምደት ትሥሥሩ፣
በዘርና ቋንቋ ግፊያው መቃቃሩ፣ ልዩነቱ ጠቦ፤
“ዩናይትድ-ኢትዮያ” ሕልሙ ተደራጂቶ፣ አብቦ ተውቦ፣
አንድ ሃገር፤ አንድ ቋንቋ፣ አንድ ሕዝብ በአንድ ላይ፣
ተመስርቶ ማየት ኢትዮጵያ ምድር ላይ። (2)
ለዚሕ ነው፤
ሁለት ዓብይ ነገር፣ ከነገሮች ሁሉ ሚዛን የሚደፉ፣
እናትና ሃገር ረመጥ ሚሆኑት እንደዋዛ ሲያልፉ። (2)
ቅዱስ ጴጥሮስ ከተማ
2004 ዓ.ም፤ ኃይለጊዮርጊስ ደስታ