ኤፍሬም እሸቴ
ምን ያደርጓቸዋል ውስጥና ውጪ ባይመሳሰሉ
እኩይ ውሳጦች በሠናይ ውጪ ቢከለሉ?
በቀሚስ ጃኖ ሥር ድብቆሽ፣
በጥምጥም በቆብ ምሽጎሽ፣
የሰማዩን ምሥጢር ስርቆሽ።


መንቆለጳጰሱ
መሽኮርመም መኩነስነሱ፣
ከገነት ደጃፍ ላያደርስ፣
የጋኔሉን ቅጥር ላይጥስ፣
አንዲት ሌሊት ለማደር ዕድሜ ለመግፋት ብቻ፣
ከርስን ሞልቶ ለማንጋቱ ለማይጠረቃው ስልቻ።

ለሽቶው መደፋት አዝነን
ባለሽቶዋን ተጸይፈን
የይሁዳን ከረጢት ዘርፈን
አንድ ዲናር ካላቱ የሌላትን ዲናር ሰርቀን
ከአልጋ አጎበር ወድቀን
ሆድ አንጀት አስቀርድደን
አንገት ለገመድ ሰጥተን
ኃጢአታችን ላይታጠብ ዕዳ በደላችን ላይጸዳ
አደራ በልቶ መገኘቱ
ለሥጋ ነው ለነፍሲቱ?


ኤፍሬም እሸቴ
ጥቅምት 9/1993 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ