የኛዋ ብርቱካንስ? (ፍቅሩ ይበልጣል)
ፍቅሩ ይበልጣል This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
መደበኛ የሥራ ሰዓቴን ጨርሼ እንደተለመደው ወደቤቴ አመራሁ። የቤቴን በር ከፍቼ ስገባ ልጆቼ ተሯሩጠው የተለመደ አቀባበላቸውን ካረጉልኝ በኋላ እኔም ሳም ሳም አድርጌያቸው ሁሌም አረፍ የምልበት ሶፋ ላይ ዝርግፍ ብዬ ቁጭ አልኩ። ዘወትር የምገባበት ሰዓት የምሽቱ ዜና የሚሰማበት ጊዜ በመሆኑ የቴሌቪዥኑን ጣቢያ መቀያየሪያ አንስቼ የዕለቱ ዜና የሚገኝበት ላይ ለመቀየር መነካካት ጀመርኩ።
ወዲያውም የምፈልገውን ጣቢያ አግኝቼ ማዳመጥ ስጀምር ‘የዕለቱ ሰበር ዜና’ ያበስረው የነበረው ሁለት የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ጋዜጠኞች ዩና ሊ እና ሎራ ሊንግን መፈታትን ነበር። ሁለቱ ጋዜጠኞች በሰሜን ኮሪያ አምባገነን መንግሥት ታግተው ከመጋቢት ወር ጀምሮ በ12 ዓመት የከባድ ጉልበት እስራት ተፈርዶባቸው በእስር ላይ ነበሩ። የታሰሩበትም ምክንያት በቻይና በኩል በሕገ-ወጥ መንገድ ገብተዋል፣ እንዲሁም የጠላት ተግባር ፈጽመዋል የሚል ነበር። ያስፈቷቸውም የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት ቢል ክሊንተን ነበሩ።
ደስ የሚል ስሜት ተሰማኝ። ምክንያቱም የሰሜን ኮሪያ መንግሥት አምባገነንና የሰብዓዊ መብትን የማያከብር በመሆኑ እነዚህም ሁለት ጋዜጠኞች ያለአግባብ መታሰራቸውን ስለተገነዘብኩ ነበር። ግን የተሰማኝ ደስታ ብዙም አልቆየም፣ በሃሳቤ ምናብ ቀጥታ ወደ ቃሊቲ እስር ቤት ተጓዝኩ። “የኛዋ ብርቱካንስ?” አልኩ። እስዋንስ ማን ነው የሚያስፈታት? ማነው የሚነጋገርላት? ... ብዙ አሰብኩ፣ ብዙ አወረድኩ። የቀረበልኝንም እራት ለመብላት ሆዴ እምቢ አለኝ። ሆዴ በኀዘን ይንቦጫቦጭ ጀመር።
ፈዝዤ ከቀረሁበት ስነቃም ተነስቼ ወደ ኮምፒዩተሬ በመሄድ ዘወትር እየገባሁ የምከታተለውን የፓልቶክ ክፍል ገባሁና ለማዳመጥ ሞከርኩ። የታዘብኩት ግን ስለብርቱካን ማንም ሲያወራ አልሰማሁም። ግራ ገባኝ ብርቱካንን ረሳናት እንዴ? አልኩ ለራሴ። በዕለቱ የሚወራው በፈረንሣይ ስለተካሄደው የኢትዮጵያን ዓመታዊ የስፖርት ፕሮግራም ነበር። የነበሩትን ችግሮች፣ ምን ያህል ተደስተው እንደተመለሱ፣ ... የመሳሰሉት።
ሃሳቤ ግን አሁንም ቃሊቲ ነበር። ልሰማው የፈለኩት ለምን ብርቱካን አትፈታም፣ ለምንስ አናስፈታትም፣ ለማስፈታትስ ምን ማድረግ አለብን?፣ የዓለም ኅብረተሰብና መገናኛው ብዙኀን ስለብርቱካን አግባብ በሌለው ሁኔታ መታሰር በይበልጥ እንዲያውቁና እንዲናገሩ ለማድረግ ምን እናድርግ?፣ ... የሚሉትን ሃሳቦች ለመስማት ነበር ጉጉቴ፤ ግን አልሆነም።
ተሰላቸሁ፣ ብዙ እናወራለን እንጂ መሥራት ከሚገባን አንድ ሦስተኛውን እንኳን የምንሠራ አልመሰለኝም። ግፊት እንፈልጋለን። በራሳችን አነሳሽነት ለሀገርና ለህዝብ ለመሥራት የሚገፋፋን ነገር የለም። ለምሳሌ ያህል በመጋቢት ወር ውስጥ እነዚሁ ሁለቱ የአሜሪካን ጋዜጠኞች እስር ቤት በተወረወሩበት ወር በካናዳ የሚኖሩ ብርቱካንንና ሀገር ወዳድ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ለካናዳ መንግሥት የሚቀርብ ብርቱካን እንድትፈታ የሚጠይቅ 10 ሺህ የድጋፍ ፊርማ ‘Care 2 Action’ በሚባለው ድረ ገጽ አማካኝነት ለማሰባሰብ ቆርጠው ተነስተው ነበር።
በዚሁ ወቅትም ለእነዚሁ ሁለቱ የአሜሪካን ጋዜጠኞች ይኸው ድረ ገጽ ላይ ፊርማ የማሰባሰብ ሥራ ተጀምሮ ነበር። ዛሬ ተመልሼ የፊርማው ማሰባሰቡ ሥራ ምን እንደደረሰ ለማየት ወደ ድረ ገጹ ገባሁ። ባየሁትም አዘንኩ። የሁለቱ ጋዜጠኞች 88 ሺህ በላይ ሲሆን (ፊርማውን ለመመልከት እዚህ ይጫኑ!)፤ የኛዋ ብርቱካን እንኳን 10 ሺህ ፊርማ ሊሰባሰብ ሁለት ሺህ የሚሞላም አልተገኘም (ፊርማውን ለመመልከት እዚህ ይጫኑ!)። በጣም አሳዘነችኝ። በሚሊዮን ከምንቆጠር ኢትዮጵያዊ ዳያስፖራዎች ተባብረን፣ ተነጋግረን ካንዱ ወደ አንዱ ተቀባብለን 10 ሺህ መሙላት አቃተን? እኔ በበኩሌ አደረኩ ለማለት ሳይሆን ፊርማውን ከመፈረሜም ሌላ ለማውቃቸው ሁሉ በኢ-ሜይል አስተላልፌያለሁ።
ከጊዜያችን ከሁለት ደቂቃ በላይ ለማትወስድ ይህችን ትንሽ ሥራ መሥራት ካልቻልን፤ ለሀገርና ለወገናችን በተለይ እንደ ብርቱካን ላሉ በእስር ለሚገኙ፣ ከዚህ በፊትም አሁንም ራሳቸውንና ሕይወታቸውን አሳልፈው የሰጡና ለመስጠት የተነሱ ወገኖቻችንን በምንድነው የምናበረታታቸው? ወይስ ተስፋ እያስቆረጥናቸው ነው? በጣም አዘንኩ፣ እንባዬ መጣ፣ ለማልቀስም በጣም ፈለግሁ … አለቀስኩም። ግን ማልቀስ መፍትሔ አይመስለኝም።
ወደ መኝታዬ አቀናሁ። አልጋዬ ላይ ጋደም አልኩ፤ ነገር ግን እንቅልፍ አልነበረኝም። እገላበጣለሁ። የብርቱካን መታሰር አልገባኝ ብሏል። ሰው በገዛ ሀገሩ እንዴት ነፃነቱን ያጣል? አሁንም ወደ ቃሊቲ ተጓዝኩ። ብርቱካን ምን እያደረገች ይሆን? ብዬ ማሰብ ጀመርኩ። ከታህሳስ ወር ጀምሮ በቃሊቲ በመክረሟ ያ ጀግንነቷ ክዷት ይሆን? ተሸንፋ ይሆን? ተስፋዋስ ተሟጦ ይሆን? ... አይመስለኝም። ብርቱካን አሁንም ብርቱ ናት። አሁንም ጀግና ናት። በወገኖቿስ ተስፋ ጥላ ይሆን? አልኩ ደግሞ፣ እራሴን ጠየኩት። አሁንም አይመስለኝም ነበር የራሴው መልስ። የምትተማመነው በሥራዋ ነው። የምታመነው እውነትን ነው። እምነት በኛ ቢኖራት ኖሮ አናሳፍራትም ነበር። እርሷ ስለሰው ልጆች መብት ማጣት ተቆርቁራ በእምነቷ ፀንታ ስለተገኘት ዳግም ወደ እስር በመወርወሯ፤ እኛ አንድ መሆን ሲገባን የተያያዝነው እርስ በርስ መከፋፈል ሆኗል። ስለሠራችው ገድል አናወራላትም፤ ግን የራሷ ገድል ይናገራል። ከቃሊቲ ወጥቶ ይጮሃል። እውነት ብትዘገይም ትወጣለች። ብርቱካንም በኛም ባይሆን በንፁኅ ሥራዋ ከእስሯ ብቻ ሳይሆን ከዘላለም ባርነትዋ ራሷ ነፃ ወጥታ እኛንም ታወጣናለች።
እናም ሁላችን እንቅልፍ ከሚነሳን ነገር ቶሎ የምንላቀቅበትን የምንፈልግ ከሆነ ክንዳችንን፣ ጉልበታችንን፣ ማንም በፖለቲካ አቋሙ እና አስተሳሰቡ የማይገደልባት ወይም የማይታሰርባት፤ ለሁሉም እኩል የሆነች ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመመስረት በሚደረገው ትግል አመለካከታችን ሳይከፋፈል የምንታገልበትና ድምፃችንን የምናሰማበት፣ የማይደክምና የማይዝል የትግል መድረክ ያስፈልገናል። አሁን የምናየው ግን ሲሞቅ አለን - አለን፤ ሲቀዘቅዝ ደግሞ ደብዛችን የሚጠፋበት አይነት ሁኔታ ነው። ይኸው እንደምናየው ብርቱካንን ለማስፈታት እንኳን ጠንካራ የሆነ ትግል ለማድረግ አለመቻላችንን ያመላክታል።
ዛሬ ብርቱካን እየተረሳች ነው። ድምፃችንን ማሰማት አቁመናል። ይህ ደግሞ በጣም ቆሽት የሚያሳርር ነው። በተለይ ባሁኑ ወቅት ከሀገር ፍቅር ይልቅ ለጫትና ለሀሺሽ የበለጠ ፍቅር ያለው ትውልድ (በየቤቱም፣ በሀገር ቤትም፣ በውጭም ታይቷል። እንዲሁም የፓሪሱ ዝግጅት ግምገማ ብዙ ተብሎበታል)። ብርቱካንን ለማስፈታት ይታገላል ብሎ ማስብ በጣም አጠራጣሪ የሆነበት ጊዜ ነው። ግን ምንም ቢሆን ምን አንድ ቁርጠኛ ተከታይ ብርቱካን እንደሚኖራት አልጠራጠርም። እሷም አንድዬ ልጇ ሐሌ ናት። ሐሌ ታዳጊዋ፣ ሐሌ ፍልቅልቋ፣ ብርቱካንም ብርቱ እንደሆነች በእኛም ባይሆን ስለ እውነት መኖር፣ ስለ ነፃነት የግድ መኖር ሲባል ትወጣለች። ስሟም የዘለዓለም ነው።
ብርቱካንና መላው የፖለቲካ እስረኞች በአስቸኳይ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ይፈቱ!!!
ፍቅርና ሠላም ያድለን!
ፍቅሩ ይበልጣል ነኝ።



