ለመስከረም 3 ሰልፍ ጋባዣችን ህሊናችን ነው (ፍቅሩ ይበልጣል)
ፍቅሩ ይበልጣል
መስከረም 3 ቀን 2002 ዓ.ም. (September 13, 2009) በዋሽንግተን ዲ.ሲ. በዋይት ሐውስ ፊት ለፊት 100 ሺህ ዕድምተኛ የሚጠበቅበት እና ወያኔ በህዝባችን ላይ የፈጸማቸውንና በመፈፀም ላይ ያለውን በደል፣ ስቃይ፣ ግድያና እስራት ለማጋለጥ ኢትዮጵያውያንና ሌሎችም ኢትዮጵያንና ህዝቧን የሚወዱ ሁሉ ሊገኙበት የሚገባ ታላቅ ሰልፍ የሚደረግበት ቀን ነው።
በዚህ ሰልፍ ላይ ለመገኘት “ማን ነው የጠራው?” ብሎ መጠየቅ እንኳን የሚገባ አይመስለኝም። ማን ነው የጋበዘኝም ወይም የሚጋብዘኝ ብሎ መጠየቅም አስፈላጊ አይደለም። ጋባዣችን የራሳችን ሕሊና ነው። በሀገራችን የሚደረገው የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የህዝቦች መንገላታት፣ መታሰር፣ መሰቃየት የሚያንገበግበን ሁሉ በተለይም በዋሽንግተን ዲ.ሲ. እና በአካባቢዋ ነዋሪዎች የሆንን ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሞትና የሕይወት፣ የመኖርና ያለመኖር ውሳኔ መሆኑን ተገንዝበን፤ ይህ ሰልፍ ለሀገራችን ሊያመጣ የሚችለው ለውጥ እንኳን አናሳ ቢሆን፤ ነገር ግን ከሕሊና ወቀሳ እራስን ለማዳን ካለን የሥራና ሌሎችም ግዴታዎች ይህችን ግማሽ ቀን ለዚህ ታላቅ ዓላማ ለማዋል መዘጋጀት ይኖርብናል።
ሰሞኑን አንድ ወዳጄ የሆነች የምትገርም ነገር ብሎ በጆሮዬ ሹክ አለኝ። አንዳንድ ያውም የፓርቲ መሪዎች ነን የሚሉ በዚህ ሰልፍ ላይ አንገኝም ሲሉ ተደምጠዋል አሉ ብሎ ነበር የነገረኝ። ይህችን ነገር ግን አንድ ቀን ማታ ፓልቶክ ክፍል ገብቼ ሳዳምጥ አንድ በጣም ጥሩ ተናጋሪ “እንዴት እዚህ ሰልፍ ላይ አትገኙ ብሎ ያውም ወያኔን ተቃዋሚ ነን በሚሉ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች እንደዚህ አይነት ቅስቀሳ ይደረጋል” ሲል በጆሮዬ ጥልቅ ሲል ሰምቻለሁ። በእውነት ይህንን ያሉ ወይም ለመቀስቀስ የተነሱ ካሉ የኢትዮጵያን መነሳት ሳይሆን በእውነት ውድቀቷን የሚመኙ ለመሆናቸው ምንም ማስረጃ የሚያሻን አይደለም።
እነዚህ ፓርቲዎች ራሳቸውን ኢትዮጵያዊ ብለው ለመጥራት የሚዳዱ ከሆነ ወይንም እውነት ለሀገራችንና ለህዝቧ ነው የምንታገለው የሚሉ ከሆነ፤ በዚህ ሰልፍ ላይ መገኘት የበለጠ ፓርቲያቸውንም ትግላቸውንም የሚያሳውቁበት መድረክ ሊያደርጉት ይችላሉ። ብሎም ደግሞ ከሌሎች የትግል አጋሮቻቸው ጋር በመገናኘት እንደውም ወደፊት በበለጠ አብረው ሊሠሩ በሚችሉበት ሁኔታዎች ለመመካከር እንዲረዳ መተዋወቂያም መድረክ ሊሆን ይችላል።
ይህ ሰልፍ የተጠራው ግለሰቦችን ለማሳወቅ እና ለማግነን አይደለም። መረዳት የሚኖርብን አንድ ነገር ቢኖር ግለሰቦች ለሀገርና ለወገን ቀንና ሌሊት ያለእረፍት ቀና በማሰብ በሚሠሩት ጥሩ ሥራና ተግባር ታዋቂ ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን ሌሎቻችን ለምን ተበለጥኩ በሚል መጥፎ ሠይጣናዊ አስተሳሰብ በመነሳሳት መልካም ሥራቸውን ከማጉደፍና እነሱንም ብዙ ጠቃሚ ሥራዎችን ሊሠሩ ሲችሉ ከማስተጓጎል እንድንቆጠብ ጥንቃቄ ማድረግ ያሻናል። ለመሥራት ችሎታውና ዕውቀቱ ካለን ብዙ የሚሠሩ ሥራዎች አሉና መላውን በውጭ የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ በማስተባበር ሁላችንም ድርሻችንን ልንወጣ ያስፈልገናል። ለዚህም ቅን ልቦና ጥሩ ህሊና ያስፈልጋል።
ሰልፉ የተጠራው በሀገራችን በኢትዮጵያ ያለውን ኢ-ፍትሃዊ የሆነ መንግሥት ለማጋለጥና በአሜሪካ መንግሥት የሚደረግለትን ማንኛውንም እርዳታ ለህዝቡ ከሚሰጣቸው የዲሞክራሲ መብቶች ጋር በማያያዝ እርዳታው የግለሰቦችን ኪስ ማደለቢያ እንዳይሆን ለማሳወቅ ነው። ህዝባችን የዚህ እርዳታ ዋንኛ ተጠቃሚ በመሆን በልቶ የሚያድርበትንና ብሎም ራሱን ችሎ ከተመጽዋችነት የሚወጣበትን ጊዜ ለማሳጠር የሚረዳን አጋጣሚ ነው።
ከሁሉም በላይ ይህ ሰልፍ በኢትዮጵያ ያለአግባብ ሰብዓዊ መብታቸው ተገፎ በእስር የሚማቅቁትን የፖለቲካ እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ የሚጠይቅና የፕሬዝዳንት ኦባማ አስተዳደር በዚሁ ላይ ግፊት እንዲያደርግ የሚጠይቅ ነው። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን እዚህ ላይ በአብነት ማንሳት ይቻላል። የሷንና ሌሎችም የፖለቲካ እስረኞች መፈታት የሚሹ ሁሉ ተገኝተው ድምፃቸውን ማሰማት ይጠበቅባቸዋል።
ይህ ሰልፍ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው እንደ ሁለተኛ ዜጋ ተቆጥረው የመናገር የመሰብሰብ ሌሎችም ሌሎችም መብቶቻቸው ተገፈው በአሁኑ ሰዓት ከሀገር ውጭ ለስደት የሚዳረገው ብዛት ያለው ህዝባችን በተለያዩ ሀገሮች የሚደርስበት ግፍና ሰቆቃ ያበቃ ዘንድ ለዓለም ህዝብ ለማሳወቅ ነው።
ይህ ሰልፍ ኢትዮጵያውያን መታወቂያችን የሆነውን የህዝባችን በረሃብ አለንጋ መገረፍ የሚያበቃበትና በሀገራችን ብሔራዊ እርቅ ተደርጎ ሁሉም የተማረ ዜጋ ሁሉ በአንድነት ለሀገር ብልፅግናና እድገት በመሥራት ድህነትን ለማጥፋት ሁሉም እንዲነሳ ዜጎች ትብብራቸውን የሚያሳዩበት ነው።
ይህ ሰልፍ በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን እጅ ለእጅ በመያያዝ ለሀገራችን እና ለወገናችን ደራሽ መሆናችንን፣ ድምፅ ለሌለው ወገን ድምፅ ለመሆንና ብሶቱን ለማሰማት አሜሪካና የዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ትብብራቸውና ልገሳቸው ህዝባችንን በቀጥታ በሚጠቅም እንጂ በተዘዋዋሪ መንገድ አፋኝ መንግሥትን በሥልጣን ላይ ለማቆየት እንዳይሆን፡ እንዲሁም በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በሚሠራቸው የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች፣ ማሰርና መግደል፣ በዘር ማጥፋት ወንጀል (በአዲስ አበባ፣ በጋምቤላ፣ በአርባ ጉጉና በመሳሰሉት የተደረጉት የዘርና የህዝብ ማጥፋት) ተጠያቂ እንዲሆን፣ በአንድነት ተነስተን ድምፃችንን ማሰማትና ለውጥ በሀገራችን እንዲመጣ ግፊት የምናደርግበት ጥሩና አመቺ አጋጣሚ ነው።
ይህንንም አመቺና ጥሩ አጋጣሚ ለመጠቀምና ለወገናችን ፍቅራችንን የምናሳይበት ሥራ ለመሥራት ታዲያ ምን ግብዣ ምን ቀስቃሽ ያስፈልገናል? ጋባዣችንም ቀስቃሻችንም ህሊናችን ነው። ማንም ጋባዥና ተጋባዥ ወይም አመስጋኝና ተመስጋኝ ሊሆን አይገባም። ሀገራችን ችግሯ ብዙ እንደመሆኑ ሁላችንም በቡድንም ሆነ በግለሰብ የተለያየ ችግሮቿን ይዘን ወጥተን በዚህ ሰልፍ ላይ በዝተንና ደምቀን ተገኝተን የዓለም ኅብረተሰብ ችግራችንን እንዲረዳልን ለማድረግ ቆርጠን እንነሳ። ዘመድ፣ ወዳጅ፣ ጓደኛ የምናውቀውንም የማናውቀውንም በመጋበዝ ሰልፉ የተዋጣለት እንዲሆን የበኩላችንን ከማድረግ አንቆጠብ! እንበርታ!!
ሠላምና ፍቅር ከሁላችን ጋር ይሁን!
ፍቅሩ ይበልጣል ነኝ