Surma

(ኢትዮጵያ ዛሬ) አንድ የውጭ ሰው ይህን ፎቶግራፍ ሲመለከት፤ በሆነች አፍሪካ አገር ውስጥ በባሪያ አሳዳሪው ሥርዓት የተነሳ ፎቶግራፍ ሊመስለው ይችላል። ይህ ግን ትናንት በእኛው አገር፤ በኢትዮጵያ የተፈጸመ ነው።

ልክ የዛሬ ዓመት ነው በደቡብ ክልል ሱርማ ውስጥ መሬታቸውን ለመንግሥት “የሙስና" ፕሮጀክት ለሆነው የስኳር ፕሮጀክት “ያለ ካሣ ከመሬታችን አንነሳም” በሚል የዜግነት መብታቸውን ስለጠየቁ ብቻ፤ እንደ ውሻ አንገታቸው ላይ ገመድ ገብቶ በውርደት እንዲታሰሩ የተደረጉት።

ይህ ፎቶ ብቻውን ኢትዮጵያን እየመራሁ ነው የሚለውን ሥርዓት ለዜጎች ያለውን ክብር እንዲሁም በዜጎች ላይ ያለውን ንቀት የሚያሳይ ነው።

ይሁን እንጂ ይህን አድራጊው የህወሓት መንግሥት የብሔረሰቦችን ቀን በጭፈራ አክብሯል፤ ሊያውም ለአስራ አንደኛ ዓመት። የዜግነትን ክብር ቸል ያለና "የብሔረሰብን መብት" አክብሬአለሁ በማለት በማይዳሰስ እውነታ ውስጥ ራሱን የሚያመጻድቅ ሥርዓት፤ ህወሓት/ኢህአዴግ።

አፈቀላጤዎቹ፤ ”... ”የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል” ጠ/ሚንስትሩ በተገኙበት በሐረር ከተማ ”በደማቅ ሁኔታ” ተከብሯል” ብለውናል። ባለፉት አስራ ሁለት ወራት ብቻ፤ በአራቱም ማዕዘናት በ”ብሔር” ስም የበዓል ቀን የተመደበላቸው ኢትዮጵያውያን ”ብሔረሰባዊና ሕገመንግሥታዊ መብታችን ይከበርልን” በማለት፤ ከክልል እስከ የፌዴራሉ ሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ድረስ አቤት በማለታቸው ሳቢያ ተደብድበዋል፣ ታስረዋል፣ ... ተገድለዋል። በያሉበት ብሶታቸውን ያሰሙም እንዲሁ።

ክብር ለሌለው ነገር ”በዓል” የሚከበርባት ብቸኛዋ የዓለማችን አገር ኢትዮጵያ ስለመሆንዋ የሚያከራክር አይደለም። ከክቡሩ የሰው ልጅ ሕይወትና መብት ”ቀን” በልጦ የሚከበርባት ህወሓት/ኢህአዴግ የሚያስተዳድራት፤ ውዷ አገራችን።

ደርግ ከሚወቀስባቸው በርካታ ነገሮች አንዱ የአስረኛው የአብዮት በዓል ነበር።

ክብረ በዓሉን አስመልክቶ ለአልባሳት፣ ለኮፍያ፣ ለፖስተር፣ ለውሎ አበል፣ ለምግብ፣ ለውስኪ፣ ለትራንስፖርት ... የወጣው ወጪ እስካሁን አልተነገረንም። በሺህ የሚቆጠሩ ”የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች” ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ገድሎ፣ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩትን በእስርና በግርፋት እያሰቃዩ፤ በእነሱ ስም ”በዓል” ማክበር ምን ይሉታል? ... ”ደርግ”?

ዩኔስኮ እውቅና የሰጠውንና ለዘመናት ሲከበር የቆየውን የኢሬቻ በዓል ሊያከብር የወጣን፤ ቢበዛ ሊጮኽ የሚችልን ሕዝብ መውጫ መግቢያ አሳጥቶ፣ ወደገደል ወርውሮና በመቶዎች የሚቆጠሩትን ሕይወታቸውን ቀጥፎ፤ በማግስቱ ”የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል” ማክበር ትርጉሙ ምንድን ነው? ... ከበዓሉ ይልቅ የዜጎች መብት ይከበር! እንላለን።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ