በሲያትል ተደመምን፤ በካልግሪም ኮራን፤ በፖርትላንድም ተደነቅን
አለቃ ተክሌ - ከቫንኩቨር
ሀተታ እና አስተያየት፤ ከቫንኩቨር ንግስ መልስ ወደ ፒስ (ፒትስ) በ(ር)ግ
ሊቀ ዲያቆኑ፤ የሲያትል ህዝብ
ሊቀ ዲያቆን ታደሰ የሲያትሉ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ዲያቆን “ቲኬት ግዙ ምናምን አትበሉን። ትኬታችሁን ያዙ። በእለቱ ብቻ ተዘጋጅታችሁ ጠብቁን” ብሎ ለሲያትል ህዝብ ልንቸበችብ የወሰድነውን ቲኬት ሲመልስብን ትንሽ ደንግጠን ነበር። የበአሉ ጊዜ እያነሰና እያጠረ ደግሞ እየቀነሰ ሲመጣ ሰው ይመጣ ይሆን ብለን ትንሽ ማሰባችን፤ ትንሽም መጠራጠራችን አልቀረም። ልበ ሙሉው ሊቀ ዲያቆን ግን ይገስጸን ነበር።
ክርስቶስ ጴጥሮስን እንደገሰጸው መሆኑ ነው። እናንተ ብላቴናዎች አትጠራጠሩ ብሎ። ሀምሳ አምስት ሰው የሚይዘው የመጀመሪያው አውቶቡስ ሞላ ተባለ፤ ሁለተኛውም አውቶቡስ ሞላ ተባለ። ሶስተኛ አስፈለገ። ሶስተኛም አውቶቡስ ተከራዩ። እነሆ እኔ የዚህ ጽሁፍ ጸሀፊ ቅዳሜ ማለዳ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር መስከረም 19 ቀን 2 ሺህ 9 ዓ.ም. ወደ ቅጥረ ቤ/ክ ሳመራ አንዱ የሰበካ ጉባኤ አባል ደውሎ “ቤ/ክኑ በመቶዎች በሚቆጠሩ የሲያትል ምእመናን ተሞልቶ መፈናፈኛም የለም” ሲለኝ አላመንኩም ነበር። ግነት መሰለኝ።
ወደ ቤ/መቅደስ ስጋባ ግን የወንድሜ መረጃ ግነት አልነበረውም። ሴቶችና ወንዶች፣ ልጆችና አዋቂዎች፣ ያገር ባህልና ዘመናዊ ልብስ የለበሱ የሲያትል ምእመናን ቤ/መቅደሱን ሞልተውታል። ቅዳሴ ተጀምሮ ወደ እኩሌታው እየተጠጋ ነበር። ምን ሰዓት ቢነሱ ነው በዚህ ሰዓት የደረሱት ብለን ተደነቅን። ይሄ ሊቀ ዲያቆን ምንስ ቢያስነካቸው ነው እኚህ ሁሉ ሰዎች ይሄንን ሁሉ ተጉዘው በውድቅት ተጉዘው የመጡት? ኩራትና መንፋሰዊ ትእቢት ውስጣችንን ሞላው። እነሆ በሲያትል ህዝብ ኮራን።
ከዚያማ ምኑ ተወርቶ? ምኑስ ታትቶ? ቅዳሴ፣ ወረብ፣ ስብከት
አስቀድመን ተናግረን አስቀድመንም አውጀን ነበር። የኆህተ ሰማይ ቅድስት ማሪያም ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ በቫንኩቨር የጸደኒያ በዓለ ንግስ እንደሚከበርና ታላቅ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅትም እንዳለ። http://ethiopiazare.com/articles/opinion/34-opinion/1074-aleqa-tekle ወይንም
http://ecadforum.com/blog/2009/09/10/ethiopian-orthodox-church-in-vancouver/ ወይንም
http://www.abugidainfo.com/amharic/?p=2248 ላይ ይመልከቱ። እነሆ በዓላችን በተሳካና በሚያስደስት መልኩ ተጠናቋል።
በዚህ ባለፈው ቅዳሜ መስከረም 9 ቀን 2002 ዓ.ም ሙሉ ቀን በተከበረው በዓል ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሲያትል፣ የፖርትላንድና ካልጋሪ እንዲሁም ቫንኩቨር ምእመናን የተገኙ ሲሆን ሶስት ሊቃነ ጳጳሳትና ብዙ ዲያቆናት ተሳትፈው በዓሉን ድምቀት ሰጥተውታል። ታላቁ የወንጌል መምህር አባ ገብረስላሴም እንዴት ያለ ወርቅ ትምህርት ለአርባ አምስት ደቂቃ አስተምረዋል። ከዚያ አስቀድሞ ግን ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ጀምሮ አባታችን አቡነ ሉቃስ ገባሬ ሰናይ ሆነው፤ አባታችን አቡነ ዮሃንስና አቡነ ሚካኤል ረዳት ሆነው፤ አባ ሕርያቆስ የደረሰው ቅዳሴ ማርያም ተቀድሷል። አቤት ያባታችን ድምጽ !!። ስቀዳው ነው የዋልኩት። ቅጂውን የሚፈልግ ምይል ይመይልልን። ምይል ኢሜል መሆኑ ነው።
እናቴ ትዝ አለችኝ እንዲሁም አገሬ፡ እንዲሁም
የቫንኩቨር ቤ/ክ መዘምራን ሁለት መዝሙርና ወረብ ከዘመሩና ከወረቡ በኋላ የሲያትል መዘምራን አጊጠው ከች አሉ። የሲያትል መዘምራን ራሱ ሁለት ሙሉ ሙሉ ቡድናት ናቸው። እንደጉድ ተወረበ። እንደጉድ ተመለከ። እንደጉድም ተዘመረ። እነሆ የበዓሉን ድምቀትና የህዝቡን ሙላት በተመለከቱ ግዜ ብዙ የተገፉ የቫንኩቨር ምእመናን ሲያለቅሱ ተመልክቻለሁ። እኔም ራሴ ከአገሬ ከወጣሁና ሰባት አመት ያገለገልኩበት ጊዮርጊስና ወዮ መድሀኔ ዓለም ሲነግሱ ካየሁ ከዘጠኝ ዓመት በኋላ እንዲህ ያለ ደማቅ ንግስ ሳይ የመጀመሪያየ በመሆኑ ደስታዬ ልክ አልነበረውም። ፡እናቶች “ነይ ነይ እምዬ ማርያም፤ ነይ ነይ ቤዛይት አለም” ሲሉ በሰማሁ ግዜ ያቺን እርጅና እየነገሰባት የመጣውን እናቴን አየኋት።
የኢትዮጵያ ባንዲራ ከጥግ እስከ ጥግ ግጥግጥ ብሎ ቤታችን ደምቆ ሳይ ውስጤ በደስታ ተተራመሰ። ሊቀ ዲያቆን መጣ። እስኪ የሲያትል ሰዎች ተነሱ አለ። ከፖርትላንድና ከካልጋሪ በስተቀር ቤቱ ከወንበሩ ተነቅሎ ተነሳ። አባታችን አቡነ ሚካኤል ካልጋሪን ወክለው ጥቂት ተናገሩ። ቀደም ባለው ሳምንት የካልጋሪ ህዝብ ባንድ ሰንበት ለቫንኩቨር ቤ/ክ እንዲሆን ብሎ ባንድ ትንፋሽ ወይም ባንድ ዙር ብቻ የሰበሰበውን ስድስት መቶ ሰማኒያ አካባቢ የካናዳ ገንዘብ አበረከቱ። ፖርትላንዶችም ቀጠሉ። እንዲሁ ባንድ ዙር የተሰበሰበ አምስት መቶ ሀምሳ አካባቢ ብር አበረከቱ።
አሁን የሲያትል ተራ ደረሰ። ያ ሊቀ ዲያቆን ታደሰ በሉሀ ሲያትል እስኪ ጉዳችሁን እንይ አለ። ብሩ ከመብዛቱ የተነሳ በውሰት ያገኘናቸው ዣንጥላዎች ሊይዙት አልቻሉም። ተንገዳገዱ። አራት ሺህ የአሜሪካን ብር ባንድ ዙር ተሰበሰበ። የተሸጠውን ቲሸርት፣ በጨራታ የተቸበቸበውን ባህላዊ ቁሳቁስ ለመቁጠር ቀኑ አልበቃንም። እነሆ ይሄንን ጽሁፍ ባጠናቀርንበት ሰዓት ከዚህ ዝግጅት ከአስር ሺህ ብር በላይ ተሰብስቧል። ግን ገንዘቡ አይደለም ሀብት። ሰው እንጂ። ሰው ይግደለኝ።
ምን አገኘን? ይሄስ ምን ማለት ነው?
አንደኛ ሞራላችን ለመለመ። ቀድሞ ኮሰን ነበር። ተጠራጥረንም ነበር። ብቻችንን የሆንን መስሎን አዝነን ነበር። ተስፋችን አበበ። እነሆ አስራ ምናምን ዓመት ይህቺን ቤ/ክ ለማቋቋም ሻይ ሲሸጡና ደፋ ቀና ሲሉ ኖረው ከኋላ በመጡ ነገረኞች ከቤታቸው ተፈንቅለው የነበሩና መገፋታቸው ሲያማቸው የከረሙት ምእመናን የህዝቡን ብዛትና የወረቡን ድምቀት ሲመለከቱ አጥንታቸው ለመለመ። ተቃቅፈው ተላቀሱ። አገሩ ተባረከ። አባታችን አገሩን ጸለዩበት። የምእመናን ሁለመናቸው ታደሰ። ደግሞ የህዝቡ ስብጥር። እዚያ አማራ ብቻ አልነበረም። እዚያ ትግሬም ብቻ አልነበረም። እዚያ ኦሮሞ ብቻ አልነበረም ወይንም ጉራጌ ፤ ብሄር ቦታ አልነበረውም ባጠቃላይ። አገራችን መጣችብኝ። መቼ ይሆን እንዲህ ሰብስቦ አንድ ላይ እንድናመልክ፣ አንድ ላይ እንድንቀድስ፣ አንድም ላይ እንድንኖር የሚያደርግ መንግስትና መሪ የምናገኘው? ሲያትልንና ካልጋሪን እንዲሁም ፖርትላንድ ምሳ አበላን። ደግሞ በነጋታው ሰንበትም አይደል? ብድር ይግባችሁ ለከርሞ እንገናኝ ብለን በጊዜ ሸኘናቸው።
ከዚህ በኋላ አሉን ካህናትና ምእመናን “የቫንኩቨር ኆህተ ሰማይ ቅድስት ማርያም ቤ/ክርስቲያን ግሼን መሄድ ላልቻልን ግሼናችን ነች።” እንደ ቅዱስ ላሊበላ መሆኑ ነው። እንደዚያ ተጽፏል። ቅዱስ ላሊበላ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናቱን ሲያንፅ አንዱ ሀሳቡ በተለያየ ምክንያት ኢየሩሳሌም ሄደው መሳምና መሳለም ያልቻሉ እዚያ ሮሃ ላስታ ላሊበላ ሄደው እንዲሳለሙ አስቦ ነበር ይባላል። እነሆ ቫንኩቨር ግሼንን ልትገነባ እየተሰናዳች ነው። ደግሞ ዳመራ/መስቀል መጥቷል። በመጪው ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ በተለመደው ቦታ እናከብራለን። ለኔ ግን ይሄ በዓል፡ ከዚያም በላይ ነው። ፖለቲካ። ትንታኔዬንና አተታዬን አስከትላለሁ።
ሀተታ እና አስተያየት፤ ከቫንኩቨር ንግስ መልስ ወደ ፒስ (ፒትስ) በ(ር)ግ
ፖለቲካና ሀይማኖት፤ የናንተን እንጃ፡ የኔን ግን እነሆ
ትንሽ አልተገጣጠመም እንጂ፡ ቫንኩቨር የመጣውን የሲያትልን ሕዝብ ነበር ወደ ፒስ (ፒትስ) በርግ Pittsburgh ማሰለፍ። በዚህ ወጌ እንዲህ እላለሁ። ፖለቲከኞች ወደ እምነት ተቋማት ገብተው በእምነት ተቋማት ውስጥ ያሉትን አባቶች ቡራኬና ካላገኙ፤ በእምነት ተቋማት ውስጥ ያሉትን ተከታዮች ካልያዙ በስተቀር ድላቸው ድል አይልም። አንዳንድ ሰዎች ፖለቲካና ሀይማኖትን/እምነትን አትደባልቅ ይላሉ። ለኔ እምነትና ፖለቲካን፤ እምነትና አገርን፤ እምነትና ሕይወትን መለየት የማይቻል ነው። ፖለቲካ በመንግስት አስተዳደርና ስራ እንዲሁም በሕይወታችን ውስጥ ለውጥንና መልካም ነገርን ለማምጣት የምንሳተፍበት መድረክ አይደለምን? እንግዲያውስ ቤታችን አየር ላይ ነው ካላልን በስተቀር እንደምን ፖለቲካና እምነት ይለያያሉ።
የኢትዮጵያ ቤ/ክ ኢህአዴግን ታውግዝ፤ ቅንጅትን ግን ትደግፍ ማለት አይቻል ይሆናል። ለኔ ግን ስገፋና ስጠቃ፤ አላግባብ ስታሰርና ስንገላታ፤ ዜጎች በአገራቸው ሲገደሉና ሲታፈኑ፣ ሲሰደዱም መንግስት ብድግ ብሎ ዜጎችን በዘርና በጎሳ፣ በሀይማኖትና በነገድ እንዲለያዩና እንዲባሉ ሲያደርግ የማታወግዝ ይልቅስ እጇን አጣጥፋ የምትመለከት ሀይማኖት ባፍንጫዬ ትውጣ ባልልም በዚያች ቤ/ክ አናት ላይ የቆሙ አባቶች ግን አይናቸውን አልየው እላለሁ። ምክንያቱም ይሄ ካናዳ ነው። ይሄ አሜሪካ ነው እንደሚሉት ማለት ነው። አባ ጳውሎስ/አባ ገብረመድህን ያንን ናቸው ለኔ። እስኪ ጥቀሱልን አንድ እንኩዋን ቀን አባ ገብረመድህን ያንን ያደረጉበት። እንደውም ህዝብ ሲወገር ድንጋይ የሚያቀብሉ አይነት ሰው ናቸው። እንግዲያውስ
እነሆ ሕግ ጥሰው፣ የቤተክርስቲያን አባቶችን አሰድደው የቤ/ክ ስልጣንን ያለአግባብና አለቀኖና የነጠቁ አጭበርባሪዎች ከነጠቁ በኋላ እንኩዋን በመልካም ስራቸው ስልጣናቸው ማቃናትና ህዝቡንም ማሳመን ሲችሉ ይልቅስ ከገዢው ስርአት ጋር ተባብረው የዘረኝነት ስራቸውንና መርዛቸውን እየረጩ ነው። ልክ በሲቪል መንግስቱ መስሪያ ቤቶች እንደሚደረገው ሁሉ፤ ዛሬ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ ያሉትን የአስተዳደር ቦታዎች ሁሉ ካንድ ጎሳ የወጡ ሰዎች ብቻ እንዲይዙት እየተደረገ ነው።
ይሄም ብቻ አይደለም አባ ጳውሎስ/አባ ገብረመድህን ሕግ ጥሰው መቀመጣቸው ብቻ ሳይሆን የራሳቸውን ተክለ ሰውነት መገንባት ከጀመሩ እነሆ አስራ ስምንተ ዓመት ሞላ። የዛሬ አስር ዓመት ዣንጥላና ቀሚስ አጥተው በራሳቸው ጋቢ የሚቀድሱ አብያተ ክርስቲያናት፣ ጧፍና ሻማ መግዣ የሌላቸው ቤ/ክርስቲያናት፣ የአባ ጳውሎስን ምስል በሶስት መቶ ብር እንዲገዙና ግድግዳቸው ላይ እንዲሰቅሉ ሲገደዱ ተመልክቻለሁ። በቅርቡም የሀሰት ስም አጥፊ መጽሀፍ ታትሞ የአዲስ አበባ ቤ/ክ ካህናት በግድ ከደሞዛቸው እየተቆረሰ እንዲገዙ እንደተገደዱ ተጽፎ ተመልክቻለሁ።
ከምንም በላይ ግን ምእመናን በህወሀት ጦረኞች ሲደበደቡና ሲገደሉ የማያወግዙና የማይቆጡ፤ እንዲያውም ምእመናንን አፋቸውን ሸብበው የያዙ፤ ይባስ ብለውም ለምን ብለው የሚጠይቁ ወጣቶችን በካድሬዎች እያሳደኑ የሚያሳስሩና የሚያስወግሩ ካድሬ የቤ/ክ አባት ተብዬዎች መወገዝና መነጠል አለባቸው። ለኔ የኢትዮጵያን ቤ/ክ ነጻ የማውጣት ስራ ኢትዮጵያን ነጻ ከማውጣት ስራ ነጥዬ አላየውም። ስለዚህም እንዲህ እንደ ቫንኩቨር ባለ ከተወሰኑ የወያኔ ጋሻ ዣግሬዎች ጋር ፍልሚያ የገጠመ ምእመን በሚገኝበት ቦታ የሚደረግ በዓለ ንግስ ሀይማኖታዊ ፋይዳ ብቻ አይደለም ያለው።
ፖለቲካዊና ዴሞክራሲያዊም ፋይዳም ጭምር እንጂ። በነገራችን ላይ ይሄ ጸሀፊ ወደ አባ ጳውሎስ የሚያዘነብሉ ወይንም እሳቸውን የሚከተሉ ሰዎች በሙሉ ወይነዋል ብሎ አያምንም። እንዲያውም አብዛኛዎቹ በየዋህነትና ምናልባትም በፓትሪያርክ መርቆሬዎስ ከሚመራው ህጋዊው ሲኖዶስ ስንፍናና ድክመት የመነጨም ሊሆን ይችላል። መቼም እንዲህ ብለን በመገመታችን አባቶች አይከፉብንም ብለን እናምናለን። የሆነ ሆኖ፡ ስለቤተክርስቲያንና ዴሞክራሲ ትግል የጀመርኩትን ልቀጥልበት።
ቤ/ክርስቲያንና ዴሞክራሲ፤ አባቶችና ፖለቲከኞች
በዴሞክራሲ ትግሉ ውስጥ፡ ቤ/ክ የራሷ ጉልህ ሚና አላት። ምሳሌ። እነሆ የቤ/ክ አባቶችን ጥሪ ሰምተው በመቶዎች የሚቆጠሩ ምእመናን በአውቶብስና በራሳቸው መኪና ነድተው ከሲያትልና ካልግሪ፤ ከፖርትላንድም ጭምር መጡ። ሌላውም ትግል እንዲሁ ነው። ኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች ብቻ አይደለችም። ትግሉም የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ብቻ አይደለም። ስለዚህ ፖለቲከኞቻችን የዚህን ወይንም የዚያን እምነት ይታከኩ ብለን አንሰብክም። አንመክርምም። ፖለቲከኞቻችን ግን የሀይማኖት አባቶችን ቡራኬና ይሁንታ ቢያገኙ የተከታዮቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ቁጥር ይበረክታል። በአሜሪካ ወይንም በካናዳ የሚሆን ሁሉ ለኢትዮጵያ ይጠቅማል ብለን ባንናገርም፤ በአሜሪካና በካናዳ በኬንያም ሳይቀር የሆነውና የሚሆነው ይሄው ነው። ፖለቲከኞች በፖለቲካዊ አጀንዳዎቻቸው ላይ ለምሳሌ በፅንስ ማስወረድ ጉዳይ ላይ የታላላቆቹን (በቁጥር) ሀይማኖቶች ድጋፍ ካላገኙ የምርጫ ውጤታቸውን በብዙው ይጎዳዋል።
እነሆ ወደ ሲያትል የሚመጣ ነገር ግን የአባቶችን ቡራኬ ያላገኘ ፖለቲከኛ ዓለም ትደፋበታለች ባንልም ቢያንስ በዚያ በኩል ሊያገኝ የሚችለውን ድጋፍ ያጣል። ፖለቲከኛው ጴንጤ ወይንም የእስልምነ እምነት ተከታይ ቢሆንስ? መስቀላቸውን ባይሳለም እንኩዋን ቀረብ ብሎ የአባቶችን ሀሳባቸውንና ምክራቸውን መስማት ይገባል። እየተናገርኩ ያለሁት የሆነውንና ሊሆን የሚችለውን ነው። መሆን ይገባዋል ማለቴ አይደለም። ትክክል ነበር እንደማለት እንዳይወሰድብኝ እንጂ፡ አጼ ቴዎድሮስን ከካህናት ጋር የነበራቸው ጸብ በክፉ ጎድቷቸዋል። የስልጣን እድሜያቸውንም አሳጥሮታል። ከዚህ አንጻር እነሆ በዚያ ዘመን በአጼ ቴዎድሮስ የደረሰ በዚህ ዘመን በኛም እንዳይደርስ ለስልትም ቢሆን አባቶችን እንጠጋ። አባቶች ምእመናን ከጎናችን ሊያሰልፉ ይቻላቸዋል። አባቶች አጀንዳችንና አካሄዳችን ካልተመቻቸውም ትግላችንን ከጠላትም በላይ ያወሳስቡታል። ስለዚህ ወደ እምነት ተቋማት እንጠጋ ነው ነገሩ።
ከዚህም ከዚያም፤ እንደ ማሳረጊያ
እነሆ ሲያትል አኮራን። ካልግሪም አስደመመን። ፖርትላንድም አስደነቀን። ለከርሞ ደግሞ ኤድመንተንም ይመጣል። ዊኒፔግም ይከተላል። ቶሮንቶና ኦታዋም አይቀርም። እነሆ በቶሮንቶ በጣገብ በኦንቴሪዮ ግዛት በኪችነር ከተማ ያሉ ዴሞክራሲ ወዳድ ምእመናን አኛ በቫንኩቨር ያለፍንበትን መከራ በነሱም እንደደረሰና ጉዳያቸው ወደፍርድ ቤት እንዳመራ ሰምተናል። ቤ/ክኑን ያቋቋሙት የኢትዮጵያ ቤ/ክ በካናዳ የበላይ ጠባቂ አባ ምሳሌ እንግዳ ሆነው ሳለና በየጊዜውም እየተመላለሱ እየቀደሱ ለወግ ማእረግ ካደረሱት በኋላ ያው እንደተለመደው ባንድ በኩል ኢህአዴግ አረደን፣ ኢህአዴግ ሰቀለን፣ ህወሀት አሰቃየን አባ ጳውሎስም ከቤተክርስቲያናችን አባረሩን ብለው ኬዝ ሰርተው በኬንያም በሱዳንም በዩጋንዳም ብለው እዚህ መጥተው መልሰው ደግሞ ከአባ ጳውሎስ ጉያ ገብተው የሚተሻሹ ጥቂቶች እነሆ ቀምተዋቸዋል። በቅርቡ ዝርዝሩንና በሁሉም ወገን የድራማውን ተዋናዮች ሚና በድረ-ገጾች ላይ እናወጣለን። እስከዚያው ግን አሁንም ለአባቶች መልእክት አለን።
አባታችን ሊቀ ካህናት ምሳሌም ቤተክርስቲያን በየቦታው ማቆማቸው መልካምና የሚደነቅ ሆኖ ሳለ ባግባቡና ጥርት ባለ መልኩ አስተዳደራዊና ቀኖናዊ ጉዳዮችን ሳይቋጥሩና የቤተክርስቲያኗን ግንኙነት እንዲሁም የሲኖዶስንና ፓትሪያርክን ጉዳይ በቅጡና በግልጽ ሳያትሙ በመሄዳቸው ምክንያት በየግዜው የሚፈጠረውን ችግር ሊቀርፉት ይገባል። ቤ/ክ ከተቋቋመ በኋላ ቤ/ኗ ከማን ወገን እንደሆነች፤ የሚመጡም ካህናት ተጠሪነታቸው ለማን እንደሆነ፣ ፓትሪያርካችንም አቡነ መርቆሪዎስ እንደሆኑ፣ ሲኖዶሱም በስደት እንደሚገኝ በደንብ አስምረው በመተዳደሪያ ደንብ ሊቋጥሩ ይገባል። ይሄ የተድበሰበሰ ነገር መተው በብዙው ጎድቶናል። በየጊዜውም ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ይገባል እንጂ ምእመናን ለፍተውና ገንዘባቸውን አውጥተው ቤ/ክ ከሰሩ በኋላ ከኋላ በሚመጡና ቤ/ኑን ለማቋቋም ምንም ባልለፉ ሰዎች ሲነጠቁ ማየት የለባቸውም። ያ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ፡በዚህ በቫንኩቨር የደረሰ አይደርስም ነበር። በኪችነርም የተጸነሰው ያ ነው። ይሄ በዳላስም፤ በአውስትራሊያም፤ በሌሎችም ቦታዎች እንደደረሰ ሰምተናል። አንዳንዱን የኛ ወገን አሸንፏል። አንዳንዱን ግን ተሸንፈናል። ለነገሩ ብናሸንፍም ብንሸነፍም፤ ያሸነፍንም የተሸነፍንም እኛው ነን። ያለነውም የሞትነውም እኛው ነን እንዳሉት መሆኑ ነው ጃንሆይ።
ቅዱስ ሲኖዶሳችን፡ በመጪው ጥቅምት በኮለምበስ ኦሀዮ እንደሚሰበሰብ ሰምተናል። ሲኖዶሱ ሲሰበሰብ ይሄንን ጉዳይ ሊመክርበት ይገባል። ጠንካራ የሆነ የህዝብ ግንኙነት ስራም ያስፈልገዋል። የሲኖዶሱን መኖርና መስራት ልናውቅ የምንችለው ሲኖዶሱ በየጊዜው በሚያወጣቸው መግለጫዎች፤ አባቶች አቅማቸው የተዳከመ ቢሆንም በየቦታው እተንቀሳቀሱ በሚሰጧቸው ትምህርቶችና ጉባኤዎች እንዲሁም በየመድረኩ ባላቸው ተሳትፎ ነው። ያለበለዚያ ጠላት አይሎ መድረኩን ሁሉ ይቆጣጠርብናል። ኢትዮጵያ ውስጥ አቅምም የለንም። እዚህ ግን አገሩ የእኩልነት ነው። አንዱ ሁሉንም ጠቅሎ የሚወስድበት አገር አይደለም። ቢሆንም ግን እለት እለት ባይሆን በየወሩ መግለጫና ቡራኬ ቢጤ ጣል ሊደረግብን ይገባል።
መቼም አባቶች አገር እንደሌለው ሰው አገራችንንና መንበራቸውን ተነጥቀው በሰው አገር በስተርጅና መንከራተቱን ወደውት አይመስለኝም። ስለዚህ ቤ/ክ ወደ አገራችን በድል የመመለሱን ትግል ልትመራ ይገባል። ታንክና መድፍ መተኮስ ባይችሉ ቀንጌልና ቃለ እግዚአብሄር መተኮስ አይሳናቸውም። አባታችን ለምሳሌ በወር አንዴ እንኩዋን መኖራቸውን በመገናኛ ብዙሀን ቢያሰሙን ለኛ ለተከታዮቻቸው መልካም ነው። እድሜዎትን ባሉበት ያቆይልን። ወይ ደግሞ ኮለምበስ መጥተንም የሲኖዶሱን ጉባኤ እንጽፋን። አባታችን እንደውም በኮለምበስ አካባቢ ካሉ ልክ እንደ ሲያትል ምእመናን የኮለምበስን ምእመናን ባርከውና አስታጥቀው ያንን መናጢ መለስ የበላው ይመለስና እንዲቃወሙ መላክ አለባቸው። ለነገሩ ኮለምበስ እንኩዋን የሚስቲቱ አገር ነው ብለዋል። ስለዚህ ከሚሰለፍበት የሚሰለፍለት ሳይበዛ አይቀርም። ነገር አስረዘምኩ መሰለኝ? ከምኔው ከቫንኩቨር ተነስቼ እዚያ ኮለምበስ ደረስኩኝ? በቃ። ሰላም ሰንብቱ።
መስከረም 23፡ 2009



