መዥገርን ስትነቅል፤ ተጠበብ ከራሱ እንዳይቀር ራስቅል (ጎዶሊያስ)
ጎዶሊያስ
መዥገርን ስትነቅሉ ከራሱ ተቆርጦ ገላ ውስጥ ከቀረ፣
ማመርቀዙ አይቀርም በዋለ ባደረ፣
መጋዝ መሳይ ጥርሱ ስጋ ውስጥ ስላለ ስለተቀበረ።
ስለዚሕ፤
አነቃቀሉ ላይ ጎድሎበን ጥበቡ፣ ተስኖን ምስጢሩ፣ በደም
የተነፋው፣ በደም የሰከረው ሆዱ የመዥገሩ፣ ተቆርጦ
ቢወድቅም በአቤ በ”ዲዲቲ”ው ከላይ ከመንበሩ፣
ተግባር ይቀረናል ከነሸለፈቱ፣ ከግብረ በላው ጋር መጣል ወደ ዱሩ።
አልያ፤
የተጣባው መዥገር ያለው ከጉያ ስር፣
እያመረቀዘ፣ እያሰለሰለ፣ እያደረ ኣደማት ባሰ በዚያች ሃገር።
የሶስት ሺሕ ዘመን የነጻነት ዓርማ፣
የደም፣ የአጥንት ክፋይ፣ የብስራት ከተማ፣
የአፍሪካ ነጻነት፣ የአድዋ ድል ዜማ፣
እንዴት? በሸለፈት፣ በእንክርዳድ ፍሬዎች፣ አንጡራ ታሪኳ ነጭ ስምዋ ይቀማ።
ለኢትዮጵያ ክብር፤ ለእማማ ባንዲራ፣
ሺዎቹ በገደል፣ ሺዎች በተራራ፣
ሺዎቹ በአራዊት፣ ሺዎቹ በአሞራ፣
የተሰውላትን ምርጥ የምስራቅ ጮራ፣
ሶስት ሺሕ ዘመናት የገነነ ስምዋን፣ የዋለ በራማ፣
እንዴት? በሸለፈት፣ በእንክርዳድ ፍሬዎች አንጡራ ታሪኳ፣ ነጭ ስምዋ ይቀማ።
እምነት በራዥ ጳጳስ፣ ሃገር አጥፊ መሪ፣
የአምበጣ ግሪሳ በሰብል ሰፋሪ፣
ዓላማ የሌለው ጭፍን አስተማሪ፣
አራቱ አንድ ናቸው፤ በጅምላ ጨራሾች ሃገርን ቀባሪ።
እረ ጉድ በል ሃገር፤ እረ ወገን ስማ፣
ብቸኛዋን ወደብ የእምነትዋን ባድማ፣
በጎሳ፣ በቀለም፣ በወንዝና ቀዬ፣
በእምነትና፣ ቋንቋ፣ በባህል በዘዬ፣
እየከፋፈሉ፣ እየሸነሸኑ፣ እንደ ቄራ ስጋ፣
መሬት ሽያጭ ሆኖአል ዶላርን ፍለጋ፣
ነባር ሃገሬውን እየጨፈጨፉ አድፍጦ በ አደጋ።
የስኳሩ ቦታ ይመስክር ዋልድባ፣
ይናገር ዳውሮ፤ ጀግና፣ ጀግናው ወጣት ወዴት እንደገባ።
እረ ጉድ በል ሃገር፤ እረ ወገን ስማ፣
ብቸኛዋን ወደብ የእምነትዋን ባድማ፣
የሶስት ሺሕ ዘመን የነጻነት ዓርማ፣
የደም፣ የአጥንት ክፋይ፣ የብስራት ከተማ፣
የአፍሪካ ነጻነት፣ የአድዋ ድል ዜማ፣
እንዴት? በሸለፈት፣ በእንክርዳድ ፍሬዎች፣ አንጡራ ታሪኳ ነጭ ስምዋ ይቀማ።
ስለዚሕ፤
እምነት በራዥ ጳጳስ፣ ሃገር አጥፊ መሪ፣
የአምበጣ ግሪሳ በሰብል ሰፋሪ፣
ዓላማ የሌለው ጭፍን አስተማሪ፣
አራቱ አንድ ናቸው፤ በጅምላ ጨራሾች ሃገርን ቀባሪ።
እናም፤
መዥገርን ስትነቅሉ ከራሱ ተቆርጦ ገላ ውስጥ ከቀረ፣
ማመርቀዙ አይቀርም በዋለ ባደረ፣
መጋዝ መሳይ ጥርሱ ስጋ ውስጥ ስላለ ስለተቀበረ።
ጎዶሊያስ!
02/06/2013