ለ3 ነጥብ 8 ኪሎሜትር 243 ሚሊዮን ብር የወጣበት የሐረር መንገድ ተመረቀ
ኢትዮጵያ ዛሬ (ኀሙስ ኅዳር ፳፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. Dec. 8, 2016)፦ ህወሓት መራሹ መንግሥት ከሚታወቅበት ነገሮች አንዱና ዋንኛው በልማት ስም የሚመድበውን የህዝብ ገንዘብ ወደ ግለሰቦች ካዝና የማዛወር ችሎታው እንደሆነ በርካቶች በተደጋጋሚ ይተቻሉ።
ይህንን ትችት የሚሰነዝሩት ወገኖች እንደሚሉት ከሆነ፤ ለፕሮጀክቶች የሚመደበው በጀት ምንጩ ቢያንስ 75 ከመቶው ከውጭ ብድር ቢሆንም፤ የትየለሌ ገንዘብ ይመደብና ባልተጠና ወጪ ግለሰቦች ይቀራመቱታል።
እነዚሁ ወገኖች፤ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው ብለው ለምሳሌ የሚያቀርቡት ደግሞ በሐረር ትናንት የተመረቀው እና 243 ሚሊዮን ብር የፈሰሰበትን የሦስት ነጥብ ስምንት ኪሎ ሜትር መንገድ ነው። አንድ ኪሎሜትር 64 ሚሊዮን ብር ፈጀ ማለት ነው።
በ243 ሚሊዮን ብር ወጪ በከተማዋ የተገነባው የአስፋልት መንገድ ተመርቋል። እነዚሁ ተቺዎች “ከሐማሬሳ እስከ አራተኛ ድረስ የተገነባው መንገድ የጥራት ደረጃውም ምናልባት እስካሁን እንደታዘብናቸው እንደ ነቀምቴው አስፋልት መንገድ ስድስት ወር ሳይቆይ የሚፈርስ እንደማይሆን ምንም ማረጋገጫ የለንም” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ሐረር ለ፲፩ኛ ጊዜ በአገሪቱ የተከበረውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓልን በከተማዋ ያስተናገደች ሲሆን፤ ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝም በበዓሉ ላይ ተገኝተዋል።
“ከተማዋ 'የብሔር ብሔረሰቦችን የጭፈራ በዓል" በማክበር ላይ ስትሆን የመንገዱም በሩጫ መመረቅ ለዚሁ የፖለቲካ ፍጆታ መሆኑ ከዚህ ቀደም ያየናቸው የፕሮጄቶች አጨራረስ ምስክሮቻችን ናቸው” ሲሉ እነዚሁ ተችዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።