Unity is Power

አንድነታችን ኃይላችን ነው!

ከከፋፋይ አመለካከቶች በመራቅ ኢትዮጵያዊነታችንን እናስቀድም!!

ኢትዮጵያ ዛሬ (ርዕሰ አንቀጽ) - የኢትዮጵያን ፈተና ያባባሱ በርካታ ሁኔታዎች ለዓመታት ተስተናግደዋል። እንደ አገር ያጋጠሙ ችግሮች ውጫዊም ውስጣዊም ኾነው ሲገኙ ደግሞ ፈተናው ይበረታል። ኢትዮጵያ በረዥም ታሪኳ ውስጥ በርካታ ፈተናዎችን አልፋ ዛሬ የደረሰች ቢኾንም፤ ዛሬም አንድነቷን የሚፈታተኑ፣ እንድትበታተን ተግተው የሚሠሩ እንደ ሕወሓት ያለ አደገኛ ቡድን በቅሎባት ይህንን ለመንቀል ትግል ውስጥ ተገብቷል።

ወትሮም ለኢትዮጵያዊነት ደንታ ያልነበረው ይህ ቡድን የውጭ ወራሪ እንኳን ያደርጋል ተብሎ በማይታሰብ ደረጃ በግልጽ ጦር ሰብቆ ኢትዮጵያ ካልፈረሰች አልተኛም ማለቱ ነው።

እነዚህ በጽንፈኝነትና በዘረኝነት የታወሩ ኢትዮጵያ የራሴ የምትላቸው ጥቂት ልጆችዋ ተቧድነው ሊያፈርሷት መነሳታቸው፣ ወቅታዊውን ፈተናዋን የተለየ ያደርገዋል። ሕወሓት ይህንን ለመፈጸም ዘግናኝ የሚባሉ ድርጊቶችን እየፈጸመ፤ አሁን ላለበት ደረጃ ሲደርስ ቡድኑ ኢትየጵያን ሲመራ እንደነበር ሁሉ እንድንጠራጠር ያደርጋል።

ወትሮም ቢኾን በዘርና በብሔር የተቃኘ ፖለቲካ ፍጻሜው አደገኛ ሊኾን እንደሚችል የታወቀ ቢኾንም፤ አገር ለማፍረስ እስከመማማል እና “ኢትዮጵያ ትውደም!” ብሎ ዛሬ እንደ ሕወሓት ያለ ቡድን እስከማየት ደርሰናል።

ይህ ዓይን ያወጣ አደገኛ የሕወሓት አካሔድ የቱንም ያህል አገር እያደማ ቢኾንም፤ ፍጻሜው በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት መሸነፉ አይቀሬ ነው። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከ ዳር ሕወሓትን ወደ መቃብር ለመውሰድ ያሳዩት ትብብር የኢትዮጵያን አሸናፊነት ከወዲሁ ያረጋገጠ ነው።

ይህ የማይቀረው የኢትዮጵያውያን ድል፤ የሕወሓትን ግብዓተ መሬት ለመፈጸም ብቻ ሳይኾን እርሱ የዘራውና እንደ አገር ለዘመናት ነቀርሳ የኾነው በዘር ላይ የተመሠረተ ፖለቲካችንንም የሚያከስም በመኾኑ፤ ድሉ ድርብ እንደሚኾን ይታመናል።

ሕወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የከፈተውን ጦርነት ለመከላከል ለተደረገው አገራዊ ጥሪ የተሰጠው ምላሽ የሚያሳየን ኢትዮጵያ የማትፈርስ መኾኑን ብቻ ሳይኾን፤ ለዘመናት እንዲከፋፈል ብዙ ሲሠራበት የቆየው ሕዝብ ሴራውን በመበጣጠሱ ጭምር ነው።

ኢትዮጵያውያን ወትሮም ቢኾን በአገር ጉዳይ ላይ የማንደራደር ስለመኾናችን የሚታወቅ ነው። በሕወሓት ስሌት ግን በዚህ ወቅት ኢትዮጵያውያን ተባብረው ኢትዮጵያን ለማዳን እንደማይችሉ ቢኾንም፤ ይህ መርዛማ አስተሳሰብ ግን ያለመሥራቱና ዜጐች ለኢትዮጵያ ዘብ መቆማቸውን ማረጋገጣቸው ራሱ እንደ ትልቅ ድል የሚወሰድ ነው።

የሕወሓት የቀደመ እሳቤ አሁንም ኢትዮጵያ ትፍረስ ብሎ የጀመረው ጦርነት የቱንም ያህል ዋጋ ቢያስከፍል እንኳ፤ ኢትዮጵያ አሸናፊ መኾኗ አይቀርም የሚባልበት የጠነከረ እምነት እንድንይዝ የሚያደርገው፤ ኢትዮጵያውያን በአንድነት መቆማቸው ነው። አሸናፊነታችን አንድነታችን ስለመኾኑ ይህ ጥሩ ማሳያ ነው።

ኢትዮጵያውያን ትናንትም፣ ዛሬም ኾነ ነገ ያሸነፍነውና የምናሸንፈው ልዩነታችንን አስወግደን እንደ ኢትዮጵያዊ በመቆማችን ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያዊነታችንን እናጠንክር የምንልበት ብርቱ ምክንያት አሸናፊ ስለሚያደርገን ጭምር ነውና አንድነታችንን አጠንክረን እንዝለቅ።

ይህ ከኾነ ጠላትን በጋራ በመመከት የምናስመዘግባቸው ድሎች በሌሎች ዘርፎችም በጋራ የምናደርገው ርብርብ ለውጤት ያበቃናል። አገራችንን በእድገት ጐዳና ላይ ያራምዳል። ጽንፈኝነትን እና ዘረኝነትን ይቀብራል። የተሻለች አገር ለቀጣዩ ትውልድ እንድናስረክብ ያደርገናልና አንድነታችን ኃይላችን እና የድላችን መሠረት መኾኑን በማወቅ እንትጋ። ከከፋፋይ አመለካከቶች በመራቅ ኢትዮጵያዊነታችንን እናስቀድም!! ያኔ ጠላትን ቀድመን ማሸነፋችንን ያረጋግጥልናል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!