ባለፈው አንድ ዓመት በየሣምንቱ ”የረቡዕ ግጥም” በሚል ሃምሳ ሁለት ግጥሞችን ”ወለላዬ” በሚል የብዕር ስም የሚታወቀው ገጣሚ ማትያስ ከተማ ሲያቀርብልን ቆይቷል።

ገጣሚ ማትያስ ይህንን በኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ላይ ሲያስነብበን የነበረውን ለየት ያለ ግጥም ባለፈው ሣምንት ረቡዕ ቋጭቷል። እነኝህን ሃምሳ ሁለት ግጥሞች አስመልክቶ ገጣምያን፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ ፀሐፊዎች፣ ... እንዲሁም አንባብያን ያላችሁን አስተያየት በኢትዮጵያ ዛሬ የኢ-ሜይል አድራሻ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.) ትልኩልን ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን። በሥነ-ግጥም ዙሪያ በተለይ ባለሙያዎች ያላችሁን አስተያየት ብትሰጡና ኢትዮጵያ ዛሬን የመማሪያና ማስተማሪያ መድረካችሁ ታደርጓት ዘንድ በዚህ አጋጣሚ aቸልንገልጽ እንወዳለን።

ከዚህ በታች የወለላዬ (ገጣሚ ማትያስ ከተማ) ሃምሣ ሁለቱ የረቡዕ ግጥሞች ቀርበዋል። መልካም ንባብ!

ቁጥር ፩

አሁንስ በዛ የኔ ችግር

መነጽር ፍለጋ ሌላ መነጽር

ይህስ አልመሰለኝም የዓይን

ሰውሮኝ ነው ህሊናዬን

 

ቁጥር ፪

መሄጃ መች አጣሁ ወደሷማ

ሞልቶኛል ብዙ ጫማ

አልገባችሁም ነገሩ

ተሸፋፍኖ ነው ፍቅሩ።

 

ቁጥር ፫

እገደል አፋፍ ዛፍ በቅሎ

ለቆረጣ አልመች ብሎ

ዘመድ አዝማድ በአንድነት

እንክበደው ብሎ ወጣበት

ዛፉ ተገንድሶ ወደቀ

የ‘ንክበደው ዘርም አለቀ

 

ቁጥር ፬

ለምን ትላለህ ሰው ጠፋኝ

መጀመሪያ እራስህን አግኝ

አንተን አግኝተህ ስታበቃ

ሌላ ሰው ፈልግ በቃ።

 

ቁጥር ፭

እኔ ክፉ ሆንኩ በል ወንድሜ

እኔን አትጥራኝ አለስሜ

ሰው ከፋ ብለህ ጠልተከኝ

ከኔ ፍቅር አትመኝ።

 

ቁጥር ፮

ሲበርደን ኡ ኡ ታ

ሲሞቀን ኡ ኡ ታ

ሲርበን ኡ ኡ ታ

ስንጠግብ ኡ ኡ ታ

ስንጠማ ጩኸት

ስንጠጣ ጩኸት

ስንፋቀር ጩኸት

ስንጣላ ጩኸት

በድለንም ለቅሶ

ሲበድሉን ለቅሶ

ግራ ግብት አለው

እግዜሩ ጨርሶ

 

ቁጥር ፯

መጀመሪያ ለራስህ ነፃነት ስጥ

ከሱ አገኛለሁ ብለህ አትለማመጥ

መብትህን እራስህ ሳትጠብቅ

አትገረም በእሱ መንጠቅ

 

ቁጥር ፰

እነዛን ሰዎች ምከሯቸው

አለበለዚያ ዕድሜም የላቸው

ለራሳቸው ብቻ እየበሉ

እንዴት ሌላውን ’ተራብ’ ይላሉ

የተራበ ይጠግባል ኋላ

የጠገበ በጠገበ ሲበላ

 

ቁጥር ፱

እዛ ቀብር ላይ ያየሁህ

ወይኔ ወይኔ ስትል የሰማሁህ

ለሱ ነው ላንተ የጮኽከው

እንባህን እንደዛ ያፈሰስከው

 

ቁጥር ፲

ከናቅከው ስለሚንቅህ

አትናቀው እንዳይንቅህ

አትመልከት ካንተ ማነሱን

ማንም አይከለክለው ንቀቱን

 

ቁጥር ፲፩

ቃሌን አለውጥም ባለች

እንደማንዴላ ታሰረች

ልዩነቱ ከማንዴላ

ጥቁር በጥቁር ተበላ

ሌላም ልዩነት ታይቷል

ወንድ እያለ ሴት ተፈርቷል።

 

ቁጥር ፲፪

እሁድ ጠዋት ተጠራርተው

ጥቂት ሰዎች ተሰባስበው

ቁጭ አድርገው መርዶ አረዱኝ

”ዘሃራ ቤይሩት ሞተች” አሉኝ

እኔ ምንድነኝ ለዘሃራ

ብዬ ነገሩን ሳጣራ

ለካስ ልጄ - ሣራ ብሩ

ሆና ኖሯል - ዘሃራ ኑሩ

 

ቁጥር ፲፫

ሀገሬ ናፍቆኝ ሄጄ

ለካስ ሀገሬ አይደለም ወዳጄ

መልኬን አትኩረው እያዩኝ

ቋንቋዬን በትክክል እየሰሙኝ

'ዘርህ ምንድነው?' ብለው ጠየቁኝ

 

ቁጥር ፲፬

ሠላምታዬን ወስደህ ከበላኸው

ምን ቸገረኝ ዕዳው ያንተ ነው

ትከፍላታለህ አንድ ቀን

ወይ በደስታ ወይ በኀዘን

 

ቁጥር ፲፭

እንዳተ ማናለ ዕድለኛ

ሆንክ እንጂ መንገደኛ

በቁምህ የቆረጥከው ዕጣ

ሞተህ ላንተ ወጣ

 

ቁጥር ፲፮

ሳስርና ስፈታ ስስብ ስሸመቅቅ

ብዙ ዘመን ኖርኩኝ ስዘዋወር ስለቅ

ዘንድሮም ደርሶብኝ ይሄው መገላበጥ

ልብስ መሃል ቆሜ መስያለሁ ሸቀጥ

 

ቁጥር ፲፯

ድንገት መሃላቸው እሳት ወደቀና

እታች ያለ ሲሞቅ የላዩ ቀረና

ንገሩ ለሁሉም ከላይ ያለው ይውረድ

ከዛ ላይ ተሰቅሎ ተንጠልጥሎ እንዳይነድ

 

ቁጥር ፲፰

ለመኖር እንዲችል ሁሉም እንዳመሉ

ምናለ በዕቅዱ ትራባለህ ቢሉ

ለነገሩ ተዉት እናውቃለን በደንብ

ጥጋብ ከነገሩን መምጣቱን ረሃብ

 

ቁጥር ፲፱

ሆዴን ምሞላበት በጎደለ ቁጥር

የተጓዝኩት ጉዞ ቢለካ በሜትር

ወይ የቀን ውሎዬ ቢሰላ በግምት

እችል ነበር ምድርን ዘጠኜ ልዞር

 

ቁጥር ፳

ልጅነት ነፍስ ውስጥ ስውር አዋቂነት

በስተርጅና መሃል ብጣቂ ልጅነት

ለካስ አለ ኖሯል በመጠኑ ትንሽ

ባለፈው ቅዳሜ ሆኜ ነበር ማሙሽ

 

ቁጥር ፳፩

ህመምህ እንዳያገረሽብህ ኋላ

መጥፎ ነው የሰው ጥላ

ብለው ሲሉህ ሰምቼ

ለወንድምነትህ ሳስቼ

ልመክርህ ተነሳሁ በጥብቅ

ከጥላቸው እንድትርቅ

 

ቁጥር ፳፪

ያገለግላል ፈሪ ለእናቱ

ቢሉህ አትስማ እስከተረቱ

አያጣም መውጫ ደፋርና ጭስ

ብትል ይሻላል አንተ ሰው ተነስ

 

ቁጥር ፳፫

አስፍቼ እጽፋለሁ ብለህ ከመቀመጥ

ድርጊቱ እንዳይጠፋ አንተም እንዳታመልጥ

ሰብሰብ አጠር አርገህ በቆንጆ አማርኛ

የዕለቱን በዕለቱ ወርውርና ተኛ

 

ቁጥር ፳፬

እውቀቱ ሲአነጥስ ወጥታ ምትጠፋበት

መልክና ቁመናው እዚህ ግባ እማይሉት

መሆኑን ስናውቀው እሱም እያወቀ

እዛ ላይ ተሰቅሎ ህዝቡን ሁሉ ናቀ

ሥልጣን ገንዘብ ሲያገኝ ምኞቹ ሲሳካ

የሰው ልጅ በእብሪት ይሞላል ወይ ለካ

 

ቁጥር ፳፭

ልክ እንደሥራህ አታጣምና

ደጋግ ጣቶች ቀና ልቦና

ይኑርህ ጎበዝ ደግነት ተማር

ምርጫ ከመጣም እሷው ላይ አጥቁር

 

ቁጥር ፳፮

ህይወት አስተምሮት ካልመለሰው በቀር

አድናለሁ ብለህ ይሄን ሰው በምክር

ያለህን አሟጠህ ጆሮው ብትገለብጥ

እመነኝ ጨርሶ አትችልም መለወጥ።

 

ቁጥር ፳፯

አላህ ቢሻ ኖሮ ብዙ እንድንናገር

አፍን ሁለት አድርጎ በፈጠረ ነበር

ሆኖም በመውደዱ ብዙ እንዳናወራ

አፍን አንድ አደርጎ ሁለት ጆሮ ሠራ

 

ቁጥር ፳፰

ተጨነቅ ያለው ሰው አዕምሮው አይረፍ

ያሻው የወደደው ሞልቶ ቢትረፈረፍ

የነገውን ስቦ ያምናውን ጎትቶ

ሲፈጭ ነው የሚኖር ሳይጋግር አቡክቶ

 

 

ቁጥር ፳፱

ምንም ነገር ሳልይዝ ባዶዬን መጥቼ

እውቀት በመሰለኝ ክፋት ተሞልቼ

ግዜዬን ስጨርስ ከዝች ዓለም ስሄድ

ማምለጫዬን እንጃ ከሚጠብቀኝ ፍርድ

 

ቁጥር ፴

ፍራቻ ሠልጥኖ እጅግ ተቀናጣ

ገደቡን ዘለለ ከአናት በላይ ወጣ

ግፍ ስቃይ መከራ ይበቃናል ባልኩኝ

እንኳንስ ሌላውን እራሴ እኔን ፈራኝ

 

ቁጥር ፴፩

መጨበጫም የለው መቼም የኔ ጣጣ

በሀገሬም አልኖር ካገሬም አልወጣ

እዛ ስሆን እዚ ከዚ እዛ እያሰብኩኝ

ማደሪያ የሌለው ከንቱ አሞራ ሆንኩኝ

 

ቁጥር ፴፪

ደግ መሃል ገብቶ ”ር” ተወትፎ

ደርግ አደረገብን ይህ የፊደል መጥፎ

አሁን ደግሞ ይሄው ”ያ” ክፉ ሸፋፋ

ወኔ መሃል ገብቶ ሀገርን አጠፋ

እኛ ባንቸኩል ዘመኑም ባይከዳን

ቀስ መሃል ሆኖ ”ኃ” ነበር ሚሻለን

 

ቁጥር ፴፫

በጭለማ መሃል ምንም በሌለበት

በዚህ በአሁን ዘመን የተገኘህ ወጣት

ዝምታህ ምንድነው ሰምተህ ነው ሳትሰማ

በየአደባባዩ እንዲህ ስትታማ

ማንም አይመጣልህ አንተ ራስህ መልስ

ከናት ካባቶችህ ምን አገኘህ በውርስ

 

ቁጥር ፴፬

ቀኑ ልማዱ ነው ይመሻል ይነጋል

መብራቱም እንደዛው ይሄዳል ይመጣል

ዝግጅት እናድርግ ሻማ ለመለኮስ

አይቀርም መጥፋቱ ካዲስ'አባ መለስ

 

ቁጥር ፴፭

ከሀገር እርቀን ከወዳጅ ከዘመድ

ብዙ ብንቆይም ውጪ በመሰደድ

እንመለሳለን ሞተን ለመቀበር

ለእናት ሀገራችን አለን ልዩ ፍቅር

 

ቁጥር ፴፮

ሕይወትን በዘዴ ጥፎና ለጥፎ

ገበናውን ከድኖ ሰው ቢኖርም አርፎ

ከውስጥ ወይ ከውጪ የሚጠዘጥዘው

የራሱ የሆነ ሁሉም ሕመም አለው

 

ቁጥር ፴፯

ሆዱ ያኖረውን በድንገት ሲያወጣ

ተሰደብኩኝ ብለህ ወንድሜ አትቆጣ

ይልቅ ነካ አድርገው ቆጥቦ እንዳያስቀር

ያንግዜ ነው ጆሮ ባዳነቱ የሚቀር

 

ቁጥር ፴፰

የትናንትናውን ዛሬ ላታገኘው

ብለህ አትናገር ”ደሞ ለዛሬ ሰው”

ቀኑን ከተረከብክ እስከ አሰስ ገሰሱ

የዛሬ ሆነሃል አንተም ልክ እንደሱ

 

ቁጥር ፴፱

”ግልፅ ነው ይሄ ሰው የግንባር ላይ ሥጋ

እውነትን አፍረጥራጭ ጨርሶ ሳይሰጋ”

በማለት ብዙ ሰው ይችላል ሊያደንቅህ

ወይም ባፉ ብቻ ሸነጋግሎ ሊያልፍህ

እኔ ግን አጥብቄ እናገርሃለሁ

ሁሉንም አትዘርግፍ ብዬ እመክርሃለሁ

 

ቁጥር ፵

እውነትን የሚወድ ጥበብ የሚያፈቅር

ተለይቶ አያውቅም ምንግዜም ከችግር

ስለዚህ ”እንርዳው”፣ ”አክብረው”፣ ... አትበለኝ

ሲሞት እደርሳለሁ ከልምዴ አታርቀኝ

 

ቁጥር ፵፩

ሚስጥር ያልሆነውን ’ሚስጥር’ ብሎ ነግሮኝ

ሚስጥሬን በሚስጥር አታሎ ነጠቀኝ

ሁለተኛ ሚስጥር አልከፍልም በሚስጥር

ሚስጥሩን በሚስጥር ከማስቀመጥ በቀር

 

ቁጥር ፵፪

የመኖር ሚስጥርን ጠልቆ የተረዳ

ለሱው ለራሱ ሲል ማንንም አይጎዳ

በደል የሚፈጽም፣ ሰው የሚነካ ግን

እንቅልፉም ወግ የለው ይኖራል ሲባንን።

 

ቁጥር ፵፫

እጃችሁ ከገባ ድንገት ብታገኙት

ሰይጣን የታባቱ ቀጥቅጡ ውገሩት

ነገር ግን ጨርሶ አይገባም መግደል

ጥፋት ስናጠፋ ማን አሳተኝ እንበል

 

ቁጥር ፵፬

ጥላቻ ንትርክ - አሉባልታ ክፋት

ምቀኝነት ተንኮል - ራስ ወዳድነት

በሰው ተመስለው አብረው እየዋሉ

እርሙን አስገደፉት ሰዉን እያባሉ

 

ቁጥር ፵፭

ከሰው ሰማሁ ብለህ አትጥላም አታፍቅር

ነገሩን ራስህ በአንተው ሚዛን ስፈር

ለአድማጭ እንዲረዳ ወሬውም እንዲጥም

አያጣም አንዳንዴ ማጣፈጫ ቅመም

 

ቁጥር ፵፮

ሕይወቱን ሲያቃና ኑሮውን ሲያሳድድ

ከልጅ የተለየ ከወዳጅ ከዘመድ

በናፍቆት በሃሳብ ላደረሰው ጉዳት

መክፈል የሚገባው ለካስ ካሣ አለበት

 

ቁጥር ፵፯

እንዲህ ዛሬ ልንታረቅ

ከረምንበት ስንቧጨቅ

በፀብ መሃል የበደለኝ

ቅንነቴን ገደለብኝ

 

ቁጥር ፵፰

ከበደኝ ብላቸው የኑሮዬ ሸክሙ

ተቀላቀል አሉኝ ግባ ከሲስተሙ

ምንድነው የሚባል ይሄ በአማርኛ

ሲስተም ተከትለን አድገናል ወይ እኛ?

 

ቁጥር ፵፱

ቢሸሽና ቢያመልጥ ቢፈራ ቢደበቅ

ድምፁንም ቢያጠፋ ከሀገሩም ቢርቅ

ፈሪ እንዳይመስላችሁ የሰው ልጅ ለነፍሱ

እሞታለሁ ብሎ አይሳሳም ለራሱ

 

ቁጥር ፶

ስጠጣው ሲጠጣኝ

ስቅመው ሲቅመኝ

ሳጨሰው ሲያጨሰኝ

ላልጨርስ ጀምሬው

ራሴን ጨረሰኝ

 

ቁጥር ፶፩

አጠፋ አይመስለኝም ድንገት ካጠፋሁኝ

ስተቴን እንዳውቀው ባንተ ዓይን አሳየኝ

በአፍህ ልናገር በጆሮህም ልስማ

ዘመን እንዲለምደኝ ከሰው እንድስማማ

 

ቁጥር ፶፪

የረቡዕ ግጥም ሣምንቱ ሲሰላ

ሃምሳ ሁለተኛው ድፍን ዓመት ሞላ

እኔም ከቀኑ ጋር እየሮጥኩ አብሬ

በዚህ አበቃሁኝ ሥራዬን ቋጥሬ

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ