አማኑዔል ዘሠላም ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ) ነሐሴ 29 ቀን 2001 ዓ.ም.

“መሪያችን ብርቱካን ሚደቅሳ በግፍ ታስራ፣ ደጋፊዎቻችን በየቦታው ወከባ እየደረሰባቸው፣ በህዝብ ገንዘብ የሚተዳደሩ የመንግሥት መገናኛ ብዙኀን ርካሽ ፕሮፖጋንዳ እየረጩ፣ ስለምርጫ ማሰብና ስለ ምርጫ ማውራት እራስን ማታለል ነው። አንዳች ጥቅም ለማያመጣ ገዢው ፓርቲ በውጭ ሀገር መንግሥታት ለመደገፍ ሲል ብቻ የሚጫወተውን የፖለቲካ ጨዋታ ለማዳመቅ ፍላጎቱ የለንም።” [1]

 

የአንድነት ለዲሞክራሲ ለፍትህ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አባል ገዢው ፓርቲ በምርጫ ሥነ ምግባር ላይ እያደረኩ ነው የሚለውን ስብሰባ፣ አንድነትና ሌሎችም የመድረክ አባላት ረግጠው መውጣታቸውን አስመልክቶ የተናገሩት ነበር።

 

የአንድነትና የመድረክ አባላት የወሰዱትን ቆራጥ እርምጃ እያደነኩ ሌሎች የተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለይም አቶ ኃይሉ ሻውል የሚመሩት መኢአድ፣ በኢህአዲግ ሸንጎ ውስጥ ምን እያደረገ እንደሆነ ለመጠየቅ እወዳለሁ።

 

”የ1997ቱን ብሔራዊ ምርጫ ተከትሎ በተፈጠረው የህዝብ ተቃውሞ ቅንጅት፣ ከዚያም ወዲህ መኢአድ ለነፃ፣ ለፍትሃዊና ለሠላማዊ መንግሥታዊ ሽግግር እንዲሟሉ ለመንግሥት ያቀረባቸው ሰባት ጥያቄዎች” በሚል ረጅም ርዕስ ሥር ሰባት ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጡ ይታወሳል። የመጀመሪያው ቅድመ ሁኔታ እንደ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ያሉ ”የፖለቲካ እስረኞች ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ” የሚጠይቅ ነበር። [2]

 

በመኢአድና በአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ መካከል በጣም የቀረበ ግንኙነት እየተፈጠረ ነው ብዬ እገምታለሁ። የመኢአድ ሊቀመንበር አቶ ኃይሉ ሻውልና በርካታ የድርጅቱ አመራር አባላት፣ የቃሌ ምሽት በተሰኘው በየወሩ የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ መታሰርን በሚያስታውሰው ዝግጅት ላይ ተገኝተው ንግግር ማድረጋቸውንና በግፍ ለታሰረቸው ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ያላቸውን ድጋፍ መግለጻቸው ያታወሳል።

 

መድረክ ባዘጋጀው የጋራ ማኒፌስቶ ላይ፣ መኢአድ መጀመሪያውኑ መድረክን እንዳይቀላቀል ምክንያት የሆነው እስከ መገንጠል የሚያደርስ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትን (አንቀጽ 39 ተብሎ የሚታወቀው) እንደማይቀበል፣ መድረኩ በማረጋገጡ፣ መኢአድ መድረክን የመቀላቀል ዕድሉን በጣም ያሰፋው ይመስለኛል።

 

የገዢውን ፓርቲ አቋም የሚያንጸባርቁ ጋዜጦች አንድነትንና መኢአድን ለማጋጨት፣ በሁለቱም መካከል ያለው ልዩነት እንዲሰፋ ለማድረግ ከፍተኛ ዘመቻ ጀምረዋል። ለምን ቢባል የአንድነት ኃይሎች በጋራ ከተሰባሰቡ ምን ማድረግ እንደሚችሉ የአምባገነኑ ኢህአዲግ ካድሪዎች ጠንቅቀው ስለሚያወቁ ነው።

 

”የአንድነት ፓርቲ አቋም ኢዴፓ፣ መኢአድና ቅንጅት (የአየለ ጫሚሶ ቡድን ማለታቸው ነው) ባሉበት ቦታ አንድ ላይ አንሰበሰብም የሚል ነው” [3] ሲል ነበር ኢትዮቻናል የአንድነት ፓርቲ በምርጫ ሥነ ምግባር ላይ የሚደረገውን ውይይት እንደማይሳተፍ የሚገልጸውን የፈጠራ ወሬ የዘገበው። እዚህ ላይ ልብ በሉ … በመኢአድና በአንድነት መካከል ልዩነት እንዳለ ለማሳየት የሚደረግ ከፋፋይ ተግባር እንደሆነ።

 

እንዲህ አይነቶቹን ከፋፋይና እኩይ ተግባራት፣ በተደራጀ መልኩ በገዢው ፓርቲ የሚደረገው ትግሉንና የኢትዮጵያን ህዝብ ተስፋ ለማጨለም እንደሆነ በማሰብ አንድነትና መኢአድ ከመቼውም የበለጠ ግንኙነታቸው ማጠናከር አለባቸው።

 

መኢአድ ያቀረባቸውን ሰባቱ ጥያቄዎች ወደ ጎን አድርጎ፣ በምርጫ ሥነ-ምግባር ላይ ብቻ ለመወያየት ከአቶ ልደቱ አያሌውና ከአቶ አየለ ጫሚሶ ጎን የአመራር አባላቱ መቀመጣቸው ትልቅ ስህተትና በቶሎ መታረም ያለበት ነው።

 

ምናልባትም በቅንነት ይሆናል በዚያ ስብሰባ ላይ የመኢአድ አመራር አባላት የተገኙት። ነገር ግን ከዚህ ስብሰባ ከአገዛዙ ቡራኬ ከማግኘት በስተቀር ለትግሉም ሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብም የሚያመጣው አንዳች ጥቅም አይኖርም።

 

መኢአድ ያቀረባቸው ሰባት ጥያቄዎች አሉ። እነዚህ የመኢአድ ሰባቱ ጥያቄዎች የአንድነት ፓርቲም ጥያቄዎች ናቸው። መኢአድም ሆነ አንድነት የምርጫ ፓርቲ እንደመሆናቸው፣ ለምርጫ የሚያደርጉትን ዝግጅቶች ከመቼውም የበለጠ በጋራ እያጠናከሩ፣ ለምርጫ የሚያስፈልጉ መሰረታዊ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎች እንዲመቻቹ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በጋራ መታገል ይጠበቅባቸዋል።

 

ስለዚህም ለመኢአድ አመራር አባላት የሚከተሉትን ጥሪዎች በአክብሮት አቀርባለሁ፦

 

• ከአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲና ከመድረክ ጋር በመቆም፣ ገዢው ፓርቲ በምርጫ ሥነ ምግባር ደንብ ላይ ብቻ ሳይሆን ለምርጫ በሚያስፈልጉ መሰረታዊ ቅድመ ሁኔታዎች ላይም መወያየት እንደሚያስፈልግ በማረጋገጥ፣ የአንድነት አመራር አባል የተናገሩትን ልዋስና፣ አገዛዙ የሚያደርገውን የፖለቲካ ጨዋታ ከማዳመቅ እንዲቆጠቡ፤

• መድረክ የተሰኘው አካል፣ የራስን እድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብትን (አንቀጽ 39) እንደሚቃወም በማኒፌስቶ አስቀምጧል። በመሆኑም መኢአድ በመድረክ ውስጥ ለመሥራት እንቅስቃሴና ውይይት እንዲጀመር፤

• በአንድነትና በመኢአድ መካከል አንዳችም አይነት የፖለቲካ ፕሮግራም ልዩነት የለም። በርካታ የአንድነት አመራር አባላትና የመኢአድ አመራር አባላት አብረው የሠሩና አብረው ብዙ የማቀቁ ናቸው። በመሆኑ እነዚህ ፓርቲዎች በተናጥል የሚንቀሳቀሱበት ምክንያት አይታየኝም። ስለዚህ ያለፉት ስህተቶች እንዳይደገሙ በሚያስችል ሁኔታ፣ ላለፉት ስህተቶች ይቀርታ በመጠያየቅ፣ መኢአድና አንድነት እንዲዋሃዱ የሚረዳ ሥራ እንዲጀመር የሚሉ ናቸው።

 

አሳሳቢና ወሳኝ ወቅት ላይ ነው ያለነው። ሁላችንም ከዚህ በፊት በርካታ ስህተቶች ሠርተናል። ባለፈው ስህተት ላይ ብቻ እኝኝ ብሎ ከመቀመጥ ወደፊት ማየትንና መተባበርን የጊዜው ትግል ይጠይቃል። በብሔር ከተደራጁ ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመሥራት እየተሞከረ ባለበት ወቅት አንድነትና መኢአድ በጋራ መቆም ካልቻሉ በጣም የሚያሳዝን ነው።

 

ለመኢአድ አባላት ሀገራዊ ጥሪ ሳቀርብ ሳልጠቅስ ማለፍ የማልፈልገው ትልቅ ጉዳይ አለ። መኢአድ ለኢትዮጵያ ንጹኅ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ መከበር እያደረገ ያለውን ትንቅንቅ ሁላችንም በአድናቆት እየተመለከትነው ነው። በአርባምንጭ የመኢአድ አባላት ይህን አባቶቻችን ደማቸውን ያፈሰሱበት ሰንደቅ ዓላማ ለምን ሰቀላችሁ ተብለው፣ ግራዚያኒ ያኔ ያደርግ እንደነበረው መታሰራቸው፤ የመኢአድ ፓርቲም ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ በሰንደቅ ዓላማችን ዙሪያ መንቀሳቀሱ በኢትዮጵያ አንድነት ዙሪያ መኢአድ ምን ያህል የታመነ መሆኑን የሚያሳይ ነው።

 

 [1] http://www.abugidainfo.com/amharic/?p=2167

 [2] http://www.kaeup.com/newsImages/pressrelease/PR-AEUP-SevenPointsAEUPDemandofGov-082009-Amh.pdf

 [3] http://www.ethiopiafirst.com/news2009/Aug/Ethiochannel_01Sept09.pdf


አማኑዔል ዘሠላም  This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ