በልጅግ ዓሊ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

የዛሬውን አያድርገውና አዲስ አበባ ትንሽ ከተማ ነበረች። አሁንማ በጣም ሰፍታለች። የህዝቡም ቁጥር ጨምሯል። የሽጉጤ ደሜ ታሪክ ሲፈፀም አሁን ካላት ስፋት ጋር ሲወዳደር የትየለሌ ነው። ከሦስት አስር ዓመታት በፊት አንዱ ሠፈር የተፈፀመው ሌላው ሠፈር ይሰማ ነበር። ዛሬማ ምኑ ቅጡ ብሽቅጥቅጡ እንኳን ሌላ ሠፈር የተሠራው የጎረቤትም መርዶ አይሰማም። አዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙት ሠፈሮች አንዱ ”ልደታ” ነው። ሠፈሩ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች ጥቅጥቅ ብለው የሚኖሩበት ነው። የሠፈሩ ነዋሪ ችግረኝነቱ ሳይበግረው ተፋቅሮ የሚኖር ሲሆን፣ በደስታም ይሁን በኀዘን የማይለያይ ነበር።

 

ይህ አሁን የምተርክላችሁ እውነተኛ ታሪክ የተፈፀመው እዚሁ ልደታ ውስጥ ነው። የልደታ ክልል በውል ተለይቶ አይታወቅም። መንፈሣዊው የልደታ ክልልና ደርጋዊው የቀበሌ ክልል ልዩነታቸው ሰማይና ምድር ያህል ነበር። ከአሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ አንስቶ እስከ ሰንጋተራ፣ ከተክልዬ አንስቶ እስከ ጨርቆስ ሁሉም ልደታ ነው። የዛ ሠፈር ሰዎች እንኳን ክርስቲያኑ ሙስሊሙም ”ልደትዬን” ብሎ ከማለ ውሸት የሚባል አይገኝበትም። የልደታ ልጆች ልደታን እንደ ሁለተኛ እናታቸው ነው የሚቆጥሩዋት። አንዳንዴም ልደትዬን እንዳባት ስም እንጂ እንደ ኃይማኖት መገለጫ ማን ወስዶ?

 

አወይ የልደታ ትዝታ!!! ... ስንቱን ነገር ያስታውሳል እባካችሁ?! ባልቻ ሆስፒታል ሳይክል የተማርንበት ቦታ፣ ዋና ለመማር አቫሲዮኒ መሄድ፣ እግር ኳስ ለመጫወት አሸዋ ሜዳ፣ ጥምቀት ልደታን ማውጣትና ማስገባት፣ የግንቦት ልደታ፣ ተስፋ ኮከብ፣ ባልቻ አባ ነፍሶ፣ ቢሪሞ፣ ቶሎሣ ሰፈር፣ ፍርድ ቤት፣ ማኅበረ ሠላም ዕድር፣ የዕድሩ ለፋፊ ማሙዬ፣ በጠዋት የዕድር ልፈፋው፣ ጡ ጡ ጡ ... የቱልቱላ ጩኸት ... ዕድሩ ምኑ ቅጡ ...

 

”ጡ ጡ ጡ ... የወይዘሮ አትጠገብ አያት ስለሞቱ ቀብሩ ልደታ ውስጥ ስለሚፈፀም የማኅበረ ሠላም ዕድር አባላት በሞላ እንድትገኙ። ስም ይጠራል። የቀረ መቀጮ አለው። ጡ ጡ ጡ ...”

 

ማን እንደ ሞተ ለማወቅ ከእንቅልፍ ተነስቶ ወደ ውጭ መሮጥ፣

 

”አባባ ማሙዬ ማን ሞተ ያሉት?”

 

”እዚህ ቢሪሞ ወፍጮው ጋ ያሉት ሴትዮ። የታወቁ ናቸው። ሁለት ጎረምሳ ልጆች ያሏቸው። ለእሜቴ ንገሩ! እናንተ አታውቋቸውም። ለጌቶችም እንዳትረሱ ንገሩ!! ... ጡ ጡ ጡ! ...”

 

የዕድር ለፋፊው የማሙዬ ድምፅ የሚረሳ አይደለም። የዕደር ብርጭቆ ልንወስድ ተልከን ስንሄድ የአባባ ማሙዬ አቆጣጠር የሚያስቀን አይረሳም ”... አስራ ሰባት ... አስራ ስምንት ... አስራ ዘጠኝ ... አስራ አስር (ካያ) ...” ልደታ የአባታችንን የአባባ ማሙዬን ነፍስ ትጠብቅልን። ትዝታው ወዴት ወሰደኝ እባካችሁ። ልደታ ውስጥ ጽፈው የማይጨርሱት፣ ተናግረውት የማያልቅ ስንት ታሪክ አለ።

 

ከሁሉም ትዝ የሚለኝ የሽጉጤ ደሜ ታሪክ ነው። ከቀይ ሽብር በኋላ ሁላችንም በፍርሃት የምንኖርበት፤ በተለይ ልደታ ቤተ ክርስቲያን ደጃፍ ላይ ተገለው የተጣሉት ወጣቶች ግፍ በልደታ ነዋሪዎች ውስጥ ትልቅ ኀዘን ትቶ ያለፈበት፤ ገና የቀይ ሽብር ድንጋጤ ያለቀቀው የልደታ ነዋሪ አምላክ ለዚህ ሁሉ ጉድ መፍረዱ አይቀርም ብሎ እየፀለየ በትዕግሥት የሚጠብቅበት፤ ልደታ ይህን ንቀት ያደረሰባትን መንግሥት ልኩን ታሳያዋለች የሚል እምነት በህዝቡ ውስጥ ሰፍኖ የነበረበት ወቅት ነበር። ምን ያድርግ? ያ ህዝብ ደሃ ነበር - ከልደታ በስተቀር ምን መተማመኛ አለውና።

 

የልደታ ሰው የልደታን ተዓምር ይጠብቃል። በግፈኞቹ ላይ የሚደርሰው ሁሉ የልደታ ፍርድ መሆኑን የሚጠራጠር የለም። ለምሳሌ ያህል ለማ የቀበሌ 02 ሊቀመንበርና ከሰተ የቀበሌ 07 ሊቀመንበር ከመቶ አለቃ ደስታ የከፍተኛ 22 ሊቀመንበር ጋር ተጣሉ ሲባል ”ገና ልደታ ታባላቸዋለች” ተባለ። በመኢሶንና በሰደድ ድርጅቶች መካከል የተነሳውን ጠብ ለማለት ነው።

 

”ጋምብለር የአብዮት ጥበቃው ታመመ፣ ሰውነቱ ቆሰለ” ተብሎ ሲወራ ደግሞ፣ ”ልደታ በዚህ ይብቃህ ትበለው እሱ እንኳ ምስኪን ነበር” ብሏል። ጋምብለር የሰፈሩ ኩሊ የነበረ ሲሆን፣ በኋላ አብዮት ጥበቃ የሆነ ነው።

 

መምህር ሙሉጌታ ስልቡ ጤናም የለው ሲባል ደግሞ ”ልደታ በስንት በኩል ትቅጣው ምሕረቱን ትላክለት” በመባል ታልፏል። እንደ ሁኔታው እየታየ የረገማቸው ህዝብ መልሶ ምሕረትን ከልደታ ይጠይቃል። የአንበሳ አውቶቡሷ ካድሬ የነበረችው ተጎሳቆለች ሲባል ደግሞ ”የሰው ደም ገና የሚያደርገውን ታዩታላችሁ! ልደትዬ የለችማ!” ተብሎ ወደ ሰማይ እንባ ይረጫል። ይግረም ፖሊሱ ወደ ጎጃም ተዛውሮ የቶሎሣ ሰፈር ልጅ ያኔ በቀይ ሽብር ታስሮ የነበረ አለቃው ሆኖ ተሾመ፤ የሚለው ወሬ ሲሰማ ደግሞ ”ልደትዬ ፈረደች”። ... ለእያንዳንዱ ጨካኝ ልደታ የራሷ የሆነውን ልዩ ቅጣት ያዘጋጀች ይመስላል - በልደታ ሠፈር ነዋሪዎች እምነት።

 

የልደታ ተዓምር ብዙ ነች። ልጅ እንዲሰጣት ለለመነ ልጅ፣ ጤንነት ለለመነ ጤንነት፣ ትምህርት ያልገባው እንኳ ልደትዬ ትምህርቴን ግለጭልኝ ብሎ ይሳላል። ... ወዘተ የአካባቢው ነዋሪ በተለይ ልጆቻቸው የተገደሉባቸውን አሮጊትና ሽማግሌዎች ባየ ቁጥር ለልደታ ፍርዱን እንዳትረሳ ማስታወሱ ግን የልደታ ሠፈር ሰው ሁሉ ፀሎት ነበር።

 

”አታውቋቸውም እንዴ? የነ አበበ፣ የነ ውብሸት አባት ናቸው እኮ፣ ... ልጆቻቸውን ሁሉ ቢጨርሱባቸው፣ ኀዘኑ ቢበዛባቸው ነው’ኮ ብቻቸውን እያወሩ የሚሄዱት፣ ልደታ ይኼን ነገር ዝም ትይ!!? አዬ! ...” እያንዳንዱ ነዋሪ ልደታ ፍርዷን እንድትሰጥ ይጠይቃል። የልደታ ህዝብ በቀይ ሽብር ያየውን ግፍ ልደታ እንድትበቀልለት እየለመነ በፀሎት ላይ ነበር።

 

አንድ ቀን ጠዋት የሚጠበቀው ተዓምር ደረሰ። ሠፈሩ ተበጠበጠ። የልደታ ሰው በሙሉ ወደ ሜክሲኮ መሮጥ ያዘ። ”ጉድ! ጉድ! ...” ይባል ጀመር። ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ መሬቱ መጮኽ ጀመረ። ወሬው አንድ ጊዜ አካባቢውን አጥለቀለቀው።

 

”ምንድነው የሆነው?” ብሎ አንዱ ይጠይቃል።

 

”መሬት መጮኽ ጀመረች።” ይላል ከሜክሲኮ አካባቢ የተመለሰው።

 

”የምን መሬት?” ሌላው ይጠይቃል።

 

”ጠቅላላው ሜክሲኮ አደባባይን ይዞ፣ ዴ አፍሪክን ይዞ፣ ወደ ታች ደግሞ እስከ ጥይት ፋብሪካ አካባቢ መሬት ትጮኻለች።”

 

”ምን እያለች?”

 

”ሽጉጤ ደሜ ነኝ እያለች።”

 

ወሬው ከቦታ ቦታ እየተዛመተ እንደ ሰደድ እሳት ተቀጣጠለ። ”ልደትዬ ፈረደች!” የሚለው ቃል እየተባዛ ሄደ። ልቅሶ ፊታቸውን ያበለዘው አሮጊቶች ወደ ሜክሲኮ አደባባይ ሲሮጡ እግረ መንገዳቸውን ልደትዬን እየተሳለሙ በአጭሩ ምስጋና አቅርበው አለፉ። የሜክሲኮውን ተዓምር የሰማ አብዮት ጥበቃ ደግሞ ትንግርቱ ሳይሞላ ከእግዜር ቁጣ ይድን ይመስል ቤቱ ገብቶ በሩን ዘግቶ ከእግዜር ሊደበቅ ሮጠ። ሌላው አካባቢ ደግሞ፤

 

”ልደትዬ ተዓምሯ መች ያልቃል?” ይባላል።

 

”ምን ተፈጠረ ደግሞ?” ይጠየቃል።

 

”የአምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ፖሊሶች ደግም እንፈራለን አሉ” ይባላል ...

 

”ምኑን?”

 

”ጨኽት የሚሰማበት ቦታ ላይ መቆፈር”

 

”ለምን?”

 

”የልደታ ቁጣ ነው ብለው”

 

”የቱ ጋ ነው ቦታው?”

 

”ምን የተወሰነ ቦታ አለው። ሁሉም ጋ ይሰማል። በቀይ ሽብር የተመቱት ወጣቶች ደም በዝናብ ታጥቦ ምድር ውስጥ ገብቶ ነው ይባላል”

 

”ዴ አፍሪክ ብትሄድ እሱ ነው። ሰፈሪያን ብትሄድ ይሰማል። ሜክሲኮ ጋር ብትሄድ ይሰማል። ሁሉም ጋር ብትሄድ ይሰማል። በተለይ ወደ አስፋልት ጥግ ከመጣህ በደንብ ይሰማል።”

 

”ምንድነው የሚለው?”

 

”ሽጉጤ ደሜ ነኝ ነው የሚለው አሉ።”

 

”ምን ሆነህ መሬት ገባህ ሲሉት፣ አላውቅም ሞቼ ሊሆን ይችላል። ምንም ነገር አላይም ሁሉም ጨለማ ነው ይላል አሉ።”

 

”ታዲያ ሽጉጤ ደሜ ሰው ይሆን ይሆናል። ሳይሞት ሞተ ብለው ቸኩለው የቀበሩት ይሆን?” አንዱ ይጠይቃል በመገረም።

 

”ለመሆኑ በዛ ሥም በቀይ ሽብር የተገደለ አለ እንዴ?”

 

”ሽጉጤ ደሜ የሚባል በቀይ ሽብር የተገደለ ተፈልጎ ጠፋ። ደግሞ እንኳን ሥም ስንት ሰው እንደተገደለ በቅጡ ይታወቃል እንዴ?” ይላል ሌላው።

 

ሌላኛው ደግሞ ”እስቲ አስቡት እነ ቴዎድሮስ በላይነህ (አንጃው)፣ እነ ይግረም፣ እነ ከስተ፣ እነ ለማ፣ እነ መቶ አለቃ ደስታ፣ ... የገደሉት። ከፍተኛ አራትን ተዉትና ከፍተኛ ሦስትና ከፍተኛ ሃያ ሁለትን ብቻ አስቡት። እንኳን መሬት መጮኽ ከላይ ደም አለመዝነቡ?”

 

ሌላው ደግሞ ይደግፋል - ” ማን ማን እንደተገደለ ይታወቃል ብለህ ነው? ከፍተኛ 3 ቀበሌ 53 ያሉ አብዮተኞች ለመሆኑ የገደሉትን ያውቁታል? ትንባሆ ሞኖፖል የሚገኘው ቀበሌ 07 ቢሆን በመደዳ አደለም እንዴ ሲገድሉ የነበሩት?”

 

”የዛ ሁሉ ሰው ደም ቢጮህ ይገርማል እንዴ? ስንት እናቶች’ኮ ናቸው እንባቸውን ወደ ሰማይ የረጩት። ስንት ሸማግሌ አባቶች’ኮ ናቸው ይጦረኛል ያሉትን ልጃቸውን ያጡት። አሁን ሁላችንም እግዚኦ ማለት ብቻ ነው። ለኃጥያን የመጣ ለፃድቃን እንዳይተርፍ” ይላል የእግዜርን ቁጣ የፈራ።

 

”ልደታ እንደነሱ እውር አደለችም ሁሉንም በጅማላ የምትቀጣው። እንደ ጋምብለር አቆሳስላ ለማኝ አድርጋ ነው የምትገለው። ልደትዬ የምትሠራውን ታውቃለች” ብሎ እራሱን ያፅናናል በልደታ ፍርድ የሚተማመን ሠፈርተኛ።

 

”ግን እንደሚወራው ከሆነ ልደታ ጋ የተገደሉት በሽጉጥ ነው። ደሜ የሚለው ደግሞ የነእርሱን ደም ነው ይባላል።” ይላል አንዱ።

 

”እንዲያውም የታወቁ የሰፈሩ ሽማግሌ ልደታን የሠሩት ንግሥት ነገሥታት ዘውዲቱ ጥቁር ለብሰው ሲያለቅሱ በሕልሜ አይቻለሁ ብለዋል። ድርቅ የገባ ጊዜ እኚሁ ሰውዬ ምኒልክ ተክዘው አይተዋቸው ነበር። ጉድ ነው መቼም! ...” ይላል በሕልም የሚያምነው ደግሞ።

 

ይህ የምድር ውስጥ ጩኽት የደርግን ቁጣ ቀስቅሶ ያስጨርሰናል ብሎ የፈራው ደግሞ ”አሁን ታዲያ መንግሥት ምን ሊያደርግ ነው?” ሲል ሌላ ጥያቄ ያነሳል።

 

”አየር ወለዶች ከደብረ ዘይት ሊያስመጣ ነው ይባላል። ለእንደዚህ ዓይነት ጉዳይ ይጠቅሙኛል ብሎ ደርግ ቀድሞ ያሠለጠናቸው ናቸው ነው የሚባለው። ካለመንጌ የሚያዛቸው የለም። ኃይለኞች ናቸው። ጉድጓድ ውስጥ እንዳደገ ውሻ ገና ሰው ሲጠጋቸው ላዩ ላይ ነው የሚሰፍሩት” ይላል በመደነቅ።

 

ልደታ ተጨነቀች። ቤተክርስቲያን የሚሄደው ሰው ቁጥር ጨመረ። ኮምዩኒዝም አንገዳግዶት የነበረው ኃይማኖተኛ ሁሉ ከተደበቀበት ተዓምረ ማርያሙን ይፈልግ ጀመር። የስምንተኛው ሺህ መድረስ ምልክቶች እንደገና ተጠቀሱ። ፍካሬ ኢየሱስ በእየቤቱ ተነገረ ...

 

”ከዚያም ወራት መከራ በኋላ ፀሐይ ይጨልማል፣ ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም፣ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፣ የሰማዮችም ኃይላት ይናወጣሉ፣ በዚህም ጊዜ የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፣ የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፣ የሰው ልጅንም በታላቅ ኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል፣ መላዕክቱንም ከታላቅ የመለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል።” - ማቴ 24፣29

 

የሰው ልብ ሁሉ በፍርሃት ተያዘ። የስምንተኛ ሺህ መድረስ ምልክት የሆነውን የመሬት ዋይ ዋይታ ጀመረ። በሌላ በኩል ደግሞ የግፎች ሁሉ ቁንጮ የሆነው ደርግን ደካማው ህዝብ ሊፋረደው ስላልቻለ ለአምላኩ ያደረገው ፀሎት ስለተሰማለት ህዝብ ደስ አለው።

 

በጉጉት የተጠበቁት አየር ወለዶችም መጥተው ድምፁ ወደሚሰማበት የቆሻሻ ቱቦ መግባት ፈሩ። የደፈሩት አውቶማቲክ መሣሪያቸውን ይዘው ትንሽ አንገታቸውን ካስገቡ በኋላ እንዳይገቡ ”ወደ ውጭ የሚገፋቸው ኃይል” እንዳለ እየተናገሩ ተመለሱ። ደርግ የእግዜርን ኃይል ለመዋጋት ልደታን በታንክ ከበበ።

 

ከሦስተኛው ቀን በኋላ ድምፁ እየደከመ መጣ። ሰዎች ቢጮኹም መልስ አጡ። ተፈጥሮ በቁጥጥር ሥር ሆነች። እግዜር ፈራ፣ ደርግ አሸነፈ። የልደታ ነዋሪዎች በተስፋ መቁረጥ ተከበቡ። ግን ልደታን ሄደው መሳለም አላቆሙም። የደርግ ካድሬዎች የእግዜር ኃይል ውሽት መሆኑን አመኑ። ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ሰበኩ። የፀረ-አብዮተኞች ሽብር ነው ብለውም ተመፃደቁ።

 

በአራተኛው ቀን ከሜክሲኮ በታች ከሚገኝ የቆሻሻ ማስተላለፊያ ቱቦ ውስጥ ጥቁር የሆነ ቆሻሻ የለበሰ አንድ ሰው ብቅ አለ። በአካባቢው የሚገኙ ሰዎች ደንግጠው ሮጡ። ሰውየው ወደ ሰው ሲጠጋ ሰዉ ይሸሸው ጀመር። ፖሊሶች ተጠሩ። እነርሱም ሊጠጉት ፈሩ። አየር ወለዶችም ከበቡት። ግን ማንም ሊጠጋው አልደፈረም። በሩቅ በድምፅ ማጉያ፣

 

”ማነህ አንተ? ስምህን ተናገር!” ብለው ለፈፉ።

 

”ሽጉጤ ደሜ” ብሎ መለሰ።

 

ሆኖም ማንም ሊጠጋው አልደፈረም። አየር ወለዶቹ በደረታቸው ጠመንጃቸውን ወድረው መሬት ለመሬት ተስበው ደርሰው ያዙትና መሬት ላይ አስተኙት። የፊጥኝ አሰሩትና በመኪና ጭነውት ሄዱ።

 

በሣምንቱ በፖሊስና እርምጃው ጋዜጣ ላይ፤ ... ”አዲስ አበባን ያስጨነቀው ሽጉጤ ደሜ ተያዘ” የሚል አነበብን። ሰዓት እላፊ ደርሶበት የሚሮጠው ሽጉጤ ደሜ አብዮት ጥበቃዎችን ለመሸሽ ሲል ዴ¬አፍሪክ አካባቢ ካለው ቱቦ ውስጥ ገብቶ በመደበቅ እስከ ሜክሲኮ ድረስ በቱቦ ውስጥ ከሄደ በኋላ ስካሩ ሲበርድለት መውጫ አጥቶ ሲጮህ እንደነበርና ህዝቡን እንደረበሸ አትቶ ተገቢውን ቅጣት እንደሚቀበልና ለጊዜው ግን የአዕምሮ ችግር ሊኖርበት ስለሚችል አማኑኤል ሆስፒታል እንደሚገኝ ጋዜጣው በኩራት ዘገበ። ሽጉጤ ደሜ የሰንጋ ተራ አካባቢ የቀን ሠራተኛ ሲሆን፣ ደሞዝ ተቀብሎ ውሻ ገዳይ ከሚባለው ጠጅ ቤት ገብቶ ጠጥቶ በከፍተኛ ደረጃ ሰክሮ እንደነበርም ተፃፈ።

 

የልደታ ሠፈር ወደ መደበኛው ኑሮዋ ተመለሰች። ልደታና ህዝቧ እንደገና ፀሎት ጀመሩ። ከዚያ በኋላ ሽጉጤ ደሜ የት እንደደረሰ አይታወቅም። ደርግ ግን ከዛ በኋላ አስራ ሦስት ዓመት ሙሉ የሚገድላቸው ሰዎች ደም ይጮኻል ብሎ ሳይፈራ መግደሉን ቀጠለ።

 

ተፈፀመ!


 

ይህንን ጽሑፍ በሚመለከት ሃሳብ መስጠት ለምትፈልጉ በ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ኢ-ሜይል አድራሻ ተጠቀሙ።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!