ቸሩ ላቀው
ወዳጆችሽ ናቸው ወይስ ጠላቶችሽ
ሁልጊዜ ወደኛ ነይ ብለው የሚጠሩሽ
ምን ይሆን ምክንያቱ እንዲህ የተጨነቁት
ዙሪያሽን ከበው በገመድ የሚያንቁት።


ወራሪዎችሽ ተነስተው ዘርግተው ወጥመድ
ከጎረቤት የጀመሩት ከጨካኙ ጓድ
በየመኑ ተወላጅ በግራኝ አሕመድ
በውጭ ወራሪው በፊታውራሪው ክንድ
ብዙ ጥፋት ደርሷል በሁሉም ረገድ።


ፖርቱጋሎችም ሞክረው ለማስካድ ሃይማኖት
የሕዝቡን ጥንካሬ ሳይከቱት ከግምት
ልል ሕዝብ መስሏቸው የሚታለልለት
ይኸማ እንዴት ሆኖ የሌለ በኛ እምነት
ብሎ ተሰባስቦ ባሰማው ጩኸት
አፍረው ተመለሱ ተከናንበው ሐፍረት።

ግብፆችም ተነስተው ጉልበት ተሰምቷቸው
ሀገር ለመውሰድ ሊወጉን መጥተው
ሳይሳካ ቀርቶ ያቀዱት ያን ጊዜ
ተዋርደው ተመለሱ ካንድም ሁለት ጊዜ፣
ሀገሬን አላስነካም ብለው ዮሐንስ
አከናንቧቸው የውርደት መልስ
እርም ብለው ሔዱ ዳግም ላለመመለስ።

ጣሊያንም ፎክሮ ለመያዝ ሀገር
ጦሩን ይዞ መጥቶ ከሮማ ምድር
በንቀት አይቶ የኢትዮጵያን ሠራዊት
እንዋጋ ብሎ የሚያሸንፍ መስሎት
አዬ አለማወቅ አለመገመት
ተሸንፎ ወጣ ተከናንቦ ውርደት።

እንግሊዝም መጥታ በሰላም አስከባሪ
ግን ከተልዕኮዋ ወጥታ ሆና ተባባሪ
ሕዝቡን ለማጣላት ለመገንጠል ሀገር
ሥልጠናም ሰጥታ እንዲታይ በተግባር
አስተሳስራ ነበር እንዲሆን የከፋ
ሳይሳካ ሲቀር መና ሆኖ ተስፋ
መርዟን ቀብራ ሔደች ሀብታችንን ዘርፋ።

የዓረብ ሀገሮች ከበው በዙሪያሽ
ከጥንትም ጀምሮ ሊቀራመቱሽ
አስበው ሞክረው ሳይሳካ ሲቀር
የኛኑ አሰልጥነው ላኩብሽ በቀትር
ገንጣይ አስገንጣዮች ሁለቱ ቡድኖች
ሻዕቢያ ወያኔ ቀንደኛ ሰልጣኞች

በተሰጣቸው ተልዕኮ ተግባራቸውን አጠናክረው
ማንነትሽን ለማጥፋት ምለው ተማምለው
ለውጭ ባንዳ አድረው ልጅነታቸውን ክደው
ብትንትንሽን ለማውጣት ሁልጊዜ ተጠምደው
ቀጠሉ መፍጨርጨር እስከ ወዲያኛቸው
ማጥፋት ወይም ሞት ብለው ፎክረው
አብልተሽ አጠጥተሽ ተንካባክክበሽ አሳድገሽ
ምንም የማትበድይ ሆደ-ሰፊ እናት ነሽ።

ግና ምን ይሆናል እነዚህ አፈንጋጮች
የጥፋት አራማጆች የእናት ጡት ነካሾች
ልጆችሽን ፈጁት በጦር በቆንጨራ
እህልም በመከልከል ሆዳቸው የማይራራ
አንችንም ደፍረው ከውርደት ላይ ጥለው
ልጆችሽን አባረው እንደ ከብትም ሽጠው
ቆራርሰው ቆራርሰው ምድርሽን ሰጥተው
ምድረ በዳ አድርገው ሀብትሽን አስወስደው
የት ይሆን መጨረሻው የጥፋት መቆሚያው።

አሁንማ ተጠራርተው ከየማዕዘናቱ
አዳዲስ ዘራፊዎች ከየዓለማቱ
አሜሪካ እንግሊዝ ከናዳና ስፔን
ቱርክና ቻይና ሕንድና የመን
ሳዑዲ ዓረቢያ ኳታርና ጀርመን
ማሌዢያ እንዲሁም ኖርዌይና ስዊድን
ባፍ ጢሙ እንዲደፋው የያዘው ጥጋብ
ቁንጣኑ እንዲባባስ አዕምሮው እንዲደድብ
ገቡ ለወያኔ ገንዘብ ለማስረከብ።

ሳስብሽ እውላለሁ
ሳስብሽ አድራለሁ
ስጨነቅ ስጠበብ ሁልጊዜም አለሁ
የምጠይቀው አጥቼ ግራ ተጋብቶኛል
ኧረ ለመሆኑ አንችን ማን ይሉሻል።

 


ቸሩ ነኝ፣ ቸር ይግጠመን!

ቸሩ ላቀው

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ