መስፍን ወልደማርያም (ፕ/ር)

በዛሬው ጊዜ ዓለም አቀፍ ሕጎች፣ በተለያዩ የአካባቢ ማኅበሮችና በተባበሩት የዓለም መንግሥታት ማኅበር ታትመውና ታውጀው፣ ተሰብከው፣ ብዙ ዲስኩሮችም በታላላቅ ሰዎች በተደጋጋሚ ተደርጎባቸዋል። ከብዙ ዓመታት በፊት ቻይና ቲቤትን ስትውጥ፣ ለጥቂት ጊዜ ተወራና ተረስታ፤ እኛም ካልረሳነው ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ስትወር እንዲሁ ነበር፤ ዛሬ እኛም ወግ ደርሶን ከወራሪዎች ጋር መሰለፋችን በሰፊው እየተወራ ነው። አሁን ደግሞ የአውሮፓ ሕብረት “ቲቤት የቻይና አካል ነች” ብሎ ዐወጀ ይባላል። እንግዲህ ወረራ በይርጋ ይጸድቃል ማለት ነው፤ ጉልበተኞች ጨክነው ዘመናትን ካስቆጠሩ፣ ወረራው በይርጋ እንደሚጸናላቸው አዲስ ትምህርት እየተገኘ ነው። አሜሪካ በኢራቅ ስድስተኛ ዓመቱን እያስቆጠረ ነው፤ ስንት ዓመት ይቀረዋል? ሆኖም የአሜሪካ መንግሥት ከህዝብ ፈቃድ ውጭ ጉልበት የለውምና ወረራው በአሜሪካ ህዝብ ትዕዛዝ የሚያበቃበት ጊዜ ያለ ጥርጥር ይመጣል።

 

 

ዘመኑ መላ-ቅጡ የጠፋው ዓይነት ወረራ በዘፈቀደ የሚካኼድበት ሆኗል፤ እሥራኤል በፍልስጥኤማውያን ላይ የሚፈጽመው ዕለታዊ ግፍ አይነሳ፤ አሜሪካ ፈቃደኞች የሆኑትን አገሮች አሰልፎ ኢራቅን ወረረ፤ አሜሪካን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን አገሮችን አስተባብሮ አፍጋኒስታንን ወረረ፤ አሜሪካ ኢትዮጵያን ይዞ ሶማልያን ወረረ፤ ኢትዮጵያ ነች ወራሪዋ ለማለት ከበደኝ፤ ኢትዮጵያ የወራሪ የሶማልያን ጦር እያሳደደች፣ የኢትዮጵያ ጦር ወደ ሶማልያ ድንበር ሲጠጋ በ1956 ግድም በአሜሪካ ትዕዛዝ ከድንበር እንዳያልፍ ታግዷል። እንደገና የሶማልያን ጦር ተከትሎ የሶማልያን ድንበር እንዳይጥስ አሜሪካ የሶቪየት ሕብረትን አስጠንቅቆ የሶቭየት ሕብረት በበኩሉ ለኢትዮጵያ ትዕዛዝ አስተላለፈና የኢትዮጵያ ጦር ተገታ። አሁንም ካልረሳነው ሶማልያ በኢትዮጵያ ላይ ያደረገችውን ወረራ ከአበረታቱ አገሮች አንዱ አሜሪካ ነበር፤ ስለዚህ ጉዳይ በጊዜው በሰፊው ጽፌያለሁ። ከዚያ በኋላም ኢትዮጵያ የባሕር ወደብ እንድታጣ አሜሪካ በብዙ መንገድ ድጋፉን ሰጠ።

 

 

በደርግ ዘመን ሱዳን ከአሜሪካ ጋር ኢትዮጵያን ለመጥለፍ በተወዳጀችበት ጊዜ፣ ሊቢያ ደግሞ ሱዳንን ለመጥለፍ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር እሰጣለሁ ብሎ ኢትዮጵያን ሲያባብል ነበር። እሳትን የሚያነድድና የሚያቀጣጥል ዶላር፣ እሳቱን ለማጥፋት በመሞከር ላይ ይውላል እንጂ ሌላ ፋይዳ አይሠራም።

 

 

በአሁኑ ጊዜ አሜሪካ አለ ልማዱ ኢትዮጵያ ሶማልያን እንድትወርለት የፈቀደው፣ አንዳንድ የዋሆች እንደሚያስቡት ኢትዮጵያ ያጣችውን የቀይ ባሕሩን ወደብ፣ በሕንድ ውቅያኖስ ወደብ ለመካስ አይደለም፤ አጼ ኃይለሥላሴ ያጋጠማቸው ክፉ ምርጫ ከቤናድርና (የቀድሞ የሶማልያ ስም) ከኤርትራ ነበር፤ እሳቸው የፈለጉት ሁለቱንም ነበር። ዛሬ አሜሪካ ኢትዮጵያን የሚክስበትም ሆነ ዘላቂ ጥቅምዋን የሚፈልግበት አንድም ምክንያት የለም። ለአሜሪካ የኢትዮጵያ ጥቅም ሦስት ብቻ ይመስለኛል። አንዱ አልገብርም ያለውን ኤርትራን ለማስፈራሪያ ነው፤ ሁለተኛው ኢትዮጵያን ከእስልምና ጋር በዘላቂ ቅራኔ ለማጣመድ ነው፤ ሦስተኛው በይፋ እንደሚባለው አክራሪ የእስልምና ሽብርተኞች በሶማልያ ውስጥ እንዳይገቡ ለመከላከል ነው። ሁለተኛውና ሦስተኛው የተያያዙ ናቸው። ሦስቱም የአሜሪካ ዓላማዎች የኢትዮጵያን መሠረታዊና የዘለቄታ ዓላማዎች የሚቃረኑ ናቸው።

 

 

ለአሜሪካ ጥቅም ስትል ሶማልያን በመውረር ኢትዮጵያ የምታገኘው ጥቅምስ ምንድን ነው? መሣሪያና ስንዴ። በተረፈ ጉዳቱ፣ ሰፊና ዛሬ በሕይወትም ሆነ በአካል ከሚያስከትለው ጉዳትና በውስጥ ፖለቲካም ሆነ በውጭ በተለይ የጎረቤቶች ፖለቲካ ላይ ከሚያሳድረው ተፅዕኖ በላይ ለብዙ ዘመናት የሚቆይ የቆላ ቁስል ይሆናል የሚል ብርቱ ስጋት አለኝ። በገንዘብ በኩል የሚያስከትለውን የማላነሳው ምናልባት የኢትዮጵያ አይሆንም በማለት ነው። ከአካባቢው አገሮች መማር ይቻላል፤ ሶማልያ ለአሜሪካ ገብራ ምን አገኘች? ሱዳንስ? ፓኪስታንስ? በሰሜን በኩል በአንድ የከፋ ጦርነት ከወገኖቻችን ጋር ተፋጅተን ክፉ ቂምን አተረፍን፤ አሁን ደግሞ በደቡብ በኩል ከሌሎች ወገኖቻችን ጋር ተፋጅተን ሌላ ቂምን የምናተርፈው ማን ይድላው ብለን ነው? የአሁኑ ቂም ግን ይሰፋልም፤ ይጠልቃልም። የሶማልያን ድንበር ያልፋል። ስለዚህ ቶሎ መላ ሊፈለግለት ይገባል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ