ስደት ... 2 (ሃብታሙ ደሃ)
/የቆመው ወንዝ …/
ሃብታሙ ደሃ (ከሀገረ ስዊድን)
የስደት ህይወቴ ብዙ ቢያሳየኝም
ወንዝ ይቆማል ብዬ ጠብቄ እንኳ’ አላውቅም፤
በርግጥ እንደማውቀው የሀገሬ ወንዝን
ሲያገላብጥ እንጂ ግንድ አለት ቋጥኙን
... ወይ ንብረት አውድሞ ሲያስለቅሰው ስንቱን
አላየሁ እስካሁን ‘ወንዙ ድልድይ ሆኖ ሲያገናኘው ሰውን፤
ዛሬ ግን ታዘብኩኝ ... በስደት ሀገሬ እንደበጋው ሁሉ ወንዝ እንዲያሻግረኝ
ድልድይን ፍለጋ ባይኔ እያማተርኩኝ ... እኔ ስደተኛው ስደናበር ቢያየኝ
ወንዙ እየታዘበኝ ... በክረምት ሞገሱ በአጀብ ቆሞ ጠርቶኝ
አንደበት አውጥቶ “ና ተራመድብኝ ... ተሻገረኝ!” አለኝ፤
ባለሁበት ዓለም እንኳን ሰው ግዑዙ ወንዙ እንኳን ታዝቦኝ
ከዘመኑ ጋራ ‘ራሱን አዘምኖ ተ-ዓ-ም-ር ሊያሳየኝ
“ና ተራመድብኝ ... ተሻገርም! ...” ቢለኝ
እኔም እንደወቅቱ ራሴን አሠልጥኜ መራመድ ተስኖኝ
አለሁ ... እንዳለሁኝ
ቀኝ መቀኘት ትቼ ... በግራ እንደዋልኩኝ፤
እናም በስደቱ ... ከህይወት ስንክሳር ከልምድ የተማሩ
የተለወጡቱ ... ጥሪውን የሰሙት ፈጥነው ሲሻገሩ
እኔ ግን በፍርሃት ... ራሴን በራሴ እያልኩ እሹሩሩ
ወንዙን አልረገጥኩም ... ቆምያለሁ ከዳሩ፤
ግን በህልሙ ዓለሜ ... አለሁ እንዳለምኩኝ
የስደት ሀገሬን ከትውልድ ሀገሬ ... እያነፃፀርኩኝ
በልዩነታቸው ... እየተገረምኩኝ
ወይ ሀገሬ ብዬ ... ከልብ እየቆጨኝ
በክፉው እያዘንኩኝ ... ይቅርብን እያልኩኝ
በበጎው በመቅናት ... እየተመኘሁኝ
ስነቃ እየረሳሁ ... ስተኛ እያሰብኩኝ
ሳንቀላፋ ደግሞ ... መልሶ እየቆጨኝ
ለውጥ እንደተመኘሁ ማምጣት ግን ተስኖኝ
አምጪ ... እየጠበቅሁኝ
ገብቶኝ ወይ ሳይገባኝ
ከቅዱስ እርኩስን ሁሌ እንዳስቀደምኩኝ
አለሁ ... እንዳለሁኝ
መኖር ከተባለ ... በርግጥም አለሁኝ፤
ሃብታሙ ደሃ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ከሀገረ ስዊድን የካቲት 2004



