ልዑልሰገድ (ከአቢሲኒያ) This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

“ማንም ሰው ከሕግ በላይ አይደለም” ይሄን ማለቱን የሰማነው አንድ የሕግ የበላይነት ባለበት ሀገር የሚሠራ እና እውነተኛ ዳኛ ቢሆን አያስገርምም ነበር። እንዲህ የተባለውም በሕግ ፊት ከፍርድ በፊት ንፁኅ ሆኖ የመገመት መብቱ ታውቆ፣ በነፃ የመከራከር መብቱ ተጠብቆ፣ ሁሉም ማስረጃዎቹ ተመዝነው ፍትህ ለተሰጠው ሰው ቢሆን ዜና መሆኑ ይቀራል።

 

“ማንም ሰው ከሕግ በላይ አይደለም” ሲል የተናገረው የወያኔው ፍርድ ቤት ፍትህ ገዳይ “ዳኛ” ተብዬ ልዑል ገ/ማርያም ለቴዲ አፍሮ በመሆኑ ነው እብሪት የምለው። ይህን ካድሬ እና እሱን መሰሎች በፍትህ አደባባይ ከወያኔ አለቆቻቸው ጋር እየተሻረኩ እንዴት ፍትህን እየገደሉ እንደኖሩ ህዝቡ አሳምሮ ስለሚያውቅ ለሰሞኑ ዲስኩር ጆሮ የለውም።

 

ቴዲ እነሱ ሕግ ፊት የቆመው በፈጠራ መሆኑ ቢታወቅም፤ ወያኔ ለዚህ የፈጠራ ክሱ እንኳን በቂ ሐሰተኛ ምስክር እና በቂ የፈጠራ ማስረኛ ሲያጣ ዳኛ ልዑል ገ/ማርያም የጎደለውን እየሞላ፣ የዓቃቤ ሕግን ቃል ብቻ እያዳመጠ፤ የመለስ ቀኝ እጅ መሆኑን አስመስክሮ ቴዲን በስድስት ዓመት እስር እና 18 ሺህ ብር ቅጣት በመጀመሪያው ውሳኔ በየነ።

 

ይህ ሰው በድምፃዊው ብቻ ሳይወሰን በጋዜጠኞች፣ በጠበቃ እና በፍርድ ቤት ታዳሚዎች ላይ ማስፈራሪያ፣ ቅጣት እና ወከባ በሕግ ስም ሲፈጽም የነበረ ነው። ቴዲ ያመክሮ ጥያቄውን ሲያቀርብ ለዚህ ነው ወደዚሁ ሰው ተመርቶ በወያኔ ዕቅድ መሰረት በሁለት ዓመት ገደብ የተፈታው። ይህ ፍትህ ገዳይ ግለሰብ ለአመክሮ “ግምገማ” በተሰኘው ስላቅ ላይ ባደረገው ዲስኩር “ማንም ሰው ከሕግ በላይ አይደለም … መልካም ዕድል ይግጠምህ!” ማለቱ ዜና ሆኗል።

 

በሕግ ፊት ሁሉም እኩል የሚሆንበት ሥርዓት ቢኖር በፍትህ አደባባይ ላይ ፍትህን የገደሉት ዳኛ ልዑልና ጓደኞቹ፣ ፍትህን እና ንፁኀንን በአደባባይ በጥይት ያስፈጁት አለቆቹ በአንድነት ቃሊቲ በገቡ ነበር። ቴዲም ሆነ ብርቱካን እንዲሁም ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች ላለፉት 18 ዓመታት በሕግ ስም የበቀል ሰለባ ባልሆኑ ነበር።

 

ከዓመታት በፊት ሟቹ የመብረቅ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ወርቁ አለማየሁ በጊዜው የከፍተኛው ፍ/ቤት ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ይቀርባል። የተከሰሰው ወያኔ የመጀመሪያዎቹን “ጄነራሎች” ከብዙኀኑ ህዝብ ደብቆ ሾሞ ወሬውን አፍኖት ስለነበር፤ “በረኸኞቹ ያለወታደራዊ ሣይንስ በከፍተኛ ማዕረግ ተንበሸበሹ” በሚል ርዕስ ባወጣው ዜና ነው። በዜናው የተሿሚዎቹን ዝርዝርና ያላቅማቸው የተጫነላቸውን “ማዕረግ” ዘርዝሮ ለህዝብ አቀረበ። የቀረበው የነፃ ፕሬስ ጋዜጠኞችን፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪዎችንና አባላትን እንዲሁም ሥርዓቱ ያሰጉኛል ያላቸውን በመቅጣት ከሚታወቁት “ዳኛ” ተብዬዎች ዋነኛ ከሆነው ልዑል ገ/ማርያም ያለበት ችሎት ነበር።

 

ጋዜጠኛው ዜናው እውነት መሆኑን ወንጀል አለመፈጸሙን ገለጸ። በዚሁ ዜና በምርመራ ስም በፓሊስ ጣቢያ ለረጅም ጊዜ ታስሮ መንገላታቱም አግባብ አለመሆኑን አስረዳ። በጊዜው መከላከያ ማስረጃ እንዳለው ይገልፃል። በዚህ ጊዜ በቁጣ ይህ ዳኛ ተብዬ “ምንድነው መከላከያ ማስረጃህ?” ብሎ ይጮኻል። ተከሳሹ “መከላከያ ማስረጃዎቼ የተሾሙት ጄነራሎች ከየትኛው ወታደራዊ ሣይንስ ተመርቀው እንደወጡ ቀርበው ያስረዱልኛል …” በማለት፤ “… ሜ/ጄነራል ፃድቃን ገ/ተንሳይ፣ …” እያለ መዘርዘር ሲጀምር ይህ ፍትህ ገዳይ አላስችል ብሎት “ዝምበል አንተ እነሱ እንዳንተ ሥራ ፈት አይደሉም። እዚህ ሊመጡልህ አይችሉም” ይልና በቁጣ ያቋርጠዋል።

 

የቀኝ ዳኛ የነበረችው ወጣት ጣልቃ ገብታ “መከላከያ ምስክር መጥራት መብቱ ነው። እነሱም ለምስክርነት ከተጠሩ ይቀርባሉ። ማንም ሰው ከሕግ በላይ አይደለም” ትላለች። ችሎቱ ፍጥጫ ነገሰበት። ልዑል የሚችለውን ተሳድቦ ሌላ ቀጠሮ ሰጠ። ዳኛዋ ከዚያ በኋላ በዚያ ችሎት አልታየችም። ወያኔ ዘግይቶ ሓየሎም ሲገደል ወያኔ ሹመቱን ሳይወድ ይፋ አድርጎ አወጣ። ጋዜጠኛው ቢቸግረው “ጄነራሎቹ” አይቀርቡም ከተባለ ወያኔ እራሱ ያወጣው ዝርዝር በማስረጃ ይቅረብ ሲልም ሊቀበለው አልፈቀደም። ለወያኔ “ፍትህ” ማለት ይህ ሲሆን፤ ለዳኛ ተብየው ልዑል ገ/ማርያም ደግሞ “ሕግ” የወያኔ ጠላቶች የተባሉትን ሁሉ ያለምህረት መቅጫ የበቀል መሣሪያ ነው።

 

ሌላ ጊዜ ይኸው ፍትህ ምን እንደሆነ የማይገባው ግለሰብ በመርካቶ አንዋር መስጅድ የወያኔ ወታደሮች በጠራራ ፀሐይ የፈጸሙትን ጭፍጨፋ ያጋለጡ እና ዜናውን የዘገቡ ጋዜጠኞችን ጉዳይ ያያል። በጋዜጠኞቹ ላይ የቀረበው ክስ ባደባባይ በመስጅድ የተደረገውን ጭፍጨፋ ሽምጥጥ አድርጎ “ሐሰተኛ ወሬ በማሰራጨት” የሚል ነበር። የሚገርመው በዚያው ችሎት ብጥብጡን አስነስታችኋል ብሎ ወያኔ እነ አወል ረጃን አስሮ ያቀርብ ነበር።

 

ለልዑል ገ/ማርያም አንዱን “ሐሰተኛ ወሬ ፃፍክ”፣ ሌላውን “ብጥብጥ አስነሳህ” ብሎ ለመፍረድ ቀላል ነው። በዚያ ምክንያት ሁለት ዓመት ከተፈረደበት ጋዜጠኛ ሠለሞን ገ/አምላክ ሲኖር እነ አወል ረጃ ደግሞ ሞቅ ያለ የእስር ዘመን ተወሰነባቸው።

 

ዳኛ ልዑል ገ/ማርያም በቴዲ አፍሮ ላይ በቂ ማስረጃ አለመቅረቡ፣ ምስክሮች የተምታታ ምስክርነት መስጠታቸው፣ በመኪና አደጋ ሞተ የተባለው ግለሰብ የሞተበት ጊዜ እና ቴዲ ገጨ የተባለበት ቀን አለመገናኘት፣ የሬሳ ዋና መርማሪ እያለ በሌላ ዶ/ር በተጽዕኖ ፖሊስና የሆስፒታል አስተዳደር “ሞተ” ያሉበትን ጊዜ አጽፈው ማምጣታቸው ቢመሰከርም ጉዳዩ አልነበረም።

 

የአንድ ሰው በሕግ ፊት የመዳኘት መብት በሌለበት ሀገራችን ወያኔ በፍትህ ስም የጠላውን ይቀጣል፣ በመሰለው ላይ ሞት ይፈርዳል። ወዳጆቹን ደግሞ እየገደሉም እየዘረፉም ይሾማል።

 

በ1993 ዓ.ም. ሚያዝያ ወር የአዲስ አበባ ተማሪዎች የአካዳሚክ ነፃነት ጥያቄ ስላቀረቡ በወያኔ ወታደሮች ተከበቡ፣ ተደበደቡ። ህዝቡ የልጆቹ መከራ አስቆጥቶት ተቃውሞውን አሰማ። በጊዜው በአንድ ጀንበር ከ40 በላይ ንፁኀን ተገደሉ። ዶ/ር ብርሃኑን እና ፕሮፌሠር መስፍንን ጨምሮ በርካታ ተማሪዎች፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪዎች እና በተለያየ ደረጃ ያሉ ዜጎች ታሰሩ። ከታሰሩት አንዱ የሆነው የቀድሞው የኢዴፓ አመራር አባል አቶ ታምራት ታረቀኝ የታሰረበት ጠፋ።

 

ቤተሰቦቹ አካልን ነፃ የማውጣት ክስ መሰረቱ። ጉዳዩ የሚታየው አራዳ ፍ/ቤት ሦስተኛ ፍ/ብሔር ችሎት ነበር። በጊዜው ችሎቱን የዳኙት ከምርጫ 97 በኋላ ምርጫውን በሚመራው ድርጅት በገለልተኝነት በመታዘቡ ከቅንጅት መሪዎች ጋር ታስሮ የነበረው ነፃነት ደምሴ እና አንድ ባልደረባው ነበሩ። የታሳሪውን ጉዳይ ፖሊስ ሲጠየቅ፤ “የት እንዳለ አላውቅም” አለ። በወቅቱ የፍትህ ሚኒስትር የነበረው አቶ ወረደወልድ ወልዴ ቀርቦ እንዲያስረዳ ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ ይሰጣል። ሚኒስትሩ ከፍ/ቤት በላይ መሆኑን ስለሚያውቅ በቀጠሮው ሳይቀርብ ቀረ። በድጋሚ ተጠራ። የፍርድ ቤቱን ቀጠሮ ያላከበረው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ስለነበረው መሆኑን ገለፀ። ይህ ሲሆን ለፍርድ ቤቱ አላሳወቀም። ፍ/ቤቱ ታስሮ ይቅረብ ቢልም ሳይታሰር ተኩራርቶ ቀረበ። ጉዳዩን ወጣቶቹ ዳኞች ቀኑን ሙሉ ሲመረምሩ ቆይተው አመሻሹ ላይ ባንድ ወር እስራት እንዲቀጣ ፈረዱበት። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በጊዜው እዚያ ችሎት ነበር።

 

የፖሊስ አዛዦች ፍርድ ቤቱ እሰር ያላቸውን ከማሰር ይልቅ መናደድ እና መቆጣትም ቃጣቸው። ተራወጡ። ስልክ ተደወለ ሬዲዮ ተደረገ። ሳይዘገይ መልሱ መጣ። ከሥራ ሰዓት ውጭ ውሳኔ የተሰጠበት ፋይል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ተወሰደ። ሚኒስትሩ እስሩ ቀረላቸውና በገደብ ተባለ። ወያኔ ከወደደህ አትታሰርም። ወያኔ የሚፈልጋቸውን የሚቀጡለትን ዳኞች ሲሾም ሲሸልም የሕግ የበላይነት ይከበር ያሉትን ደግሞ ከፍርድ ቤቱ በየጊዜው አባረረ። እንዳንዶቹም ዛሬም ድረስ እንደብርቱካን የበቀል ሰለባ ሆነዋል።

 

የቴዲ ጉዳይ በወያኔ የተወሰደ የበቀል ርምጃ መሆኑን ሀገር ቢያውቀውም ያለ ምንተ እፍረት ለማደናገር የሕግ ሽፋን ለመስጠት ነው ሰሞኑን “ማንም ከሕግ በላይ የለም” እና “መልካም ዕድል!” አሉ የሚለው ማደናገሪያ ጎልቶ እንዲሰማ የተፈለገው።

 

ቴዲ ለዚህ ነው ፍትህ በሌለበት ፍርድ ቤት ስድስት ዓመት እስራት እና 18 ሺህ ብር ቅጣት ተፈርዶብሃል ተብሎ የቅጣት ማቃለያ ሲጠየቅ “በሐቅ ለማይሠራ ፍርድ ቤት የማቀርበው የቅጣት አስተያየት የለም” ያለው።

 

ልዑል ገ/ማርያም ዛሬ “ከሕግ በላይ የሚሆን የለም” ከሚለው ባዶ ጨኸቱ አስከትሎ “መልካም ዕድል” ከሁለት ዓመት ገደብ ጋር መርቆ መሸኘቱ የወያኔን የበቀል ጥም እንዳልረካ የሚያሳይ ነው። ገደቡ ማስፈራሪያና በተፈለገው ሰዓት ለማሰሪያ ቅድሚያ ማረጋገጫ ለማስቀመጥ ነው።

 

ልዑል ገ/ማርያምን የመሰሉ “ዳኛ” ተብዬዎችን ዛሬ ህዝቡ “የፍርድ ቤቱ አጋዚ” የሚል መጠሪያ ሰጥቷቸዋል። የአጋዚ ወታደሮች በመለስ ትዕዛዝ ንጹኀንን በግፍ ተኩሰው እንደገደሉ እነዚህ “ዳኛ” ተብዬዎችም በፍርድ ቤት መሽገው የወያኔን የበቀል ፍላጎት ለማሳካት በፍትህ ስም ፍትህን ይገድላሉ። ለዚህ ነው ህዝቡ የሚገባቸውን ስም ያወጣላቸው።

 

ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ፤ አቶ መለስ የወያኔ ጓዶቹን ሳይቀር ደብቆ ፓርላማ ተብየውን ከመጤፍ ሳይቆጥር አልጀርስ ላይ ሄዶ ይግባኝ የሌለው ፍርድ ይሰጠኝ ብሎ ሲስማማ አብረውት ከሄዱት ጥቂት አጋሮቹ ልዑል ገ/ማርያም አንዱ ነበር። ሰውዬው በይፋ ያልተሾመ ሕግ የማያውቀው የአቶ መለስ ሕግ አማካሪ ነው። ለዚህም ነው የበቀል አርጩሜውን መስበቅ ሲፈልግ የፈጠራ ክሶቹን ከሚያዩለት “ዳኞች” ግንባር ቀደሙ ልዑል የሆነው።

 

ለወያኔ መሪዎች እና ልዑልን ለመሰሉ ፍትህ ገዳይ “ዳኛ” ተብዬዎች ቴዲ አፍሮ ላይም ሆነ ህዝቡ ላይ በፍርድ ቤትም ይሁን በየትኛውም መድረክ አትትፉ፤ መትፋት ያስነውራል እንበላቸው።

 

ልዑልሰገድ (ከአቢሲኒያ) This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ