ሀገር ማለት የኔ ልጅ (ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ)
ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ
ሀገር ማለት ልጄ፣ ሀገር ማለት፣
እንዳይመስልሽ የተወለድሽበት ቦታ፣ የተወለድሽበት አፈር፤
እትብትሽ የተቀበረበት፣ ቀድመሽ የተነፈሽው አየር፤
ብቻ እንዳይመስልሽ።
ሀገር ረቂቅ ነው ቃሉ፤
ሀገር ውስብስብ ነው ውሉ።
ሀገር ማለት ልጄ፣
ሀገር ማለት ምስል ነው፣ በህሊና የምታኖሪው፤
ከማማ ማህጸን ከወጣሽበት ቀን ጀምሮ፤
በጠባሽው ጡት፣ ወይም ጡጦ፣
በዳህሽበት ደጃፍ፣ በወደቅሽበት ፈፋ፤
በተማርሽበት ትምህርት ቤት፣
በተሻገርሽው ዥረት፤
በተሳልሽበት ታቦት፣ ወይ በተማፀንሽው ከራማ፤
በእውቀትሽና በሕይወትሽ፣
በእውነትሽና በስሜትሽ፣
የምትቀበይው ምስል ነው፣ በህሊናሽ የምታኖሪው፤
ስትወጅ ሰንደቅ ታደርጊው።
ቢያስጠላሽ የማትቀይሪው።
ሀገር ማለት የኔ ልጅ፣
ሀገር ማለት ቋንቋ ነው በአንደበት አይናገሩት፤
በጆሮ አያዳምጡት፤
አማርኛ ኦሮሞኛ፣ አፋርኛ ቅማንተኛ፤
ጉራግኛ ወይ ትግርኛ፣ ብለው የማይፈርጁት።
የኔ ልጅ፣
አማራውና አፋሩ፣ ኦሮሞው ሲዳማው፣ ጉራጌኛሽን ባይሰማ፤
ያልገባው እንዳይመስልሽ፣ ኀዘን ደስታሽን ያልተጋራ።
የየልቦናችንን ሐቅ፣ ፍንትው አድርጎ እያሳየ፤
ህዝቦችን ከሰንደቃቸው፣ አስተሳስሮ ያቆየ።
ሀገር ቋንቋ ነው ልጄ፣ የሁለንተናሽ መስታወት፤
ሲከፋሽ ትሸሸጊበት፣ ሲደላሽ ትኳኳዪበት።
የኔ ልጅ፣
አያት ቅም አያትሽ፣ ሠላም ሲሆን ከወልቂጤ አድማስ ማዶ ሸቅጦ፣
ሲያቀና ወረቱን፤
ለእኔና ለአንቺ መኖሪያ፣ ሲያቀና ቀዬና ቤቱን፤
ሀገር ጠላት ሲደፍራትም፣ ጦሩን ሰብቆ እየፎከረ፤
ከኦሮሞው ከትግሬው፣ ከአፋሩ ከወላይታው፣ ... ከሁሉም የጦቢያ ልጆች፣
አጥንቱን እየማገረ፤
ሀገር ይሉት መግባቢያ፣ ሰንደቅ ይሉት መለያ፣ ሲያቆይልሽ፤
በጉራግኛ ማትገልጭው፣ በጎጥ የማትገድቢው፣ ስንት አለ ታሪክ መሰለሽ!
እና የእኔ ልጅ፣
ለዚህ ነው ሀገር ይሉት ቋንቋ፣ ላንቺ የሚያስፈልግሽ፤
ከወልቂጤ አድማስ ማዶ፣ ለተሳሰረ ታሪክሽ፤
ከወልቂጤ አድማስ ማዶ፣ ለተወጠነው እድገትሽ።
እና ልብ በይ ልጄ! ሀገር ማለት ቋንቋ ነው፣ ባንደበት አይናገሩት፤
በጆሮ አያዳምጡት።
ከሁሉም በላይ ልጄ፣
ተፈጥሮ ከቸረው በረከት፣ የላቡን ፍሬ የሚበላ፤
ሀገር ማለት ወገን ነው፣ የእኔ የምትይው ከለላ።
ትመኪበት ጥሪት፣ ትደምቂበት ብርሃንሽ፤
የሰብዕናሽ ግማሽ ውል፣ ወገን ነው ማሕተምሽ።
ዜጋው ነው ልጄ ሀገርሽ።
መሬትማ የእኔ ልጅ፣
በእምነትሽና እውቀትሽ፣ ከልለሽ ካላበጀሽው፤
ለእድገትሽ ውጥን ካልሆነ፣ ለተስፋሽ ካልተመገብሽው፤
መሬትማ ባዳ ነው፣ ላለማው የሚለማ፤
ለተስማማው የሚስማማ።
ዥረቱም ግድ የለውም፣ ቦይ ለማሰለት ይፈሳል
ተራራውም ደንቆሮ ነው፣ ለቦረቦረው ይበሳል።
መሬቱ አደለም የኔ ልጅ፣ እድርተኛው ነው ሀገርሽ፤
ስትቸገሪ ታድጎ፣ ስትታመሚ አስታሞ፣ ስትሞቺ አፈር ሚያለብስሽ።
በእጅሽ ያለ ብሩህ ጽጌ፣ ሰው ነው ልጄ ሀገርሽ፤
ወገን ነው ልጄ ሀገርሽ።
እና የኔ ልጅ፣
ሀገር ረቂቅ ነው ቃሉ፤
ሀገር ውስብስብ ነው ውሉ።
ታህሳስ 1999፣ ለልጃችን ኬርዓለም
“ፍካት ናፋቂዎች” መድብል
ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ