Prof. Mesfin W/Mariamፕሮፌሠር መስፍን ወልደማርያም (ጥር 2001 ዓ.ም.)

በብዙ ሚልዮን ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሽምግልና አድባር ነው፤ ከቤተሰብ ጀምሮ በትንሽም ማኅበረሰብ ውስጥ ግጭት አይጠፋም፤ የሚፈጠረውን ማናቸውም ዓይነት ግጭት ለማለሳለስና በስምምነት ለመተካት የሚደረገው ባህላዊ ሽምግልና በመልኩም በባህርዩም ዛሬ በሽምግልና ስም ከምናየው በጣም የተለየ ነው። በኢትዮጵያ ባህል ሽምግልና የሚነሳው ከመንፈሣዊ መሠረት ላይ ነው። ሽምግልና የአምላክ ተግባር ነው።

 

ሽምግልና ለዕርቅ፣ ለፍቅርና ለሠላም የቆመ መንፈሣዊ አድባር ነው፤ ይህ አድባር ሕንፃ የለውም፤ ለሽምግልና የበቃው ሰው በአዕምሮው፣ በልቡና በመንፈሱ ይዞት የሚዞርና ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየ ነው። የሽምግልና መንፈሣዊ መሠረቱ በዋናነት የሚከተሉት ይመስሉኛል።

 

  • “ጽድቅን (እውነትንና ትክክለኛነትን) የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፤ ይጠግባሉና፤”
  • “የሚምሩ (ምሕረትን የሚያደርጉ) ብፁዓን ናቸው፤ ይማራሉና) ምሕረትን ያገኛሉና)፤”
  • “የሚያስታርቁ (ሠላምን የሚያመጡ) ብፁዓን ናቸው፤ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና”

 

ቃላቱ ይለወጡ ይሆናል እንጂ ቁም-ነገሩ በእስልምናም ተጠናክሮ ያለ ይመስለኛል። ዕርቅ፣ ፍቅር፣ ሠላም መንፈሣዊ ዋጋ ያላቸው ቁም-ነገሮች ናቸው። ሌላ ዋጋ ሲሰጣቸው ይረክሳሉ፤ ወደ ሸቀጥነት ይወርዳሉ፤ ሽምጋዮቹንም፣ ተሸምጋዮቹንም ያዋርዳሉ።

 

እንግዲህ ለሽምግልና ብቁ የሚሆነው ማን ነው? ሽምግልና ወይም ከሽምግልና ተጣምረው መገኘት ያለባቸው ብዙ ባህርዮች አሉ። መንፈሣዊነት አንዱ ባህርይ ነው። ለእኔ እንደሚገባኝ መንፈሣዊነት ለእውነት፣ ለእኩልነትና ለፍትህ መገዛት ማለት ነው። “ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ” መሆን አለባቸው። ለግዑዝ ነገር፣ ለጉልበትም ይሁን ለገንዘብ የማይሸነፉ ሰዎች መሆን ይገባቸዋል። ለሽምግልና ብቁ የሚሆኑ ሰዎች በአንድ በኩል በፈሪሃ እግዚአብሔር፣ በሌላ በኩል በሰብዓዊነትና በፍቅር የሚመሩ ለሠላም የቆሙ ናቸው። በእውቀትም በኩል የማኅበረሰቡን ታሪክ፣ ባህልና ወግ ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ በተረትና በምሳሌ እያዝናኑ በርቱዕ አንደበት የማስረዳትና የማሳመን፣ የማቀራረብና የማስታረቅ ችሎታና ብልሃት ያላቸው፣ የሚያሳፍረውንና የተሸሸገውን በተራቀቀ ዘዴ የመግለጥ፣ የአበጠውን የማፍረጥና የኅሊና ቁስልን የማሻር ጥበብ የተላበሱ ሰዎች ናቸው።

 

በነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ለሽምግልና የሚፈለጉ ሰዎች መንፈሣዊ ሥልጣን የተሰጣቸው ናቸው። የሚከበሩና ሲናገሩም የሚደመጡ ናቸው። ከሁሉም በላይ የሚታመኑ ናቸው። ሰሞኑን በፍልስጥኤማውያን አበሳ ላይ በቢቢሲ ውይይት ሲደረግ አንድ አስተያየት ሰጪ ጥልቅ ነገር ተናገረ፤ ደካማ ሰዎች ሠላምን አያመጡም አለ። ለሽምግልና የሚፈለጉ ሰዎች የፈረጠመ መንፈሣዊ ወኔ ያላቸው እንጂ ደካሞች ሊሆኑ አይችሉም።

 

መንፈሣዊ ሥልጣን ስል ክህነት ብቻ ማለቶ አይደለም። ክህነት ሳይኖራቸው ጨዋ ሽማግሌዎች መንፈሣዊ ሥልጣን ሊኖራቸው ይችላል። ማኅበረሰቡ የሚያከብራቸውና ቃላቸውን የሚያዳምጥ፣ የሚታዘዛቸውም ሲሆን መንፈሣዊ ሥልጣን አላቸው ማለት ነው። የክህነት መንፈሣዊ ሥልጣን ብቻውን ለሽማግሌነት አያበቃም፤ ነገር ግን በክብረ ነገሥት የተሰጠውን መመሪያ የተቀበለ ካህን ለሽምግልና ብቃት እንደሚኖረው አያጠራጥርም። ክብረ ነገሥት የሚከተለውን ይላል፤ “ከንጉሡ በታች ያለው ህዝብ ንጉሡን ቢያማ ጥሩ አይደለም፤” ይልና።

 

“የክርስቶስ የእውነት ፀሐይ በልባቸው ስላለ ካህናትን ጨለማን የሚያጠፋ ብርሃን አድርጎ ሰይሟቸዋልና ልቡና ያለው ካህን ስለሚያያቸው ሥራዎች ንጉሡን ይገስፀዋል፤ … ካህን ሆይ አንተ ደግሞ የሰውን የታወቀ ኃጢአት ስታይ መገሰፅን አትፍራ፤ ሰይፍም፣ ስደትም አያስፈራህ።”

 

መንፈሣዊ የክህነት ሥልጣንን ይዞ የተገለጸው መንፈሣዊ ወኔ የሌለው ሰው ለሽምግልና አይበቃም። በክህነት የገኘውን ሥልጣን ከኃይማኖት ውጭ በማኅበራዊ ኑሮ ውስጥ ከህዝብ አያገኘውም፤ “የእውነት ፀሐይ” ሆኖ ጨለማን፣ ጠብን፣ አለመተማመንንና አለመስማማትን የሚያስወግድ መሆን አለበት።

 

በሌላ በኩል ስናየው በሽምግልና የእውነተኛነትን አስፈላጊነት እንድንገነዘብ ያሻል፤ “እውነት ነፃ ያወጣል፤” የተባለው ለሽምግልና መሠረታዊ መመሪያ ነው። የሽምግልና ዓላማ የበደለው ሰው ከኃጢያቱ፣ የተበደለው ሰው ከቂሙ ነፃ እንዲወጣ ለማድረግ ነው። ነገሮችን አድበስብሶ ለማስታረቅ መሞከር ሽምግልና አይሆንም። ዕርቁ በጣም ጊዜያዊ እንጂ ዘለቄታ የሚኖረው አይሆንም። በሽምግልና የበደለው ይለያል፤ የበደሉ ዓይነት ይታወቃል፤ የበደሉ መጠን ይመዘናል፤ የበደሉ ተደጋጋሚነት ይታያል፤ በመጨረሻም የበደለው ሰው ድንጋይ ተሸክሞ ይቅርታ እንዲጠይቅ ወይም ተገቢውን ካሣ እንዲከፍል ይደረጋል። የበደለው ሰው ካሣ እንዲከፍል ሽማግሌው የሚያደርገው ጥረት የተበደለው ሰው ይቅርታውንና ካሣውን ተቀብሎ ቂሙን ከልቡ እንዲነቅል ከሚደረገው ጥረት ያነሰ አይደለም። የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳ የሚባለውን ለማስቀረት ነው፤ ወንድ ልጅ ሲወለድ ደም መላሽ የሚል ስም የሚሰጠው ቂምን ለማውረስ ሲባል ነው።

 

ዕርቅ የፈለገን ንጉሥ ገበሬ ያስታርቀዋል፤ ዕርቅ የማይፈልግ ገበሬን ግን ንጉሥም አያስታርቀው የሚባለው ችግሩ በበዳዩ ወይም በአጥፊው ሰው ላይ ብቻ ሳይሆን ወደፊት፣ ሲመቸው በደሉን በሌላ በደል ለመመለስ አድብቶ በሚጠብቀው ላይም ስለሆነ ነው። የተበደለ ሰው ቂምን በልቡ ቋጥሮ ይይዛል፤ የዕርቅ ዓላማ ይህንን ቂም ከስሩ ነቅሎ ለማጥፋት ነው። ይህ በማድበስበስ ሊሆን አይችልም። በተለይም ማድበስበስ የማኅበረሰቡ ባህል በሆነበት ሀገር ማድበስበስ መሠረታቺና ዘለቄታ ያለው ዕርቅ ያመጣል ብሎ ለማመን አስቸጋሪ ነው። አድበስብሶ ማስታረቅ ጠቡን ለወደፊት በቀጠሮ ማቆየት ነው፤ እንዲያውም ወደሚያገረሽ ጠብ ያደርሳል።

 

ችግርን ከመፍታት ይልቅ ችግርን የማራባት ዝንባሌ ያለው ማኅበረሰብ ትዝብታቸውና ምስክርነታቸው በእውነት ላይ የተመሠረተና ዘለቄታ ያለው ዕርቅንና ሠላምን የሚያመጡ አድባሮች ያስፈልጉታል። ዛፍ በሌለበት እምቧጮም ዛፍ ነው እንደሚለው የጎንደሬዎች አባባል እየሆነ ሽምግልና ከብፁዕነቱ፣ ከጽድቅነቱ፣ በአጠቃላይ ከአምላካዊና መንፈሣዊ ተልዕኮው ወጥቶ መሸጦ እየሆነ ነው። መሸጦ ሽምግልና ከኢትዮጵያ ባህል ጋር በጭራሽ የባህርይም የዓላማም ዝምድና የለውም። ፈረንጆች ከባልና ሚስት ጠብ ጀምሮ እስከሠራተኛና አሠሪ የሚያደራድሩበት መሸጦ ሽምግልና አላቸው። መሸጦ ሽምግልና (ሽምግልና ካልነው) ጠበኞቹ ደንበኞቹ ሆነው እንዲመላለሱለት የሚፈልግ ነው፤ ንግድ ነው። በመሸጦ ሽምግልና እውነት በጮሌነት ይተካል፤ የማያዛልቀውም ለዚህ ነው።

 

እውነትን የሚፈራ ሰው ለኢትዮጵያ ባህል ሽምግልና አይበቅም፤ ራሴን ማስተዋወቅ አይሁንና አንድ ምሳሌ ላቅርብ፤ አንዲት በጣም የበሰለችና ጎበዝ ፀሐፊ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ትሠራ ነበር። እናትዋ ባል አግኝተውላት ሊድሩ ይደግሳሉ፤ እስዋ በበኩልዋ የምትወድደው ሰው አላት። ጨነቃትና ተደብቃ አስመራ ሄደች። በኢትዮጵያ ዓየር መንገድ የሚሠራ ወንድምዋ የቤተሰቡን መጨነቅ ነገረኝ፣ በአንድ ጓደኛዬ በኩል አስፈልጌ አገኘኋትና ወደ አዲስ አበባ እንድትመጣና በእኔ ቤት እንድትቀመጥ አደረግሁ፤ ከጥቂት ቀናት በኋላ አስፈላጊውን ሁሉ ካመቻቸሁ በኋላ ልጅቱን ወደ እናትዋ ቤት ይዤ ሄድሁ።

 

እናትና ልጅ ማዶ ለማዶ ተቀምጠዋል፤ እኔ ስለልጅቱ የማውቀውን በዝርዝር ለእናት ነግሬ፣ እሳቸው ይቺን የበሰለችና ራስዋን የቻለች ልጃቸውን እንደትንሽ ልጅ ቆጥረው ሕይወትዋን ሊያናውጡባትና የምትወዳቸውንና የሚወዱዋትን ልጃቸውን ማስቀየማቸውን በጣም በቁጭት ነገርኋቸው። በድንገት እናት ብድግ ብለው በቀጥታ ልጅቱ ወደተቀመጠችበት ሄደው እግርዋ ላይ “ማሪኝ!” ብለው ወደቁ፤ ልጅቱ በበኩልዋ “ማሪኝ!” እያለች ወድቃ የእናትዋን እግር ትፈልጋለች። ሁለቱ መሬት ላይ ወድቀው ሲንፈራፈሩ እንባ አነቀኝና ተነስቼ ወጣሁ። ልጅቱ ዛሬ ትልልቅ ልጆችን ያደረሰችና የሞቀ ትዳር ያላት ነች። የእናቲቱን በቆሎ እውነትን የመቀበል ችሎታ በጣም አደንቃለሁ፤ እውነት ነፃ ያወጣል።

 

ከዚህ የእናትና ልጅ አለመግባባት በጣም የላቀና የአፍሪካን አገሮች በሙሉ የሚነካ ምሳሌ አለ። አፄ ኃይለሥላሴ የአፍሪካ አንድነትን ያቋቋሙ ጊዜ (ማንም ሌላ ሰው አቋቋመው ሊባል የሚቻል አይመስለኝም) ብዙ የተጣሉ፣ አንበሶች ነን የሚሉ መሪዎች ነበሩ (እነናሳር፣ እነቤንቤላ፣ እነኒዬሬሪ፣ እነኢዲ አሚን፣ …)፤ የመጨረሻው ቀን የጃንሆይ የመንፈሥ ሥልጣን ሁሉንም እኩል ወጥሮ ይዞ የአፍሪካ አንድነት ቻርተር ሳይፈረም ከስብሰባው አዳራሽ አንወጣም ብለው እስከሌሊቱ ስምንት ወይም ዘጠኝ ሰዓት ድረስ አቆይተው ተፈረመ። ያን ዕለት የተሰማኝ ደስታና ኩራት በሕይወቴ የማላውቀው ነው። እነዚያን ከእኔ በላይ ማን አለ ብለው በትዕቢት የተወጠሩ አምባገነኖች ሁሉ ማሳመንና ሰነዱን እንዲፈርሙ ማድረግ በዕለቱ (በሌሊቱ) እዚያ ለነበርን ሰዎች የሚያስገርም ተዓምር ነበር። ለተጣሉት ሁሉ የሚጠቅም የፀዳ ዓላማ ይዘው እውነት ላይ ሲቆሙ የመንፈሥ ሥልጣን ይሆናል።

 

ዕርቅን የሚፈልግ ማን ዕርቅን የሚፈልግ ሠላምን የሚፈልግ ነው፤ ዕርቅን የሚፈልግ ከራሱ በላይ የአምላክም ሆነ፣ የሕግም ሆነ፣ የህዝብ ኃይል መኖሩን የሚያምንና አርቆ የሚያስብ ሰው ነው። ምንም ዓይነት ተጠያቂነት የሌለበት መስሎ የሚታየው፣ እያጠቃሁ ለመኖር የሚያስችለኝ ጉልበት አለኝ ብሎ የማያምን ሰው፣ ከጉልበቱ ውጭ የሚተማመንበት ምንም ኃይል ስለሌለ ዕርቅን የሚፈልግበት ምክንያት አይታየውም። ተበዳይም ቢሆን አቅሙን አሳንሶ ገምቶ ደሃ ተበድሎ ማሩኝ ይላል በቶሎ እንደሚባለው አለመቀየሙንም ለመግለጽ ሲል ራሱን በደለኛ አድርጎ በማቅረብ ጉዳዩን በዳዩ እንዲረሳለት ይሞክራል። ነገር ግን በዳዩም ሆነ ተበዳዩ ከሚያቆራኛቸው የበደል ሰንሰለት አይላቀቁም፤ በዳዩ ተበዳዩ አይተኛልኝም ብሎ በስጋትና በፍርሃት ይኖራል፤ ተደዳዩም የበዳዩን ፍርሃትና ስጋት ስለሚያውቅ ሲመቸው ያጠፋኛል ብሎ በስጋትና በፍርሃት ይኖራል፤ ዕርቅ የሚያስወግደው ይህንን በሁለቱም በኩል ያለውን ስጋትና ፍርሃት ነው፤ እውነት ነፃ ያወጣል የሚባለው የሚሠራው ለዚህ ነው፤ ሽምግልና በእውነት ላይ እንዲቆም የሚያስፈልገውም ለዚህ ነው።

 

ሽምግልና መንፈሣዊና የእውነት መሠረቱን ሲያጣ ምን ውጤት እንደሚያስከትል አሁን ወይዘሮ ብርቱካን እንድትታሰር ሲደረግ ታየ፣ በሽምግልናው ውስጥ ከነበሩት ሰዎች ውስጥ ዋናውን ፕሮፌሠር ኤፍሬምንና ግሩም ግሩም ፀሎቶችን ሲያደርግልን የነበረውን ካህን ዳንኤልን፣ በመጨረሻው ላይ ቢመጣም የሕጉን ሥርዓት ሲያፍታታልን የነበረውን የሕግ ምሑርና ጠበቃውን አቶ ታምሩን ጨምሮ አንድም ሰው የምስክርነት ቃሉን ለህዝብ ማሳወቅ አለመቻሉና እውነቱ ሲዳፈነና ሰው ሲጎዳ የደኅንነታቸውን አርምሞ መምረጣቸው የሽምግልናውን ዓይነት የሚናገር ይመስለኛል። ይህም ሆኖ ሽማግሌዎቹ ታስረን ለነበርነው ሰዎች ያሳዩትን መቆርቆርና ለሀገሪቱ ሠላም የነበራቸውን መልካም ምኞት ለማስተጋባት ያደረጉትን ጥረትና ትጋት በመገንዘብ ምስጋናችን ሊቀነስባቸው አይገባም፣ እውነቱን ግን ከነሱ መስማት ካልቻልን በእኛ በኩል ያለውን መናገራችን አይቀርም።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ