እንተባበር!! የሚያዋጣን እሱ ብቻ ነው!!

ይህ ኢትዮጵያዊ በማይካድራ በአንድ ጉድጓድ ውስጥ የተጣሉ የበርካታ ወገኖቹን አስከሬን እየተመለከተ ነው። በርካታ ንጹሐን በየቦታው እየተጨፈጨፉ መኾኑ በእውነት ያሳዝናል። ኢትዮጵያዊ ባህልም አይደለም። (ፎቶ፣ ኤድዋርዶ ሶቴራስ፣ ኤኤፍፒ)
ኢትዮጵያ አገራችን ናት ካልን፤ ካለንበት አዙሪት እንውጣ! መንግሥት ገዳዮችን አደብ ያስገዛ፣ ለፍርድም ያቅርብ! መንግሥትም መኻሉን ካላረጋጋ ከውጭ ሊመጣ የሚችለውን ጥቃት ለመከላከል ይከብዳል
ኢትዮጵያ ዛሬ (ርዕሰ አንቀጽ) - አገር ከውስጥም ተወጥራለች። በአገር ውስጥ ለሰው ሕይወትና ክብር የስናፍጭ ቅንጣት ታክል ቁብ የሌላቸው ጉዳዮች እዚህም እዚያ የምንሰማው ግፍ ከልክ አልፏል። ላይመለስ የተሸኘው የሕወሓት ትርፍራፊዎች በየሸጡ ተሸሽገው ዛሬም የዚህ መንግሥትና ሕዝብ ጦስ ኾነው ትኩረት ለመሳብ እያደረጉ ያሉት ጥረት አገር ዋጋ እያስከፈለ ነው። የኢትዮጵያ ገጽታ ከውጭ እንዲጠለሽ የሚሠሩት ሴራ፤ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ሥራዎች ላይ እንዳያተኩር አድርጓል። ወዲህ ደግሞ ምርጫ የሚባለው ነገር ሌላው የአገሪቱ አጀንዳ ኾኖ ፖለቲካውን እያጋለ ነው።
የአገሪቷ የመጋቢት ወር የዋጋ ግሽበት ከ20 በመቶ በላይ መመዝገቡ ከሰሞኑ ይፋዊ መረጃ ይነገር እንጂ፤ የዋጋ ንረቱ የሕዝብም፣ የመንግሥትም ራስ ምታት ኾኗል። በአፋርና በሱማሌ ክልል አዋሳኝ ላይ ግጭት ተፈጥሮ የሰው ሕይወት ጠፋ፣ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ሰዎች ባልታወቁ ሰዎች ተደበደቡ፣ ተገደሉ የሚለውም ወሬ ጆሮ እያደማ ነው።
ነገሩን የከፋ የሚያደርገው ሕዝብ ከሚከፍለው ግብር ደምወዝ የሚቆረጠላቸው የሥርዓቱ ባለሟሎች የዚህች አገር አደጋ ናቸው ከሚባሉ አካላት ጋር አብረዋል መባሉ ነው
ብሔር ተኮር ፖለቲካው ከፈውስ ይልቅ ሲብስበት ስንመለከትም፤ ይቺ አገር ፍዳዋ በዛ ማለታችን አይቀርም። አሁን ላይ እነዚህ ችግሮቻችን ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው። አለፍ ብለን ስናስበው ከሰሞኑ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች የተፈጸሙና የግፍ ግድያዎች የክልሉ መንግሥት ላይ ጣት አስቀስሯል። ነገሩን በንግግር ለመፍታት የኦሮሚያና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ለምክር መቀመጣቸው መልካም ቢኾንም፤ በዚህ ሰዓት እንደ አገር ብዙዎችን የሚያስፈራው የአንድ ፓርቲ አካል ኾነው እርስ በርስ ሲካሰሱ መሰማቱ ነው።
አገር የማረጋጋት ኃላፊነት የተሰጣቸው የሁለቱ ትልልቅ ክልሎች ባለሥልጣናት ሊያውም የአንድ ፓርቲ አካላት ኾነው ጉዳያቸውን ለመፍታት በአደባባይ ተገናኝተው መከሩ ሲባል ግር ይላል። ይህ ድርጊት አሁን ላይ በአገራችን ካሉት ፖለቲካዊ ችግሮች አንዱ ኾኖ እንደማሳያ ሊቀርብ ይችላል። እንዲህ ላለው ነገር መላ ሳንሰጥ የውጭ ጠላቶቻችን ጥፍራቸውን አሹለው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ውጥረት ተጠቅመው ዳር ድንበር እስከ መድፈር የመድረሳቸው ነገር እጅጉን ይቆጫል።
በገዛ ሀብታችን መጠቀም አትችሉም የሚለውን አንደበታቸውን ከፍ ያደረጉት ከሰሞኑ መኾኑን ስናስብ፤ አገር ውስጥ ያለው ሽኩቻና ነገሮችን በአንክሮ ያለመመልከት ችግራችንን በመገንዘባቸው ነው።
ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ከደፈረች ውላ አድራለች። ከሰሞኑም በዶዘር መንገድ እስከመግመስ እና የሠራዊቷን እንቅስቃሴ ጠጋ ብላ እዩልኝ ማለትዋም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው።
በዓባይ ውኃና በህዳሴው ግድብ ዙሪያ በኪንሻሳ (ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ) የሦስቱ የተፋሰሱ አገሮች ድርድር የከሸፈው፤ ግብጽ እና ሱዳን ሸርበው በመጡት ሴራ ነው። ወዲህ ደግሞ በጋራ የጦር ልምምድ መጀመራቸው የሚነግረን ነገር አለ።
ስለዚህ በዚህ ወቅት ይቺ አገር ከትልቋ ኢትዮጵያ ይልቅ የሰፈር ማንነትን በሚያጐሉ አክራሪ ብሔርተኞች እና ጎጠኞች እየተወጋች መኾኑ፤ ለውጭ ጠላቶች በር እየከፈቱ መኾኑን እያወቁ እንኳን አደብ ሊገዙ አለመቻላቸው በቀጣይ ምን ይከተል ይኾን ብለን መሥጋታችን አይቀርም።
ሰው የራሱን ወገን እየገደለ፣ አገርን ለውጭ ጠላት እየሰጠ፣ አደርጋለሁ የሚለው ፖለቲካዊ ትግል በራሱ ስም የማይገኝለት በመኾኑ፤ ኢትዮጵያችን አደጋ ላይ ነች ብንል ስሕተት አይኖርም።
እነዚህ አካላት ለይቶላቸው ጫካ ገብተው፤ ሲመቻቸው ወጣ እያሉ በንጹሐን ላይ ቃታ መሳባቸው መገለጫቸው ሊኾን ቢችልም፤ ነገሩን የከፋ የሚያደርገው ሕዝብ ከሚከፍለው ግብር ደምወዝ የሚቆረጠላቸው የሥርዓቱ ባለሟሎች የዚህች አገር አደጋ ናቸው ከሚባሉ አካላት ጋር አብረዋል መባሉ ነው።
ከእነዚህ እውነታዎች እና ኢትዮጵያ አገራችንን በተመለከተ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የምንሰማቸውን የሚጐረብጡ ድርጊቶች ለማስቆም፤ ሁሉም መተባበር የሚኖርበት መኾኑን ልንገነዘብ ይገባናል። ስለዚህ አገራችን ያለችበትን እና እየገጠማት ያለውን ፈተና ለማለፍ የዜጐች በአንድነት መሰለፍ እና የፖለቲካ ድርጅቶች ኃላፊዎች ቅንነት የተሞላበት አስተሳሰብ እና እርምጃ የግድ ይሻል።
የውጭ ጠላቶች ከአገር ድንበር ላይ እሳት እየቆሰቆሱ የሚገኙት፤ እኛ ኢትዮጵያውያን በመንደር እና በቀዬ የቤት ሥራ ላይ ተወጥረን እርስ በእርሳችን እየተላለቅን በመኾናችን ነው። ካለንበት አስፈሪ ቅዠት እና አዙሪት በጊዜ መውጣት ካልቻልን፤ መጪው ጊዜ ከአሁኑ ይብሳል እንጂ በፍጹም አይሻልም።
ኢትዮጵያ አገራችን ናት ካልን ግን፤ ከዚህ አዙሪት እንውጣ! መንግሥትም መኻሉን ካላረጋጋ ከውጭ ሊመጣ የሚችለውን ጥቃት ለመከላከል ይከብዳል። ይህ ከታወቀ መንግሥት ገዳዮችን አደብ ያስገዛ፣ ለፍርድም ያቅርብ! የውጭ ጠላቶቻችን ገፍተው ሊመጡ ከቻሉ፤ እሱም ይዘጋጅ፣ ሕዝብንም ያዘጋጅ፣ ግድቡንም ያጠናቅቅ!!
እንተባበር!! የሚያዋጣን እሱ ብቻ ነው!! (ኢዛ)