ሰባኪ ወንጌል ሽመልስ ተሊላ (ኤድመንተን - ካናዳ)

ታይቶ ያልታወቀ … በተዋህዶ እምነት

መከፈል መለየት ለሀያ አንድ አመት

ከፍዳሜው ደርሶ መወገድ አለበት፤

ጳውሎስ ያወገዘው እኔ የገሌ ነኝ

መንጋውን ከፋፍሎት ተለያይቶ ሲገኝ

ያስከተለው መዘዝ እጅግ ያሳዝናል

ድብልልቁ ወጥቶ ነገር ዱለት ሆኖአል፤

 

ለዘብተኛ አክራሪ ... መናፍቅ፤ ተሃደሶ

እባብና ተኩላ ... የበግ ለምድ ለብሶ

ከአንድ በረት ገብቶ ላመነበት ጎራ

በጨበጣ ውጊያው የልቡን ሲሠራ

እክህደከ ሰይጣን … ወጊድ ካልተባለ

ህልውናን ማጣት እስከመድረሰ አለ፤

እጅግ በረቀቀ ተንኮልና ዘዴ

የወረረን ጠለት ፋታ ይሰጣል እንዴ

ትምህርተ ክህነት … ዜማ አቋቋም ሳያውቅ

ቄስ ዲያቆን ተብሎ ራስ የሚያመጳድቅ

ቤተ-መቅደስ ደፍሮ ቅዳሴ እምያበላሽ

ምዕመን አዋኪ ሥርዓት አፋላሽ

ግርግር ለሌባ ያመቻል እንዲሉ

ከአባቶች ቀርበው የሚያደቡ አሉ፤

በሥልጣን የሹመት ጥቅም የሚነግዱ

በሁለት ቢላዋ መብል የለመዱ

እርቅ፤ ሠላም፤ አንድነት … ማየት የማይወዱ፤

በአፍቅሮ ነዋይ ልቦናው የጠፋ

ጨካኝ የበላበት ወጭት የሚደፋ

አባይ ከአስታራቂ ሸንጎ ተቀምጦ

ድንጋይ ያቀብላል የባሰ አበጣብጦ

ከአለማዊ ሕይወት … ከግልም ጥቅምም በላይ

እግዚአብሔር ይልቃል የሚያኖር በሰማይ፤

ንጉሥ፤ ፕሬዝዳንት፤ ፓትርያርክ … ተራ ሰው

ከመሞት አይቀርም ወር ተራ ሲደርሰው፤

አብርሃም በእምነት ለእግዚአብሔር ታዞ

መስዋዕት አቀረበ በልጅ ካራ መዞ፤

ሙሴ የወገኑን ጥቃት ተበቅሎ

ለአርነት ወቶአል ቤተመንግስት ጥሎ

የጌታ ሃዋርያት ሁሉን ነገር ትተው

ተከትለውታል የሞተውን ሞተው፤

ኖህ በኃይማኖቱ መርከብ ሠርቶ የዳነው

ያአራዊቱን ጠባይ ታግሶ ችሎ ነው

አባታችን አዳም ትእዛዙን ተላልፎ

ሞትን አመጣብን ዐጋውን ተገፎ

ፈርኦን ፈጣሪን አላውቅም ስላላ

በኤርትራ ባሕር ቅጣት ተቀበለ

ዮናስ አሻፈረኝ አላደርግም ብሎ

አሳ አንባሪ ዋጠው ከመርከብ ተጥሎ

የመረጠው መንገድ አላዋጣ ቢለው

ወደ እግዚአብሔር ጮሆ ከነነዌ ተፋው

የሎጥ ሚስት አልሰማ አልታዘዝ ባለች

ወደ ሁዋላ ስታይ ሃውልት ሆና ቀረች

ሄሮድስ ለእግዚአብሔር ክብር ስላልሰጠ

መልአኩ መቶት ትል ተበልቶ ሞተ፤

ወንበዴ እግዚአብሔርን አምኖ ስለፈራ

በገነት ነህ አለው ዛሬ ከእኔ ጋራ

ጳውሎስ በዛቻ ጌታውን ሲያሳድድ

አይኖቹን ታውሮ ተረትቶ በመንገድ

ምን ላድርግ ልታዘዝ ብሎ ተማደነ

ሳይማር ተምሮ በወንጌል አመነ

የምሥረች ስብኮ ለዓለም ብርሃን ሆነ፤

ከዚህ ሁሉ መማር ማወቅ ካልተቻለ

ተግባር የማይገልደው እምነትም አየደለ፤

ሃያ አንድ አመታት የቆየውን ችግር

በርጋታ ለመፍታት ያስፈልጋል መጣር

በውድም በግድም ላይቀር መሸነፉ

እኛን ከሚበትን እንራቅ ከክፉ፤

ያለፈውም አልፎ የሆነውም ሆኖአል

ለወደፊት ማሰብ እጅጉን ይበጃል

እኔ ያልኩት ካልሆነ እልህ ተያይዘን

አብረን እንዳንጠፋ ዛሬም ተወጋግዘን፤

ትተን ለምንሄደው ዓለምና ስልጣን

ተከታዩ ትውልድ በታሪክ አይቅወጣን፤

ጌታ የበደሉትን ክሶ እንደታረቀ

አባታችን ሆይን … ማለት ከታወቀ

ይቅር መባባሉ ለምን ከአማኝ ራቀ

የሰው እጅ ያልሰራት በሰማያት ያለች

የኪዳኑ ታቦት መቅደሱ አንድ ነች

አዚህ ተለያይቶ ለመገባት አመትች፤

እስኪ ሊቃውንቱ ቅኔውን ተርጉሙ

ወርቅና ሰም ካለው ቀኖና ቀለሙ፤

አባቶች ምከሩ ዶም ሱባኤ ግቡ

የአንድ ልብ ልመና መስዋዕት አቅርቡ

የባሰ እንዳይመጣ የበለጠ አስቡ

የተበተነውን … ዘር መንጋ አሰባስቡ

እናንተ ታርቃችሁ እኛንም አስታርቁ

ግልገልና ጠቦት በጎቹን ጠብቁ፤

በገዳም ያላችሁ መናኝ መነኩሳቱ

እንደ ተክለ ኃይማኖት ለጌታ አመልክቱ፤

ምዕመን ለአንድነት ለደሎት ተነሱ

ወደ እግዚአብሔር ጩሁ በእግዚኦታ አልቅሱ

እርሱ መልስ ይሰጣል ነነዌን አስታውሱ፤

እመቤቴ ማርያም አማልጂን ከልጅሽ

አንቺ ለምነሽው መቼም እንቢ አይልሽ፤

ባለስልጣኖችም እግዚአብሔርን ፍሩ

ፈርኦናዊውን ልብ ለክብሩ ስበሩ፤

በስራው አትግቡ ይልቅ ተባበሩ፤

የተጀመረው እርቅ ጥረቱ እንዲሳካ

በጴጥሮስ መንበር ፓትርያርክ እንዲተካ

አባቶች በሰሩት ቀኖናና ዶግማ

ችግሮች ተፈተው ከእውነት እንስማማ፤

አማራጭ የሌለው መፍትሄ የሚሆነው

አሀዱ ሲኖዶስ ሲመራን ብቻ ነው፤

ለተዋህዶ አንድነት የኃይማኖት መቅድም

ያ ከፋፍሎ የለየን ስህተት አይደገም፤

አባቶች ካህናት ለአንድነት ደልዩ

ተዋህዶ ናችሁ የማትለያዩ፤

ካህን ምእመኑን ቤቱን ከፋፍላችሁ

በዚያ ተጠቃሚ አትራፊ የሆናችሁ

ፍጻሜአችሁ ላያምር ከንቱ ደከማችሁ

ፈራጅ እግዚአብሔርን ፍሩት እባካችሁ፤

ከዚህ የቀደመ የችግሩ መፍቻ

የማይሆን ይሆናል ቀንቀሎ ስልቻ

ይብስ የሚያመጣ መቀየር ጉል

መንጋን የሚጠብቅ አንድ ሲኖዶስ ብቻ፤

አሀዱ ሲኖዶስ ብቻ የለውም አቻ።


ከሰባኪ ወንጌል ሽመልስ ተሊላ (ኤድመንተን - ናዳ)

 

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ