ምነው ጭካኔያችን በዛ?! ኧረ እንደሰው እናስብ

ቅዱስ እስጢፋኖስ በደቦ በድንጋይ ሲወገር
በቡድንም በተናጠልም የሚፈጸሙት የግድያ ተግባራት እንደ አገር አንገት የሚያስደፋን፤ እንደ ሕዝብ ወዴት እየመራን እንደኾነ በእጅጉ ሊያሳስበን እና ቆም ብለን እንድናስብ ያደርገናል
ኢትዮጵያ ዛሬ (ርዕሰ አንቀጽ) - በዕለተ ሰኞ ሚያዝያ 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ማኅበራዊ ሚዲያዎች እየተቀባበሉት የነበረው አንድ ምስል በአገራችን እየታየ ያለው ጭካኔ ልክ እያጣ ስለመኾኑ አመላካች ነው። በቻግኒ አንድን ሰው ከተሽከርካሪ አውርዶ በደቦ በድንጋይ መውገር? ይህ እንዴት ሊታሰብ ይችላል?
የተፈጸመው ድርጊት በጠራራ ፀሐይ ወለል ባለ አደባባይ ከመፈጸሙም በላይ፤ ኧረ የመንግሥት ያለህ! ብቻ የሚያስብል ሳይኾን እንደ ሰው እያጣነው ያለውን ሰብእና የሚያሳብቅብንም ጭምር ነው። “ሰው ተዘቅዝቆ ተሰቀለ” ከሚለው ዘግናኝ ድርጊት ድንጋጤ ሳንወጣ፣ ሰዎች በማንነታቸው ጥይት ብቻ ሳይኾን በቀስት ሲገደሉ የሰማነው ሰቅጣጭ ዜና ሳያንስ፤ ለመገመት የሚያስቸግሩ የግፍ ጭፍጨፋዎች ሰው በሰው ላይ ሲነሳ እንደ ሰው እያሰብን አይደለም ማለት ነው።
የሰው ሕይወት እንደ ቀልድ ያውም በአደባባይ መገደሉ ሳያንስ የአንድ ሰው ሕይወት ለማጥፋት በደቦ ጭምር መስፈር ችግሩን በአንድ አካል ላይ ብቻ የምናላክክበት አይኾንም።
በምንም መመዘኛ ቢኾን የሰው ሕይወት መጥፋት የለበትም ስንል፤ ሕግ መከበር አለበት ማለትም ነው። ሕግ የሚከበረው ደግሞ በአንድ ወገን ሳይኾን በሁሉም ሕብረተሰብ ነው። ለእንዲህ ያለው ተገማች ያልኾነ ድርጊት ሰዎች ድንጋይ ያነሱበት ምክንያት ምንም ይሁን ምንም “የደቦ ፍርድ” አደገኛነት ከምንም ጋር ሊወዳደር አይችልም።
ሰው ያውም ወገኑ ላይ የሚፈጽመው አሰቃቂ ግድያ እውን በዚህች አገር የሚፈጸም ነው ወይ? ያስብላል። በሚያሳዝን ሁኔታ ግን እየኾነ እና እያየነው ነው። ጁንታው ወያኔ ያበላ ያጠጣና ጋሻ የኾነውን የአገር መከላከያ ሠራዊት ከጀርባ በወጋበት ጊዜ፤ ጡት መቁረጡን፣ አስሮ መግደሉን፣ ገደል መክተቱን፣ … ስናስታውስ በቡድንም በተናጠልም የሚፈጸሙት የግድያ ተግባራት እንደ አገር አንገት የሚያስደፋን፤ እንደ ሕዝብ ወዴት እየመራን እንደኾነ በእጅጉ ሊያሳስበን እና ቆም ብለን እንድናስብ ያደርገናል።
የጭካኔው ልክ ካራ ያሳረፍንበትን ሰው መግደላችንን ለማሳየት በምስል ጭምር ይሁን በመውጣት መፈክራችን በራሱ እንደ ጀግንነት እየታየ መኾኑ የበለጠ ያማል።
በምንም መለኪያ ሰውን ገሎ መፎከር ክቡሩን የሰው ልጅ በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሎ አበጀው የሚል ዜጋ መፈጠሩ የዚች አገር ክፉ ገጠመኝ እየኾነ ከቀጠለ ነገ ያስፈራናል። ለዚህ የበቃነው ለምንድነው ካልን፤ እንደ አገር ትውልዱ እንዲወጋ የተደረገው ጽንፍ የያዘ ብሔርተኝነት ስለመኾኑ ባያጠያይቅም፤ ፈውሱ የሚገኘው ግን እንደ ሰው ስናስብ ነው። (ኢዛ)