ለብርቱካንና ቴዲ ክብር ይሁን!

ከትንሣዔ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

ትውልድ የምትረግሙ ትናንትን ክባችሁ፣

ዛሬን የምትንቁ ባምናው ተኩራርታችሁ።

እስቲ ተጠየቁ እናንተ ማን ናችሁ?

 

በቆላ በደጋ በሸንተረር በዱር፣

ደግሞም በከተማው በፀሐዩ በቁር።

በየአደባባዩ በየሰርጣ ሰርጡ፣

እንደ እርግብ የዋህ እንደ አነርም ቁጡ።

ትንታግ የሚወጣው ብዕር ቀለማቸው፣

ገጣሚ ፀሐፍቶች አሉን ብዙ ናቸው።

ዛሬም ትውልድ አለ ኩራት እሚሆነን፣

እስቲ እንደ ቴዎድሮስ እንደ ብርቱ እንሁን!

 

ወጣት የምትጠሉ ትናንትን ክባችሁ፣

ዛሬን የምትንቁ ባምናው ተኩራርታችሁ፤

ከእናንት የተረፈ ችግር በወረሰ፣

ትንሹ ትልቁ ትውልድን ወቀሰ።

እስቲ ተጠየቁ እናንተ ማን ናችሁ?

ምን ተዋችሁለት ምን አወረሳችሁ?

ሴት ነች ደመ ግቡ ሕግም የተማረች፣

አስተዋይ አሳቢ ወጣት አበባም ነች።

ትንሹን ትልቁን ከወንበር ልታስነሳ፣

ትችልም ነበረ አምራ ተኮፍሳ።

ያማረ ቤት ሠርታ ደምቃና ተውባ፣

መኖር ስትችልበት ፈንጥዛና ጠግባ፤

ታጥቃ የተነሳች ፍትህ ላታዛባ፣

አለች አዲስ ትውልድ እሳትም አበባ።

ቃላት አጣጣልዋ የአንደበትዋ ለዛ፣

በፍቅር የሚጥል ቀልብም የሚገዛ።

መላበስ ከፈለግን ነፃነት ኩራትን፣

ታሪክ እስቲ እንሥራ እንደ ብርቱ እንሁን!

 

ሁሉም ወሬ ብቻ ተግባር የለም ከቶ፣

የሚጀምር በዝቶአል የሚጨርስ ጠፍቶ።

የምትሉኝ ሁሉ ወቀሳ አብዝታችሁ፣

አደባባይ ውጡ እናንተን ልያችሁ።

ለወገን ለታሪክ የሚበጅ ለሀገር፣

ሠራን የምትሉት በእናንተ እሚነገር።

ዘርዝሩልኝና መረጃ ያለውን፣

እናንተን ልቀበል ትቼ የሌላውን።

 

አላሳልፍ ያለች ጠላት በመንደሬ

ሕይወትም ከፍላለች ትንሽዋ ሽብሬ

ኦባንግም ወጣት ነው የአኝዋኩ ፍሬ፣

ኢትዮጵያን የሚላት ኩራቴና ክብሬ።

ቡርቴ ፍትህ ስትል ቴዎድሮስም ፍቅር፣

ለሠላም ለአንድነት ሲሟገቱ ለሀገር።

ሲታገሉ እምናይ ከነቀዝ ከምስጡ፣

ትንቅንቅ የያዙ ከእባቡ ከጊንጡ፣

ኑ እንታረቅ ያሉ ዘንባባ እየሰጡ፤

አሉንና ጀግኖች ብልህና አስተዋይ፣

ፈርጠም ያልን በአቋም ሳንሆን ወላዋይ፣

እስቲ ብርቱ እንሁን ብርሀኑን እንድናይ።

 

በየቡና ቤቱ በስብሰባው ሁሉ፣

ውጤት ያለው ሥራ ተግባር የምትሉ፤

የሠራ ነውና የሚያምረው ሲጠይቅ፣

የናንተን አካፍሉኝ ገድላችሁን ልወቅ።

አልተሠራም ሳይሆን ይህን ሠራሁ በሉ፣

ጎድሏል አትበሉኝ እናንት ያንን ሙሉ።

ለማጣጣል ብቻ ከሚሆን ሥራችሁ፣

ይህን ሠራሁ በሉኝ እንድኮራባችሁ።

 

አለኝ ወጣት ትውልድ ሀገር የሚያኮራ፣

ነፃነቴን ብሎ ለነብሱ እማይፈራ።

ሺህ ብርቱካን አሉ መንደሪን ትርንጎ፣

ጠላት የሚጥሉ በጦሩ በሸንጎ።

ሺህ ቴዲዎች አሉን ሼመንደፈር ያሉ፣

በኃይል የማይወድቁ በፍቅር የሚጥሉ።

ሀሜት አሉባልታው ማጣጣሉ ቀርቶ፣

መሥራቱ ይበጃል በአንድነት ተስማምቶ።

ሐቅ ረግጦ ጉዞ ነፃነት አያስገኝ።

እንዲያምነን ህዝቡ እንሁነው ታማኝ፣

መከታ ጋሻቸው አጋራቸው ሆነን፣

እንድንሠራ ገድል ለታሪክ የሚሆን፤

እስቲ እንደነ ቴዲ እንደ ብርቱ እንሁን!

 

ትንሣዔ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)

ታኅሳስ 2001

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ