ማርእሸት መሸሻ

አዋጅ አዋጅ አዋጅ፣ የደበሎ ቅዳጅ
እንቁጣጣሽ ቀርቷል፤ የለም ዓመት በዓል
መልዕክቱን አስተላልፍ ለዘመድ ለወዳጅ
የእልፈ አዕላፍ ዘመን ወግና ልማዱ
ኢትዮጵያዊነቱ፣ ነባር ታሪክ አምዱ

የፍቅር የሰላም የደግነት ካባ
እዮሃ አበባዬ መስከረም ሲጠባ
በሳቅ በጨዋታ በደስታ ዳንኪራ
ነበር መቀበያው በግል በጋራ
ዛሬ ግን ይክፋችሁ መርዶ አለኝ ወገኔ
እንቁጣጣሽ ቀርቷል፤ ዳመራስ ለምኔ።

በምን ደስ ይበለኝ አሁን ሁሉም ባሰ
የደሃው ወገኔ ስጋው ተቆረሰ
የለጋዋ እህቴ፤ የለጋው ወንድሜ ደማቸው ፈሰሰ
አለቀ ደቀቀ ጨዋታ ፈረሰ።

ለምን ቀረ አትበሉ፤ ኧረ አታጉረምርሙ
አዲስ ዓመት ማለት ምንድን ነው ትርጉሙ?
ሀገር ኀዘን ሞልቷት በዳር በመሃሉ
እንዴት ጥርሴስ ይሳቅ
እንዴትስ ልቦርቅ
እንዴት ፈታ ልበል ላውርድ ዳንኪራ
እንዴት እስክስ ልበል ልፎክር ላቅራራ
ወገን እያለቀ እንዴት ደስ ይበለኝ
እንዴት ጃኖ ልልበስ እንዴት ይመርብኝ
የኦሮሞው የአማራው መርዶ ተጭኖብኝ
እንዴት ስጋ ልብላ እንዴት ጠጅ ልጠጣ
መላ ሰውነቴ ተሞልቶ በቁጣ

አዲስ ዓመት የታል ያው የሰቆቃው ነው
ሌላ ዜና የለም፤ አሁንም ፍጅት ነው
አሁንም ዕልቂት ነው፤ አሁንም ግዞት ነው
እንቁጣጣሽ ይቅር፤ ዳመራው ይታገድ
የነጻነት ችቦ በየቤቱ ይንደድ
ዓመት በዓላችን ይያዝ በቀጠሮ
ወያኔን እስኪጠፋ ከምድረ ገጽ በኖ፣ ወድሞ ተሰባብሮ።


ማርእሸት መሸሻ
ጳጉሜን ፪፻፰ ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ