እሱማ አለ! ይኖራልም ገና! (ጌታቸው አበራ)
ዘምባባውን ታቅፎ -እጁን ለሰላም ሊዘረጋ፣
ከጽንፍ-አጽናፍ እየበረረ - የደረሰውን አንተጋ፤
ባገር ባህል ክብር - የእንግዳ አቀባበል ወግ፣
በፈካ አበባ እቅፍ - በቄጠማ ጉዝጓዝ በማዕረግ፣
ልትቀበለው ሲገባ - ፊትህን አዙረህበት፣
እንደከብት ያጎርከው - ከማይጠረቃው ወህኒህ በረት፤
ደግሞም ይባስ ብለህ - ድንበር በሌለው ጭካኔህ፣
ከጓዶቹ..ከቤተሰቡ - 'ለዝንተ-ዓለም' ነጥለህ፣
በስልጣን፣ በብረት..በመታበይ - የግፍ ግፍ የፈጸምክበት ...፣
ለምን ነበር? ተጠየቅ? እንዲያ ኖረህ ላትኖርበት!
አንተ ነህ እንጂ አፈር - በምስጥ የተነከትከው፣
የሰበሰብከውን ሳትበላ - እንደበተንክ የተበተንከው፤
እሱማ አለ!
ልቡ እንደደነደነ፣
ለሕዝብ እንደወገነ፣
ላገሩ እንደታመነ፣
በሕዝብ እንደጀገነ፤
ሞራሉ እንደተጠበቀ፣
ከጠላቶቹ እንደላቀ፣
ሃቁን እንዳነገበ፣
እንዳበራ እንዳበበ፣
እሱማ አለ!
"ሙት ወቃሽ አያርገኝ" ይላል - አበሻ በልማድ ታስሮ፣
እኔስ አልተውህም - እንዳዲስ ሁሌም አንጀቴ አሮ፤
ለስምህማ ብትጨነቅ - የታሪክ ወቀሳን ብትፈራ፣
ትታቀብ ነበር ከእኩይ ድርጊት - ባገር በሕዝብ ላይ ግፍ ላትሰራ፤
ታሪክ የሌለህ ሸፍጠኛ፣ ያገር የሕዝብ ደመኛ፣
ከተኛህበት አፈር፣ ዘር-ማንዘርህ ይፈር፤
እንጂ እሱማ..
ንጹህ ታሪኩን እየተረከ፣
ካንተ በላይ ገዝፎ እውነታን እየሰበከ፣
ላገር ለወገኑ ለቤተሰቡ ኩራት፣
ዘብ ቆሟል በህይወት!
"እኔ" እላለሁ፤ እሱም ባይል፣
ለሰራኸው ግፍ በደል፣
ይድረስህ ብድራቱ፣
አፈር አይቅለልህ - ትክበድብህ ምድሪቱ፣ ነፍስህም
አትማር - "ምህረት" አይገባትም ከቶ፣ ታሪክም
ሲወቅስህ ይኑር - ሰፊ ብራናውን ዘርግቶ ...፤
(ቁስልስ በጊዜ ሂደት ይድናል፤
የስሜትን ስብራት በምን ይታከሟል?!
(ከአሳዛኙ ትረካው - በእጅግ የሚሰቅቀው ...)
የልጁ ሠርግ ላይ ሊገኝ - ዓለሙን ሊያይ ጓጉቶ፣
ጊዜው እንዳይባክንበት - "ከዚያው" ሊሄድ ተሰናድቶ፣
ጸጉሩን እንኳን ሳይስተካከል - ወረፋ እየጠበቀ፣
ባንተ ሰይጣን መልዕክተኞች - ዳግም ነጻነቱን ተነጠቀ፤
በናፍቆት ሲጠብቀው የነበር - ስንቱስ የቤተሰብ አባል ተሳቀቀ!
ይብላኝልህ ላንተ እንጂ - የልጆችህን ሠርግ ለማታየው፣
እሱስ ዕድሜና ጤና ሰጥቶት - የልጅ-ልጆቹን ሠርግ ሊያይ ነው!
ተንጨርጨር ካፈርህ ሆነህ - ልንገርህ ታላቅ መርዶ!
ሳታየው አመለጠህ - በላይህ ላይ ተረማምዶ፤
ሸርና ክፋት ስታጠነጥን፣
ከዳር ሳይደርስ ያሰብከው "ውጥን"፣
በቅጡ ሽበት እንኳን ሳታወጣ፣
ከምድረ-ገጽ መፋቅ ሆነ ያንተ ዕጣ!
እሱ ግን አለ!
እምነቱን እንዳዘለ
ለአዛውንት ወግ በቅቶ
አንቱ እየተባለ!
እሱማ አለ።
ጌታቸው አበራ
ታህሣሥ 2006 ዓ.ም. (ዲሴምበር 2013)
ከብዙ ዓመታት የወያኔ ወህኒ ቤት የግፍ እስር በኋላ፣ በቅርቡ በኢሳት ራዲዮንና ቴሌቪዢን ላይ፣ ሲሳይ አጌና ቃለ-መጠይቅ ያደረገላቸው አቶ አበራ የማነአብ በሰጡት ቃል ላይ በመመርኮዝ የተጫረች ግጥም ናት።
አቶ አበራ ከጓዶቻቸው ተለይተው በታሰሩበት ወቅት አካባቢ በድርጊቱ በመቆጨትና በማዘን "ፍትህን ፍለጋ" የምትል ግጥም በ1989 ዓ.ም. ጽፌ የነበረ ሲሆን፣ ወደ በኋላው በ2003 ዓ.ም. መስከረም ወር ላይ በኢትዮጵያውያን ድረ-ገጾች ላይ ተሰራጭታ ነበር። (ከዚያን ጊዜው በላይ በቁጭትና በሃዘን ስሜት የሚያሰምጥ ሁኔታ ዳግም ተከሰተና ...)
ሰሞኑን ደግሞ፣ ብርቱ አገራዊ ጉዳዮችን ፈልፍሎ በማቅረብ በታወቀውና በማደንቀው ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ጠያቂነት በኢሳት የተሰራጨውን የአቶ አበራን ቃለ-መጠይቅ ከሰማሁና በጣም በማደንቀው ጋዜጠኛ፣ ደራሲና ገጣሚ አበራ ለማ የቀረበውን አሳዛኝ ተራኪ ጽሑፍ ካነበብኩኝ በኋላ፣ እምባ ባቀረሩ ዐይኖቼና በተረበሸ አእምሮዬ አስገዳጅነት ይህቺን ግጥም ጭሬ እኔ ጥቂት እፎይ ብያለሁ። ስሜቴን የምትጋሩ፣ ለቃላቱ "ክብደት" ይቅርታ እንደምታደርጉልኝ አምናለሁ። በዚህ አጋጣሚ ለብርቱው ሰው ለጋሼ አበራ የማነአብ፣ ለውድ ቤተሰቡ፣ ለጓዶቹና ለሰላምና ፍትህ ፈላጊ ኢትዮጵያውያን ሁሉ እንኳን ደስ አለን እላለሁ።



