ጎዶሊያስ
የትላትል ወራት፣ የተምች፣ የኩብኩባ፣
የምስጥ፣ የጉንዳኑ፣ የቁንቋን ደረመን በቤት ውስጥ ሲረባ፣
በአልጋ በመኝታ፣ በልብስ፣ በገላችን በመላ ሲገባ፣
እንቅልፍን መመኘት ለሙሉ ጤንነት፣
ሰላም ወጥቶ መግባት፣ ለሕይወት ተግባሮች ደፋ ቀና ማለት፣
ትዳር፣ ሕጻናትን፣ ኑሮን በአቋም መምራት፣


ሰላም ውሎ ማደር፣ መስራትና መማር፣
ከቶ አይታሰብም፤ ስቃይ ነው መከራ በእግረ ሙቅ መታሰር።
ተስቦ በሽታ በአገር፣ በሰፈሩ፣ በቀዬው ከገባ፣
ጣጣቴ፣ ኩፍኙ፤ የጂራፍ ገረፋው፣ አታሞ ድብደባ፣
ስቃይ ነው መከራ፤ እንደየሰፈሩ ባሕልና እቀባ።
ግና አሁን፣
ተመስገን፣
መዓቱ የራቀ፣ ምሕረቱ የበዛ፣
ፈጣሪ ይመስገን፤ ኩብኩባና ተምቹ ብዙም አይታይም በማሳ ሲነዛ።
ያ! ቀጣና ዘመን፤ ያ! የወራት ክፉ፣
የተምች የኩብኩባው፣ የተስቦው ሲያልፉ፣
ዘመን ያመጣቸው፤ ከተምች፣ ከኩብኩባው የባሰ የከፉ፣
ለየት ያለ "ቁንቋን" በመላ አገሪቱ ወያኔ ረገፉ።
እንደ ገብረ ጉንዳን፣
ሃገሩን፣ ሰፈሩን፣ ወንዙንና ዱሩን፣
በመላ ቆጥቁጠው፣
በዘር፣ በሀይማኖት፣ በጎሳ ለይተው፣
ድሃው ማንቁርት ላይ የዓሳ እሾሕ ሰክተው፣
ዋይ! ዋይ! ያሰኙታል እንቅልፍ ሰላም ነስተው።
በዶሮ ገላ ላይ የሰፈረ ቁንቋን፣
በእርቃን ሰውነት ላይ የተጋባ ትሗን፣
የወያኔ አገዛዝ፤ ሶስቱም አንድ ናቸው፣
ሲሹ ደም ምጥመጣ፣ አልያም ማሳበድ፣ የግል ተልእኳቸው።
ኑሮ ያሳበደው፣ የቀን-ግፍ ሳያንሰው፣
በቆሰለ ሕይወት፣ የእምነትን በርበሬ መጋት በየአፍንጫው፣
ከበደልም በደል፣ ከግፍም ንጹሕ ግፍ ታሪክ የማይሽረው።
ሰማኒያ፣ ዘጠና፣ መቶ ዓመት ብትገዙም፣
ሙታን ባያያችሁ፤ ዘመናት ቢረዝሙም፣
የደም ጣቶቻችሁ አሻራዎች ናቸው፤ ቀልመዋል አይለቁም።
አንድ ነች ኢትዮጵያ፤ ከጥንትም ጀምሮ፣
ድካም ነው ትርፋችሁ፤ ድሃ ከቆረጠ፣ ድምጥማጥ ያጠፋል አይቀርም ተቀብሮ።
ትናንት በሙስሊሙ፤ ዛሬ በኦርቶዶስ፣
መርዛችሁ ቢረጭም የዲያብሎስ መንፈስ፣
እኛ ግን ጽኑ ነን፤ ዘመን የማይሽረን፤ በኢየሱስ ክርስቶስ።


ጎዶሊያስ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ