አገርና እንጀራ (ደመቀ ከበደ-ዓባይ ዳር) [ሊነበብ የሚገባ ምርጥ ቅኔ!]) አገርና እንጀራ / መቶ ሲደመር አንድ/ /ደመቀ ከበደ - ዓባይ ዳር/ ይቺ አገር - የኛ አገር አንዴ ´ምትቦካ - አንዴ ´ምትጋገር፤ ሲሻ ´ምትወድቅ - ሲሻ ´ምትሻገር አንዴ ባንተ ነበር - አንዴም በኛ ነበር፤ አገር እንደ ተረት - ‹‹ተረት›› ከተባለ ተረት ነው አገርህ - በል ተርት ምናለ፤ አገር እንቆቅልሽ - ይሁን ከተባለ ‹‹እንቆቅልሽ አገር›› - ይኸውልህ አለ፤ አገር እንደ ፈሊጥ - ምሳሌ ከሆነ ከኛዋ አገር በላይ - ምንም ‹‹ፈሊጥ›› የለ፤ አንዱ ‹ሲተርታት› - እሳት ዳር ቁጭ ብሎ አንዱ ይሰማዋል - ‹‹የመሰረት›› ብሎ፤ ሌላው ‹እንቆቅልሽ› - ሲያደርጋት ጨክኖ ‹ምን አውቅልህ?› ይላል - ያኛው ከጎን ሁኖ፤ ቀሪው እንደ ‹ፈሊጥ› - ቃል ሲያሳምርባት ይኸ በምሳሌው - አለ ሲስቅባት፡፡ ይቺ አገር - የኔ አገር ይቺ አገር - የአንተ አገር ይቺ አገር - የአንቺ አገር ይቺ አገር - የኛ አገር / የሁላችን አገር / አንዴ ስትቦካ - አንዴ ስትጋገር፤ በአቡኪና ጋጋሪ - ልኳ እየተለካ ቀድሞ ባልተፈጨ - ሊጧ እየተቦካ አለች እስከዛሬ - ሳትመር ሳትጥም መጋገሪያው ምጣድ - ከሙግዱ ሳይገጥም፡፡ ለዚያም ነው የዚያኛውን አቡኪ - ይኸ እየጋገረው ያ የጋገረውን - አንዱ እየሰበረው በሰባራ ምጣድ - እንደ እንኩሮ እንጀራ በመጣ፤ በሄደ - አገሬ ተጋግራ ይህንን እንጀራ የመጣ ጋጋሪ - ወይም ባለተራ ለባለ አገር ሁላ - ቢያበላ፣ ቢያበላ ጠኔ አላጠገገም - ራብም አልከላ! ምክንያት፤ የአያቶቹን ምጣድ - አባት እየሰበረ የአባቶቹን ምጣድ - ልጅ እየቀየረ አገር እያቦካ - ቀዬ እየጋገረ እልፍኝ እያበጀ - ከልካይ እያኖረ አብሲቱን ህዝብ ግን - ይረሳው ነበረ፤ እና እንዲህ እላለሁ፤ ማነህ ባለተራ? ምጣድ ያዘጋጀህ - ለእንጀራ ጋገራ?! እሳት ዳር ቁጭ ብሎ - ፍሙን እየሞቀ ከትላንት ጥጥ ላይ - የታሪክ ባዘቶ - እየፈለቀቀ እያጠነጠነ - ሸማ እያጠለቀ ህዝብ ይኑርልኝ ካልክ - እየፈነደቀ በሰባራ ምጣድ - ሊጥ አታነካካ ባለፈው ጋጋሪም - ሙያህን አትለካ ይልቅ የእልፍኙን ሰው - ሌማቱ እንዲያረካ በአገር ልክ ጋግር - ከህዝብ ጋር አቡካ!! ቀዳሚው ቀጣዩ Tweet