በድን (ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ)
ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ
ፊት ለፊትህ ሰው ጠኔ ይዞት
በቁንጣን እያገሳህ ልብህ ቢደነድን፣
ለተራበው አዝነህ ባትመግበው
አንተ የኖርክ ቢመስልህም ነህ በድን።
አንተ ቪላ ውስጥ ተንሰራፍተህ
ወገንህ መንገድ ላይ ወድቆ ልብህ ቢደነድን፣
በሰብዓዊ ርህራሄ አዝንህለት ባታስጠጋው፣
አንተ ያለህ ቢመስልህም፣ የለህም ነህ በድን።
ህልቆመሳፍርቱ አለአግባብ ሲታሰር፣ ሲገደል፣
ጉዳዬ አይደለም፣ ብለህ ልብህ ቢደንድን፣
እስራት፣ ግድያውን ያለፍርሃት ባትቃወም፣
ያልሞትክ ቢመስልህም፣ ሞተህ ሆነሃል በድን።
አቅመኛ ደካማውን ሲዘርፈው
እኔ ምንግዴ ብለህ ልብህን ብታደነድን፣
አንት በሕይወት ያለህ ቢመስልህም፣
ከድንጋይ የባስክ ሆነሃል በድን።
አበሳና ሮሮ በዝተው ጠፈር ነክተው
አይመለከተኝም ብለህ ልብህን ብታደነድን፣
አንተ የቆምክ ቢምስልህም፣
ወኔህን ተሰልበህ ሆነሃል በድን።
ፍትህና ርት ሲጎሉና ጭቆና ሲገን፣
ምን ቸገረኝ ብለህ ልብህ ቢደነድን፣
አንተ ነፍስ ያለህ ቢመስልህም፣
ነፍስ የለህም ሆነሃል በድን።
ወገኖችህ ሲዋረዱ፣ ሲደፈሩ፣ ሬሳቸው ባደባባይ
ሲጎተት፣ አያገባኝም ብለህ ልብህ ቢደነድን፣
አንተ እስትንፋስ አለኝ ብትልም፣
ደርቀሃል አንደ እንጨት፣ ሆነሃል በድን።
አገርህ በእብሪተኞች እየተገዘገዘች፣
እየጎረፋት የደም አበላ ልብህ ቢደነድን፣
አንተ እንቀሳቀሳለሁ ብትልም፣
የቁም-ሙት ነህ ሆነሃል በድን።
ህዝብህ ብሶቱን እንዳይገልጽ አፉን ተለጉሞ፣
ጉዳዩ ነው፣ ብለህ ልብህ ቢደነድን፣
እመነኝ ፍጹም የለህም በሕይወት፣
እሬሳህ ነው የሚላወስ፣ ሆነሃል በድን።
የትውልድህ ስፍራ እስር ቤት ሆና፣ ያገርህ ልጆች
እስር ቤት ሲማቅቁ ልብህ ቢደነድን፣
መቃብር ውስጥ ነው ያለኽው፣
አጽምህ ረግፎ ሆነሃል በድን።
ቅርስህ፣ ኃይማኖትህና ታሪክህ እየወደመ
ቅርስህን፣ ኃይማኖትህን፣ ታሪክህን ባታድን፣
የምድርህ ደብዛ ሲጠፋ ልብህን ብታደነድን፣
አልሞትኩም ብለህ አትዋሽ፣
ተዘርረህ ሆነሃል በድን።
ካብራኩ የወጣኸው ሰውህ ድረስልኝ እያለ፣
የቁምስቅሉን ሲያይ ልብህ ቢደነድን፣
ካንተ ይልቅ ሽል ሆኖ የቀረው ይሻላል፣
መንፈስ፣ አካልህ ደንዞ ነህ በድን።
ሰቆቃ፣ ዋይታ፣ እሪታ ምስኪኖቹ ላይ ተንሰራፍቶ፣
እምባና ደማቸውን ተራምደህ ልብህን ብታደነድን፣
እኔ እስካልተነካሁ ምን ዶሎኝ ብትል፣
ባትቆጣ፣ ባታምጽ፣ ለወገንህ ባትሆን መድን፣
አሁንስ በዛ! አሻፈረኝ! ባትል፣
ካንተ ይብስ የሞተ፣ የለም ካንት ይብስ በድን።
ሌላው ቢቀር ሽንጥህን ገትረህ፣ ለውነትና
ለፍትህ ሳትቆም፣ ልብህን ብታደነድን፣
ከራስ በላይ ንፋስ ብትል፣
ፍጹም ባይሰጥህ ግድን፣
ከመሬት በታች ድሮ በስብሰሃል፣
ህያው የሆንክ ቢመስልህም ነህ የበድን በድን።
ደሞም እወቀው፣ በደልንና ግፍን ለማድረግ
በቀጥታ ባትሳተፍም፣ በጅ አዙር በደልን እንደምትደግፍ፣
ዝም ብለህ ግድ ሳይልህ በማየትህ ብቻ፣
ግብረአበር እንደሆንክ ከግፈኞችና ግፍ።
ሰኔ ፳ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. (June 27, 2015)
ፕሮፌሠር ፍቅሬ ቶሎሳ፣ በlulu.com እና Amazon.com ላይ በገበያ የዋለው፣ የHidden and Untold History of The Jewish People and Ethiopians ደራሲ ነው። Heaven To Eden የተሰኘው ተራኪ፣ ፍልስፍናዊና ግጥማዊ ተውኔቱ በቅርቡ ለዓለም አንባብያን ይቀርባል። አስተያየት በThis email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ይቀበላል።



