(ወለላዬ ከስዊድን)

(ሙሉውን ግጥም በፒ.ዲ.ኤፍ. አስነብበኝ!)

ዳሪ

ወዳጄ እንደምነህ - ውዱ ጎረቤቴ

ባለህበት ቦታ - ይድረስህ መልዕክቴ

የልጄ ሠርግና - የሟች ልጅህ ቀብር

አንድ ላይ መሆኑ - ፈጥሮብኛል ችግር

መቼም ይገባሃል - ግልጽ ነው ነገሩ

ብዙ ነው ማዕረጉ - የሠርገኛ ክብሩ

ስለዚህ አደራ - የልጄን ታላቅ ሠርግ

በደስታ በሆታ - እንዳሳልፍ በወግ

በዛ ቀን ተነስተህ - ልጅህን ስትቀብር

ሰዎችን ሰብስበህ - አታብዛ ግርግር

እንደውም ጨርሶ - ከሞት ላታድናት

በሳቅ በደስታ - በ'ልልታ ቅበራት

ለለቅሶኛው ሁሉ - ይኼን ንገርልኝ

ነገ ማታ ድረስ - መልስህን ላክልኝ

**********************

ቀባሪ

ክቡር አስተዳደር - የላኩልኝ መልዕክት

እጅግ አስገራሚ - ድንቅ ነው በእውነት

ታስራ ተገንዛ - ልጅ ልትቀበር

ተሞሸረች አሉኝ - የርስዎ ልትዳር

ለክብርዎ ሲባል - ለርስዎ ወግ ማዕረግ

እንድስቅ አዘዋል - ለቅሶዬን በመንፈግ

እንደዚህ አድርጎ - ቀኑ ከከበደ

በርስዎ አስተዳደር - ታምር ከወረደ

ኀዘንና ደስታ - መውጣቱ መውረዱ

አንድ ስለሆነ - ሁለቱም መንገዱ

መቼም ምን ይደረግ - በእልልታ ልቅበራት

እርስዎም ልጅዎን - በለቅሶ ይዳሯት

ወይም ደስታ ኀዘን - እንዳይቀያየጥ

ስምምነት አ’ርገን - ቤት እንለዋወጥ

እግረ - መንገዱንም - በዚህ - አዲስ መንገድ

መከራን ይቅመሱ - እኔም ደስታ ልልመድ

 


ወለላዬ ከስዊድን (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ