ትንሣኤ

ተቃርቧል ትንሣኤሽ

ክንፈሚካኤል ገረሱ

የመይሳው ትልሞች የዮሐንስ ግርፎች፣

የአሉላ የባልቻ የገብርዬ እንቡጦች፣

የምዬ ምኒልክ የጣይቱ ደቦል የጣይቱ አንበሶች።

የአብዲሳ አጋ የሞገስ አስገዶም የዑመር ሰመተር፣

የገረሱ ዱኪ የጦና ጎበና የጅማ አባ ጅፋር።

የበላይ ዘለቀ የመንግሥቱ ንዋይ የገርማሜ ንዋይ፣

የነ ዓሊ በርኬ አክሊሉ ሀብተወልድ ያባባ ጃንሆይ።

የአብርሃም ደቦጭ የጃጋማ ኬሎ የነ ዘርዓይ ደረስ፣

የታሪካቸው ፈርጥ የቃል-ኪዳን ልጆች በሥጋ በመንፈስ፣

በየዘመናቱ ያበሩ እንደ እንቁ የታዩ አድማስ ካድማስ።

ባንድነት በፍቅር ጠላት ያዳሸቁ ጠላት ያሳፈሩ፣

ተድላ ፍቅር ደስታ ሰቆቃ ችግርን ሞትን የተጋሩ።

በፍቅራቸው ቀንቶ ቢያደባ ሳጥናኤል ቢሸምቅ ሳጥናኤል፣

ሊነጥል ቢዳክር ሊበትን ቢታትር ገብቶ ከመካከል።

ቢዘራም እንክርዳድ ከስንዴው እርሻ ላይ ቢያዘምር ላመታት፣

በፍጹም አልቻለም ሊያወርዳቸው ከላይ ካንድነት ሰገነት።

የገሞራ ልጆች የነበልባል ልጆች ቄሮዎች ፋኖዎች፣

የነፃነት ቀንዲል ታሪክ ተረካቢ የዘመኑ አርበኞች።

ስንዴና እንክርዳዱ ሲያሸት ሲጎመራ ሲያፈራ ጠብቀው፣

ምርቱን ከእንክርዳዱ ሊለዩ ወስነው ባንድ ተማምለው።

አጨዱት ስንዴውን አሄዱት ካውድማው ከተቱት ጎተራ፣

ሟሸሸ ከሰመ የሳጥናኤል ተንኮል የሳጥናኤል ሴራ።

እንክርዳዱም ቀረ ቆሞ ተገትሮ ከቃርሚያው መካከል፣

ቄሮዎች ፋኖዎች ነጥለው ለይተው አደረጉት ከሰል።

እምዬ ኢትዮጵያ የአናብስት እናት ያምላክ አስራት አገር፣

ልክ እንደ ትላንቱ አንድ ሆኑ ልጆችሽ ተያያዙ በፍቅር።

እናም እማማዬ፤

ተሰምቷል ጸሎትሽ ተቃርቧል ትንሣኤሽ ተዋርዷል ሳጥናኤል፣

በልጆችሽ ጽናት በልጆችሽ ፍቅር ክብርሽ ይመለሳል፣

ይፈካል ያብባል ለዓለም ይታወጃል በዓለም ያስተጋባል።


ክንፈሚካኤል ገረሱ

ታህሳስ ፲፰ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም.

27 Dec. 2017

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ