ይቅር በለን ሠይጣን! (አባ ቤክሲሣ)
ይቅር በለን ሠይጣን!
ከአባ ቤክሲሣ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ስብዕናችን ተናጋ
ወሮ-በላ ተባብሮ
ጎጠኝነት ነገሠ
ዳር ድንበራችን ተሰብሮ።
ሞትነው የውሻን ሞት
ፈጣሪ እንደተሳነው
ቀባሪ እንደቸገረው
አሥራት እንደበላ ገበዝ
እርግማን እንደተጫነው።
ያም ሆኖ!
ሁሉን ቻልነው እንደቁጣ
ሊያስተምረን ኃጥያንን ከፈጣሪ እንደመጣ።
ምነው ጌታ!
ላጎደሉት የምትሞላ
ለጨከኑት የምትራራ።
ለግፈኞች ዕድሜ ችረህ
ስቃያችንን አራዝመህ።
በል ተጠየቅ መልስ አለብህ
ለኛ መስሎን ስቅላታህ
ግርፋትህ።
ይባስ ብለህ
በደካሞች መጨከንህ
አንተን ያመኑ የወለዱ
የፆሙም የሰገዱ
ልጆቻቸው በርሳስ ነደው
የርሳስ ዋጋ በደም ከፍለው
ማብቂያ በሌለው ፍዳ በእግረ ሙቅ ተቀፍድደው
አንድየ መባልህንስ ለምን ከግፍ አትቆጥረው?
ካልሆነማ!
ትንሣዔህም ከራቀማ
ባልዋልክበት ባልፈየድከው
መለመንህ ለምንድነው?
ካልታደግከን እንደትውልድ
ጌታ ፍረድ ወይም ውረድ።
ይልቅ ሠይጣን!
ተክህኖህ ፍርደ-ገምድል
የስቅላት ባለሟሉ
የሙስና ሊቀጳጳስ
ሐሰት እብሪት በቀል ገድሉ።
የጣር የመከራ ሥልጡን
ፀረ-ፍቅር ፀረ-አንድነት
የውርደት ሊቀካህን
የእርዛት የምንዝራት።
የትውልድ ውርሰ እርግማን
አንተ የሞት ባለሥልጣን
ሁለት አሥርት ዓመታትን
ያጋደልከን ያፋጀኸን
የሰው ቀደምት እንዳልነበርን ባደባባይ ያዋረድከን
ያስለመንከን
ያላመድከን “ምንተስሟ ለማርያም”ን።
ወይ ነዶ!
ሞትን በሞት እንዳንቀጣው
ቂምን በደም በመበቀል
ፈጣሪያችንን ፈራነው
እሱም በተራው ይቆጣል።
አንተ ምሩቅ! በዘር ማጥፋት ግብርና
ቅስማችንን ሰብረኸው ሞራላችን ነቅዞአልና።
ከዚህ ወዲያስ ይለይለት! ...
ባንተው መጀን ክቡር ሠይጣን!
እባክህን ይቅር በለን!
የወለድነው ባንተ አይውጣ
መለስ ቀለስ አታድርገን።
ከአባ ቤክሲሣ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



