ጥቁር ሰው

ለፍጥረታት ንጉሥ ለሰማይ አባቴ
ለልዑል አምላኬ ይድረስህ መልዕክቴ፤
የቃል ኪዳን ምድርህ ያቺ የጥንቲቷ
በቅዱሱ ቃልህ ያለው መሰረቷ
ተናግቶ ተዛብቶ ላልቶ መቀነቷ
ደምታና ተንቃ ተበጥሶ እትብቷ
አለች እንዳልነበር ጠፍቶ ደም ግባቷ።

እጆቿን ወዳንተ የምትዘረጋልህ
ስምህ ያደረባት ያቺ ቅድስት ምድርህ
የጻድቃን ቅዱሳን መኖሪያ የቃልህ
እንዳልሆነች ሆና ፈርሳ ተምሳልህ
ነበር ብቻን ታሪክ ይዛ ቀረችልህ።

ምነው አምላኬ ሆይ? ምነው እግዚአብሔር …?
በቃልህ በስምህ በሕግህ ልትኖር
ባርከህ ቀድሰሀት መርጠሃት አልነበር?
እናም ዛሬን ደምታ አንገቷን ስትደፋ
ሀይ ባይ እንደሌላት ሆናልህ አዳፋ
የነበራት ጠፍቶ እንዳልነበር ስትቀር
ምነው አምላኬ ሆይ? ምነው እግዚአብሔር …?
ተሰልቦ ታሪኳ ታርሰው ገዳማቷ
ተቆርሶ ድንበሯ ሲቆረጥ አንገቷ
ምነው አምላኬ ሆይ? ምነው እግዚአብሔር?
ፊትክን አዞርክባት ይችን ቅድስት ምድር?

ብሔርተኝነት ነግሦ በጥልቁ ተምሶ
ተናግቶ ተዛብቶ የአንድነቷ ምሰሶ
መቀነት ማገሯ ተዛብቶና ፈርሶ
ስትጠፋ እያየሃት ጎጠኝነት ነግሦ
እባጭ በጥባጭ ሆኖ ጫንቃዋን ተጭኗት
እንብርቷ ላይ ቆሞ እንዳሻው ሲያምሳት
ዜጎቿን ለስደት ሲያሻው ለእስራት
ለእንግልት ለስቃይ አልያም ለግርፋት
ከጫካ የመጣ መርዛማ ሥርዓት
እርስ በርስ ሲያባላን ሲያፋጀን እያየክ
ከቶ ለምን ይሆን እስኪ ልጠይቅክ
ፊትህን ወደእኛ ያለመመለስክ።

አድማጭም ጠያቂም የለም ለምን የሚል
ጠያቂ እንኳን ቢኖር ተጠያቂ ጠፍቷል፤
በድፍረት ብንጠይቅ ለምን እንዴት ብንል
ድፍረቱን አግኝተን እርሱን ባንቀበል
ባደግንበት ቀየ ጠፍቷል ውሎ ማደር
እጣችን ፈንታችን ግርፋት መታሰር
ሆኗል የኛ ነገር …

በፈለግነው ቀየ መኖርም መስራቱ
አንተ ትብስ አንተ እንደ ቅድመ አያቱ
እምነት ባህላችን የለም ያ የጥንቱ
በጎጥ በቀበሌ ዘረኝነት ነግሦ
በቋንቋ በቀለም ሁሉም ተተራምሶ
ይሻል የመሰለን ይብስ ገኖ ብሶ
እኔ ከሞትኩ ወዲያ ይሉትን ሆኖብን
ነቅርሳው ሥርዓት መዥገር ተተክሎብን
ተጠፋፍተን ሳናልቅ እርስ በእርስ አባልቶን
ኃይል ሁነን አንተ ፈጥነህ ድረስልን።
የኃያላን ኃያል የንጉሦች ንጉሥ
አስባት እምየን ፊትህንም መልስ
እጅህን ዘርጋላት እንባዋንም አብስ።

ከጥቁር ሰው፤ ጥር 5/2007 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ