እኛም ቃል ገብተናል! (ወለላዬ)
እኛም ቃል ገብተናል!
ወለላዬ - This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ከልቧ ላይፋቅ ማንም ላያሽራት፣
ቡርቱካን፧ ቃልሽን ለውጪው አትበሏት።
እውነት ጨብጣ ነው ፊትም አነሳሷ፣
ከቃሏ ጋር አብራ ትሞታለች እሷ።
እንኳን ታክሎበት የሙያ ምግባሯ
በቃል የፀና ነው ወገናዊ ፍቅሯ።
ገና ከጅምሩ መድረኩን ስትረግጥ፣
ብርቱካን ምላለች ቃሏን ላትለውጥ።
የቃል ኪዳን ዕዳ ይዛለች አደራ፣
ላገሯ ነፃነት ልትቆም ልትሠራ።
እልቧ ያለውን ያን ቃሏን ቀምቶ፣
ሊወስደው አይችልም ማንም አስፈራርቶ።
ፍፁም ላያግዳት ላይበግራት እስር፣
ለቃሏ እንደምትሞት ተናግራ እኮ ነበር።
በሐሰት ውንጀላ እናንተው አስራችሁ፣
ሸምግሉን በማለት እናንተው ፈታችሁ፣
ያንን እኩይ ተግባር ያን የሐሰት ወንጀል፣
ከስር መሰረቱን እውነት ለማስመሰል፣
እንደልማዳችሁ ብታስሩ ብትገሉ፣
ስጋ ነው ፈራሹ ሞቶ አይቀርም ትግሉ።
ስለዚህ አትልፉ! ቃል ልታስለውጡ፣
ለሐሰት ቆማችሁ እውነት አትቀላውጡ።
መገኛ ቦታውን ስፍራውን ስታውቁ፣
ከእውነተኛ ሰዎች ሐሰት አጠብቁ።
ምንም ቢኮመጥጥ ባይጥማችሁ ቃሉ፣
እውነትን በሐሰት ለውጡት አትበሉ።
እንኳንስ በእውነት በሐሰት መለከፍ፣
ጸንቶ ባያጸናም ታይቷል ሲያክለፈልፍ።
ከእውነተኛ ዳኛ ያውም ከታጋይ ሴት፣
ልታገኙ አትችሉም ብትፈልጉ ውሸት።
እንዳሁኑ ጊዜ እንዲህ እንደናንተ፣
ለተንኮል ተውልዶ በተንኮል የሞተ፣
የፍጡር ጭቅቅት ጠባየ ጠምዛዛ፣
ወትሮም ከጥንት አሉ ቁጥራቸው ሳይበዛ።
ጊዜ ጊዜን ወልዶ ታሪክም ታሪክን፣
ዘመን እንዳስረዳን የመኖር ምስጢሩን፣
ካዳም ዘመን ወዲህ ዘርፉ ተያይዞ፣
እናንተ ላይ ደርሷል ተጉዞ ተጉዞ።
ነገር ግን እስካሁን በእጅጉም ብትለፉ፣
አትችሉም ካለም ላይ ሐቅን ልታጠፉ።
ብርቱካን ሚደቅሳም ያበራችው ሻማ፣
እንዲሁም የቴዲ የትግል ዓላማ፣
እንኳንስ በመለስ በነግርማ ፊርማ፣
በልዑል ዳኝነት የፍርድ ቁልመማ፣
በማንም የምድር ኃይል አይችልም ሊቀማ።
ስለዚህ ሁላችን በአንድነት ቆመናል፣
እወቁት እንግዲህ እኛም ቃል ገብተናል።
ወለላዬ ከስዊድን This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ታህሳስ 24 ቀን 2001 ዓ.ም. January 02, 2009



