Wake up!

ኧረ ንቃ!

ከዘር፣ ከኮታ፣ ከማግለል የጸዳ እውነተኛ ዲፕሎማሲ ላይ የበለጠ መሥራት ይጠበቅበታል

ኢትዮጵያ ዛሬ (ርዕሰ አንቀጽ) - የዲፕሎማሲው መስክ እጅግ ብዙ ሥራዎች ይቀሩናል። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያን በቅርቡ የሚገልጹ ዲፕሎማቶችን ማፍራት አለመቻሉ አንድ ምክንያት ነው።

ይህንን በዓለም ደረጃ የአገራችን ክብርና ዝና የሚያጐሉ፣ የኢትዮጵያን ፍላጐቶች በአግባቡ የሚገልጹ ዲፕሎማቶች ቢኖሩን እንኳን ልንጠቀምባቸው ባለመቻላችን መጠቀም አለመቻላችን ሌላው ግድፈታችን ነው።

ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚኾነው በተለያዩ አገሮች የሚሾሙ አምባሳደሮችና በኤምባሲው ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች የሚመደቡ ሠራተኞች ለቦታው ብቁ መኾናቸው ታምኖ ወይም ተረጋግጦ ሳይኾን፤ በፖለቲካ አመለካከቻው የሚመዘኑ በመኾኑ ነው። እንዲሁም የዘር ስብጥርን እናሟላ በሚል ጭፍን የኮታ ድልድል የአገሪቱን ጐድቷል። ይህ ብቻ ሳይኾን በአገር ቤት በተለያዩ የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ተሹመው በሥራ አፈጻጸማቸው ዓይንህ ላፈር የተባሉ፣ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ፣ ይህም በመኾኑ ከሥራ የተሰናበቱ፣ የፖለቲካ ሹመኞችን ከሥልጣን ገሸሽ ሲደረጉ “አምባሳደር” ኾነው እንዲሾሙ ሲደረግ ነበርና በዲፕሎማሲው መስክ ሊሠራ የሚገባው ሥራ እንዳይሠራ ኾኗል።

ይህ መንግሥት ሲከተለው የነበረ አሠራር አገርን ዋጋ ያስከፈለ ስለመኾኑ በግልጽ የሚታወቅ ነው። ችግሩ አምባሳደሮቹም ኾኑ ዲፕሎማቶቹ ኢትዮጵያን በአግባቡ ባለመግለጻቸውና በሌሎች አገሮች ያለንን ከበሬታ ዓለም እንዲያውቀው አለማድረጋቸው ብቻ ሳይኾን፤ የዲፕሎማት ማዕረግ ተሰጥቷቸው ለሚሾሙና ለሚመደቡ ግለሰቦች አገሪቷ በሌላት የውጭ ምንዛሪ እየከፈለችው መቆየቷም ሌላው ኪሳራ እንደኾነ ልብ ሊባል ይገባል።

ዛሬ በሽብርተኝነት የተፈረጀው የሕወሓት ቡድን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተበዳይ በመምሰል ያካሔዳቸው ምንም የእውነት መሠረት የሌላቸውን ፕሮፖጋንዳዎች፤ ሐሰት መኾኑን በመግለጽ እውነታው ይህ ነው በማለት በግልጽ ባለመሞገታቸው፤ ኢትዮጵያ ላይ በተለይ ምዕራባውያን እያሳደሩ ያሉትን ተጽዕኖ ምሳሌ አድርገን ልንጠቅስ እንችላለን።

አንድ ሁለት ከሚኾኑ አምባሳደሮች ሌላ፤ በሐሰት ኢትዮጵያ ላይ ሲነሱ ይህንን የሚያከሽፍ ሥራ ባለመሥራታቸው ይህንን ለማስተካከል አገር ብዙ እንድትደክም አድርጓል።

በመኾኑም በዲፕሎማሲው መስክ የሚታየው ክፍተት በብርቱ ሊታሰብበት ይገባል የምንለው፤ በቅርብ የገጠመን የተለያዩ አገራዊ ችግሮች አንዱ መንሥኤው ይኸው ጠንካራ ዲፕሎማቶችን በተገቢው ቦታ አለመመደብና አብዛኛው ሹመትም ፖለቲካዊ ኾኖ መገኘቱ ጭምር ነው።

ሰሞኑን በጸጥታው ምክር ቤት በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ለመነጋገር ሲቀመጥ በቦታው የነበሩ የኢትዮጵያ ተወካዮች ያስገኙልንን ድል ስንመለከት ደግሞ፤ እንዲህም መሥራትና አገርን ማኩራት እንደሚቻል ያመለክተናል።

አገሪቱ ስለ ኢትዮጵያ የሚሞግት አጥታ ሳይኾን፤ የዲፕሎማሲ ሥራ የገባቸውና መሥራትና ውጤት ማምጣት የሚችሉ ዲፕሎማቶችን መንግሥት አፈላልጐ መሾም ያለመቻሉንም ያመላክታል።

ስለዚህ ኢትዮጵያ እንዲህ ያለ የዲፕሎማሲ ሥራ የሚሠሩ ብቁ ሰዎች በየኤምባሲዎቻችን ያስፈልጉናል። ይህ ካልኾነ አሁንም እውነት ይዘን እንኳን አሸናፊ የምንኾንባቸው መድረኮች አይኖሩንም።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ግን ግብጽን በዓለም መድረክ አሸናፊ ያደረጉንን አጋጣሚ ብናገኝም፤ በተለይ ከዓባይ ወንዝና ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ግብጽ እየሠራች ካለችው ዓለም አቀፋዊ ዘመቻ እንዲሁም በአገሯ ያሰረጸችው ትርክት፤ ከኢትዮጵያ በእጅጉ ከፍ ያለ ነው።

የገዛ ወንዛችንን ግብጾች የራሳቸው ስለመኾኑ ዜጐቻቸውን ቀርጸዋል። የዓባይ ዋነኛ ባለቤቶች እኛ ኾነን ሳለ ባለቤቱ እነሱ መኾናቸውን ሌላውንም አገር ዜጋ በማሳመን ዘመናትን ዘልቀዋል። ሌላው ቀርቶ በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሳይቀር “ዓባይ የግብጽ ነው” ተብለው የተማሩ እንዳሉ አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

እኛስ? ካልን፤ ምንም አለመሥራታችንን በብዙ መንገድ መግለጽ እንችላለን። ስለ ዓባይ በበቂ ሁኔታ ካላስተማርንም ዓባይ ምን ማለት እንደኾነ ሌሎች እንዲያውቁ የሠራነው ሥራ ኢምንት ነው። ዓባይ የተፈጥሮ ብታኝ ስለመኾኑ በትምህርት ቤቶቻችን አላስተማርንም ወይም ግብጽ በምታደርገው ልክ ለዜጐቻችን አላደረስንም። በአገር ጉዳይ ሁሉም ዲፕሎማት ኾኖ እንዲሠራ በማድረጉ ረገድም ብዙ የሚቀረን መኾኑን መዘንጋት የለበትም።

ስለዚህ ኢትዮጵያ የተሻለች አገር ኾና ትቀጥል ዘንድ በዲፕሎማሲው መስክ ያለውን ክፍተት ለመድፈን አጠቃላይ አሠራርን መቀየር ቀዳሚ ተግባር ሊኾን ይገባል። ከሌሎች አገሮች ጋር በሚያገናኘን እንደ ዓባይ ወንዝ ያሉ ጉዳዮችን ደግሞ፤ ዜጐች ከታች ጀምሮ የሚያውቁበት የትምህርት ሥርዓት መዘርጋት፣ ለዚህም መትጋት ያስፈልጋል። ሁላችንም በጋራ ጉዳዮቻችን አንድ ዐይነት ቋንቋ እንናገር ዘንድ ትውልዱ ላይ አብዝቶ መሥራትና አገሩን በአግባቡ የሚገልጽ ዜጋ ማፍራት የግድ ይለናል።

ይህ የሚኾነው ደግሞ በዲፕሎማሲው መስክ ጠንካራ ባለሙያዎች እንዲወጡ ከታች ጀምሮ መሥራት፣ ተተኪዎችን ማፍራት እና የዲፕሎማት ሹመት በተግባር በሚታይ ሥራው እንዲመዘን ማድረግን ይጠይቃል።

በእርግጥ ባለፈው ሳምንት በጸጥታው ምክር ቤት ድል ተቀዳጅተና፤ ይህ ድል ግን ዘላቂ አይደለም። ከዚህ በኋላ ገና ብዙ ፈተና ይቀረናልና፤ ከወዲሁ መንግሥትም ኾነ ሕዝብ በዲፕሎማሲው መስክ የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል። በተለይ መንግሥት ከተኛበት ነቅቶ፣ ከዘር፣ ከኮታ፣ ከማግለል የጸዳ እውነተኛ ዲፕሎማሲ ላይ የበለጠ መሥራት ይጠበቅበታል! (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ