ዳዊት መላኩ
ከመቃብር ምሶ፣
ሙታንን ቀስቅሶ፣
ዘር አጥንት ቆጥሮ ከሰውነት ወጥቶ
እንደራበው ውሻ አጥንት እየጋጠ፣
በስንቱ ቀለደ በስንቱ አላገጠ።


ዛሬን እንዳንቃኝ እንዳናልም ነገን፣
ሁል ጊዜ በፍርሀት እያሸማቀቀን፣
ሽብረተኛ እያለ ሽብር ሲዘራብን፣
እኛም ሚስኪን ህዝቦች እንቀበላለን።


በጥላቻ ወሬ እግር ከወርች ታስረን፣
እንዳንከባበር በትዕቢት ተውጠን፣
አንዱ አንዱን ላይሰማው ስንደነቁዋቆር
ሁሉም በያለበት እየየውን ሲያወርድ፣
የተጫነብንን መርገም እንደማውረድ፣
አንድ መቶ ዓመታት የሁዋሊት ተጉዘን፣
ከሙታን መንፈስ ጋር እንፋለማለን።


ሀገርን ባቀና ክብርን ባስመለሰ፣
የምኒልክ ሐውልት ይላል ካልፈረሰ።
ወያኔ የሚባል የባንዳ ስብሰብ፣
ከከርሱ ውጪ ምንም የማያስብ፣
መርዝ እንደቀመመ ተንኮል እንዳደራ፣
በጅምላ እንዳሰረ ካገር እንዳስወጣ፣
ሌላ ማዘናጊያ አኖሌ 'ሚል መጣ።


ስንት ሰዎች አለን ግራ የተጋባን፣
የሰጡንን ስራ ሰርተን ያልጨረስን።
አንዴ አብዮታዊ ሲለው ልማታዊ፣
ፌደራልም አልከው ወይም ክልላዊ፣
በቃላት ጋጋታ ህዝብን እያምታታ
መልክ እና ጸባዩን እየለዋወጠ
ሥልጣን ኮርቻ ላይ ከተቆናጠጠ
ዘመናት ነጎዱ
ስንት ኹነት ሄደ ስንት ኹነት መጣ
ወገኔ ከችርግ ከዋይታ ሳይወጣ።


አንዱዓለም፣ ውብሸት፣
በቀለ እና ርዮት
በሰላሙ መንገድ ህዝብን የሰበኩት
ነጻነትን ሲሹ ፍትህ የተጠሙት
ላገሩ በጮኸ ለፍትህ በጻፈ፣
እስክንድር ታሰረ ብዕሩ ነጠፈ።


ሀገር እየሸጡ ሀብት እየዘረፉ፣
በጅምላ እያረዱ ዘርን እያጠፉ፣
የጌቶቹ ልጆች ጮማ እየቆረጡ፣
ስንቶች ማደሪያ አጥተው ከቤታቸው ወጡ።


እምዬ ንገሪኝ ምንድን ነው መርገምሽ፣
አልወጣልሽ ያለው መከራ ከቤትሽ።
ኀዘን ኀዘን ወልዶ ልቤን እየነካው፣
የትናንቱ ቁስል ሳይጠፋ ጠባሳው፣
ወደብ አልባ መሆን እያንገበገበኝ፣
ዛሬ ይባስ ብሎ ድጋሚ አስደፈረኝ።


ከእንግዲህ ይበቃል ምን ሊመጣ ሌላ፣
ዘር ቀለምን ሳልለይ ወይም እምነት ጎራ
አብሬ ልሰለፍ ከነአንዱዓለም ጋራ፣
እንደሰው ልቆጠር እኔም ታሪክ ልስራ።



ዳዊት መላኩ (ከጀርመን)
ፌብሩዋሪ 2014

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ