አለቃ ተክሌ

እነሆ ቅድስት ማርያም በቫንኩቨር ልትከብር ነው

ሰንጋው ተመርጧል፤ ቢላ ተስሏል

ሰንጋው ተመርጧ። ጋሽ ከቤና ሙሌ ናቸው የመረጡት። ጋሽ ከቤ ባለፈው ወደ ዲሲ ለመስከረም 3ቱ ሰልፍ ሊያመራ ሲያኮበኩብ የነበረው ከበደ ሀይለማሪያም ነው። እህቶቻችንና እናቶቻችን እኛን ወንዶቹን ወደምድጃ አናስደርስም ብለው ወገባቸውን አስረው ተነስተዋል። እዚህ ከምእራቡ ዓለም ሁላችንም ጾታችን አንድ እንደሆነ አላወቁም። ወይ ሁላችንም ሴቶች ነን። ወይም ሁላችንም ወንዶች ነን።

 

አርብ ወጥ ይወጠወጣል፤ ለትእይንት የሚቀርቡት ፎቶግራፎችና ስእሎች ተዘጋጅተዋል፤ ማስታወቂያዎች ለሚመለከታቸው ሁሉ ተበትነዋል። ትኬቶች ተሸጠዋል። ወደ አምስት መቶ አበሻ ወደ ሶስት መቶ ፈረንጅ ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል። በተለይ ሲያትልን በጉጉት እየጠበቅን ነው። ፖርትላንዶችና ካልጋሪዎችም ተሳስተው ሊመጡ ይችላሉ እንላለን። አሁን ወደ ድረ ገጽ ከመሰቀላችን በፊት የደረሰን መረጃ እንደሚጠቁመው ከሆነ ካልጋሪዎችና ኤድመንተኖች ተነስተዋል። ቤተ/ክርስቲያናችን በዓሉን ባሮጌ አልባሳት አታከብርም ተብሎ፡ መጋረጃዎች እየተሰፉ ነው። እነሆ ዛሬ ማታ የመጨረሻውን ስብሰባ እናደርጋለን።

 

ቫንኩቨር ኢትዮጵያዊያንንና የኢትዮጵያን ወዳጆች ለማስተናገድ እየተሰናዳች ነው። ይሄ ሁሉ ግርግር ለምንድነው? ትንሽ ታገሱ ልብ ሰቀላ መሆኑ ነው። ትናንት ለኳስ ነበር፤ ለስጋችን። ለኳስ የመጡትን እነሱን ሸኘን። ደግሞ ለነፍሳችንም አምልኮ ያምራታል። በየዓመቱ የምትከበረው ጸዴንያ ማርያም በኛ አቆጣጠር መስከረም 9ኝ እዚህ ቫንኩቨር በደመቀ ሁኔታ ትከብራለች። ለዚያ እየተሰናዳን ነው። ታዲያ ምን ይሄ ሁሉ ሀተታ አስፈለገ? እነሆ ነገሩ።

 

ትንሽ ወደኋላ፡ የቀደመውን ማወቅ ያሁኑን ለማሞቅ ይረዳል

ታስታውሳላችሁ እኛ ገለልተኛ ያልሆንን ከብሪቲሽ ኮሉምቢያ ጠቅላይ ፍርድቤት ቫንኩቨር-ካናዳ በወርሃ ሚያዚያ/09፡ የዛሬ አምስት ወር አካባቢ ማለት ነው፡ “የቫንኩቨር ቅድስት ማርያም ቤ/ክ ውዝግብ በፍርድቤት መሰማቱን ቀጥሏል” ብለን ስንዘግብ? አዎ ታስታውሳላችሁ። የማታስታውሱም ዛሬ ላስታውሳችሁ። ከዚያ በፊትም በ2008 ጥቅምት ወር መሰለኝ የክርክሩን መጀመር አውስተን ነበር። እነሆ ክርክሩ አልቋል። ፍርድ እየጠበቅን ነው። እስከዚያው ግን ማን ይተኛል? እነሆ የቫንኩቨር ቅድስት ማሪያም ቤ/ክ በመጪው ቅዳሜ መስከረም 9 ቀን 2002 ዓ.ም. (September 19, 2009) ጉደኛ ድግስ ደግሳ የአካባቢውንና የጎረቤት ከተሞችን ምእመናን ሰብስባ ታላቅ የበዓልና የገንዘብ ማሰባሰቢያ ውሎ ልታደርግ ሽር ጉድ ይዛለች።

 

በነገራችን ላይ የዚህ ጽሁፍ ጸሀፊ ከቤተክርስቲያኒቱ ሰበካ ጉባኤ ቡራኬ አልተሰጠም። ስለዚህ በዚህ በምንጽፈው ነገር ሀላፊነቱ የኛ ነው። እኔና እኛ ደግሞ ፍላጎታችን ግልጽ ነው። ይሄ የሀይማኖት ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ ይሄ የክርስቲያኖችም ብቻ አይደለም፤ ይሄ የቫንኩቨር ጉዳይም ብቻ አይደለም። ይሄ ይሄንን ጨቋኝ ስርአት የሚፋለሙ ሀይሎች ሁሉ ነው። በቫንኩቨር ከተሸነፍን በየትም አንረታለን። ቫንኩቨርን ካቀናን ሌሎችም ሁሉ ይበረታሉ። በቅድስት ማሪያም የደረሰ፤ በቅዱስ ገብርኤል አይድረስ። በቫንኩቨር የደረሰ፤ በሌሎችም እየሆነ ያለ ነገር ነውና ነው እንዲህ ወጥረን መያዛችን።

 

ትንሽ ለማስታወስ፤ የነገሩ አመጣጥ

ኦኬ፡ ታሪኩን ለመጀመሪያ ግዜ ለምታነቡ፡ ነገሩ እንዲህ ነው። በ199ዎቹ አካባቢ፡ የቫንኩቨር ቅድስት ማሪያም ቤተክርስቲያን በኢትዮጵያ ቤ/ክ በካናዳ ስር በሊቀ ካህናት ምሳሌ እንግዳ ተባባሪነትና በኋላ ላይ በአቡነ ዜናማርቆስ ቡራኬ ተቋቋመች። ሲፈጠርም ጀምሮ ቤተክርስቲያኗ ከአባ ገብረመድህን/አባ ጳውሎስ ህበረት አልነበራትም። እነሆ እንደ ከሳሽ ወገን ክስ ከሆነ ዘመዶቻችን ቀስ በቀስ ገቡበትና ማንም ሳያውቅ ማንም ሳይሰማ እኚያን ተንኮል ያልገባቸው ግን ደግሞ ደካማ የቤተክርሰቲያኗን መነኩሴ አጃጅለው የቤተክርስቲያኗን ስምና መተዳደሪያ ደንብ ለውጠው፤ ያቺ ቤተክርስቲያን እያለች ነገር ግን በዛችው ቤ/ክን ንበረት እንዲሁም ጽላት እንዲሁም ገንዘብ፣ እንዲሁም ምእመናን ስም፣ ሌላ አዲስ ቤተክርስቲያን በብሪቲሽ ኮሎምቢያ አቋቋሙ። በ2005። ለህዝቡ አልተነገረም። አልተገለጠም።

 

በኋላ ላይ መነኩሴውም ነገሩ ሲገባቸውና እንደተታለሉ ሲያውቁት ዘራፍ አሉ፤ ነገሩም ተጋለጠ። በሽምግልና ቢሞከረም ችግሩ ሊፈታ አልቻለም። ስለዚህ ጉዳዩ ወደፍርድ ቤት ሄደ። ከሳሽ ቀድሞም የነበረችው አሁንም ያለችው ኆህተ ሰማይ ቅድስት ማሪያም ቤ/ክ ነች ባይ ነው። ተከሳሽ የአዲሲቷ ማሪያም የቀድሞ ሰበካ ጉባኤ አባላት እነተክላይ፣ እነታሪኩ፣ እነኤርሚያስና ሌሎችም የለም ራሳችንን ችለን በህዝቡ እውቅናና ፈቃድ አዲስ ቤ/ክ አቋቁመናል ባይ ናቸው። ብዙ አጨቃጫቂ ነገሮችን ተመልክተን ነበር በወቅቱ፡ አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው።

 

ቤተክርስቲያኗ ቀደም ሲል በማን ስር እንደነበረችና በማን ስም እንደሚቀደስ፤ ስለትክክለኛው ሲኖዶስ፣ ስለአቡነ መርቆሬዎስ፣ ስለአቡነ ይስሀቅ፣ ስለምእመናኑ፣ አባል ስለሆኑና ስላልሆኑትም ሰዎች በክርክሩ ወቅት በምስክርነት የቀረቡት ሰዎች ተጠይቀው ነበር። እነሱም መልሰዋል። እነሆ ህወሀት/ኢህአዴግ በሄደበት ምስክር አያጣም። ለምሳሌ ብዙዎቹ የተከሳሽ ምስክሮች ስለ ፓትሪያርክ ጉዳይ ግማሹ እኔ አላስተዋልኩም ሌላው ደግሞ ሁለቱንም ሲጠሩ ተመልክቻለሁ አሉ። ስለሲኖዶስ ደግሞ፤ ስለሕጋዊው የውጪ ሲኖዶስ አናውቅም። እዚህ ከመጣን በኋላ በተለይ ከ2006 ወዲህ ሰምተናል አሉ። 2006 በውጭ ጳጳሳት የተሾሙበት ወቅት መሰለኝ።

 

ውጭ አገር ይኖሩ የነበሩ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ስደተኞች ነን ብለው ኬዝ ሰርተው ካናዳ የገቡ ሰዎች ስለኢትዮጵያ ቤ/ክ ውዝግብ አናውቅ ስለትክክለኛው የስደት ሲኖዶስ አላውቅም ሲሉ አሳዘነን። ስለአባላት፡ (ይህቺኛዋ በጣም የምታበሰጭና በየቦታው የምትነሳ ነገር ነች)፡ በ2004 የመጣው አንዱ ምስክር እነዚያ ቡናና ሻይ ሸጠው ቤተክርስቲያኑን ያቋቋሙትን ምእመናን አላውቃቸውም አለ። “ጭራሽ አይቻቸው የማላውቀው ቤተክርስቲያን መጥተው የማያውቁ ሰዎች ናቸው” የበጠበጡን። ሲል ቃሉን ሰጠ። በነገራችን ላይ ከዚህ ውዝግብ የምንማረው ዋናው ነገር በየቤተክርስቲያናቱ የምትማልዱ ሁላ የአባልነት መታወቂያችሁን አግኙት። ያለበለዚያ ምን ብርና ላብ ስታዋጡ ብትኖሩ መደበኛ አባል ካልሆናችሁ ከኋላችሁ የመጡት ብልጦቹ እነብርሀኔ እና እነመድሀኔ ይፈነግሏችኋል። ያ ነው በቫንኩቨር የተከሰተው። ዳላስ በደንብ ስማ። ዴንቨርም ልብ ብለህ አድምጥ።

 

ለነገሩ፤ ገለልተኛ መሆን ይቻላልን?

ቀደም ሲል የቀረቡ ዘገባዎችን www.ethiopiazare.com ሄዳችሁ ተመልከቷቸው። ለማስታወስ ያህልና አንዳንዶቹ ነጥቦች እጅግ አስፈላጊና ዛሬም ድረስ አስፈላጊዎች በመሆናቸው ልንደግማቸው ወደናል። ይሄ ጽሁፍ በገለልተኛ ወገን የተጠናቀረ አይደለም። ለነገሩ ኢህአዴግን እየታገሉ ስለገለልተኛነት መናገር ቅንጦት ነው። ዘገባውን ሚዛናዊ ለማድረግ ብንሞክርም ሙሉ በሙሉ ሚዛናዊ ነው ብለን ቃል አንገባም። አንድ ነገር ማለት ግን እንወዳለን። ከዚህ ቀደም ለምእመናን ይሄንን መልእክት አስተላልፈን ነበር።

 

በየቤተክርስቲያናችሁ ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ። መደበኛ አባል ያልሆናችሁ በመጪው እሁድ ሂዱና መደበኛ አባል ሁኑ። ያለበለዚያ የለፋችሁባቸውን አብያተ ክርስቲያናት ጠላት ይነጥቃችኋል። አገራችንን ቀሙን፤ ቤተክርስቲያናችንንና አድባራቱን ቀሙን፤ አሁን ደግሞ በዚህ በስደት የገነባታን ስደታችንንና ቤተ ክርስቲያናችንን ሊቀሙን ነው እንዴ ብለን አስጠንቅቀን ነበር። ለአባቶች ደግሞ እንዲሁ አታንቀላፉ። አትሳነፉም። ንቁ ብለን መልእክታችንን አስተላልፈን ነበር። አሁን አባታችን አቡነ ዮሀንስና ዲያቆን ወንድማችን በየጊዜው ከሲያትል ያለምንም ውሎ አበል፤ ያለምንም ክፍያ እየተመላለሱ ለቫንኩቨር ምእመናን የሚሰጡት ቡራኬ እጅግ የሚደነቅ ነው። ሌላው አባታችንም አቡነ ሚካኤል ከካልግሪ ድረስ እየተመላለሱ አገልግለውናል። ባርከውምናል። ብድር ይግባቸው እንላለን። ትንሽ ወርጄ ግን ለበላይ ጠባቂዎች ወቀሳና ጥሪ አለኝ።

 

ግን ይሄ የኔ ቅስቀሳ ነው፤ የማንም አይደለም

ይሄ መልእክት በግል አነሳሽነት በኔ በዲያቆን ተክሌ የተጠናከረ እንጂ፡ የቫንኩቨር ኆህተ ሰማይ ቅድስት ማሪያም ሰበካ ጉባኤ እጅም፣ እግርም፣ ቡራኬም በርታም የለበትም። ስለዚህ ለተባለው ለተጻፈው፡ ለቀረበው ነገር ሁሉ ተጠያቂው እኔ ነኝ። እኔ የቀድሞው ዲያቆን ተክለሚካኤል አበበ። ድቁናዬ የምር ነው በነገራችን ላይ። ኬንያ ባላፈርሰው ኖሮ። ግን እዚያ ቢፈርስም መፍረሱ አይቀርለትም ነበር። ባለፈው ቀን አንድ በአባ ገብረመድህን/ጳውሎስ የወጣ መግለጫ ሳነብ ነበር፤ እኛ በአቡነ መርቆሬዎስ ስር የምንገኝ ዘረ-ካህናት በሙሉ ክህነታችንን መነጠቃችንንና ውጉዝ ከመ አርዮስ መባላችንን ያስተዋልኩት።

 

የዛሬ 19 ዓመት ሀምሌ ወር 1983 ዓ.ም. አቡነ ገብርኤል ናቸው ዝዋይ ሐመረ ብርሀን ገዳም ለሀምሌ ገብርኤል ሄደን የድቁና ክህነት የሰጡኝ። ትዝ የሚለኝ ታላቁ አባት አባ ጎርጎሪዎስ በመኪና አደጋ ከሞቱ በኋላ አቡነ ቄርሎስ ከዚያ አቡነ ገብርኤል መጡ። እኔና አንድ አስር የምንሆን ታዳጊዎች ዘንድሮ ክህነት አይሰጥም ጳጳሱ አዲስ ናቸው ተብለን ተስፋ ቆርጠን አዝነን ወደ ነጌሌ ልንመለስ ስንል መልአኩ ገብርኤል ኤጲስ ቆጶሱን ላከልንና አስቀረን። በነጋታው ክህነት ተሰጠን። ያኔ ባንካን እጅግ በጣም ከማዘናችን የተነሳ እምነታችንን ልንቀይር ሁሉ እንችል ነበር። እህ ልክ ነዋ። ሸንኮራ ሽጠን ያጠራቀምናትን ገንዘብ ሰውተን ነው ከነጌሌ ዘዋይ የተጓዝነው። ከአውቶብስ ወጪያችን ባሻገር የሚያውቅ ሰው መያዝ ስለነበረብን ከኛ ቀደም ብሎ ክህነት ለተቀበለው ጎበዝ ግን ብልጥ ዲያቆን የመሪጌታ ታዬ ልጅ ትንሽ ጉርሻ መስጠትና የአውቶብስ መክፈል ነበረብን። ስለዚህ ክህነት ሳንይዝ ብንመለስ ትንሽ ሞራላችን ብዙ ይደማ ነበር። ግን ተካንን።

 

ያንን ክህነት ጠብቄ አንድ ስድስት ሰባት ዓመት ቀድሻለሁ። አሁንም አባቶች የሚባለውን ካሉልኝ፡ ክህነቴ ሊቀጥል ይችላል። እስከዚያው ግን የቫንኩቨር ኆህተ ሰማይ ቅድስት ማርያም ቤ/ክ ማበብ አለባት። ምክንያቱም በቤተክርስቲያኗ ምክንያት የገጠምነው ህጋዊ ፍልሚያ የኛ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያዊያን ሁሉ ነውና። የዛሬው ጉዳይ አስቸኳይ ነው። የቫንኩቨር ቅድስት ማርያም ቤ/ክ ክብረ በዓል።

 

ቤታችን በሰማይ ነው? በምድርስ?

ከወቀሳዬ በፊት ትንሽ አተታ ልጨምር። ከሀይማኖት ስብከትና ትምህርት ሁሉ የሚያናድደኝ የቱ እንደሆነ ታውቃላችሁ? ቤታችን በሰማይ ነው የሚለው ትምህርት። አገራችንም እንዲሁ። ማንንም ለመንካት አይደለም። አመለካከቱን ብቻ ለመጸየፍ እንጂ። ቤታችንም አገራችንም በምድርም በሰማይም ነው ይሻላል። ዘፈንና መዝሙር አንድ ናቸው። የሚለያየው ሰዓቱ ብቻ ነው። ስንጠጣ ከሆነ ዘፈን ነው። ስናመልክ ከሆነ መዝሙር ነው። እንዘፍናለን ግን እንዘምራለን። አብዱ ኪያር መጣ። አጫወተንም። አብዱ ኪያር ግን ሄደ። ሕይወት ግን ቀጠለ። እንጫወታለን። ግን ደግሞ እንሰራለንም።

 

ብርቱካንን ሸለምናት። የብርቱካን ሽልማት ከስጋና ነፍስ ጨዋታ መሀል ያለ ጉዳይ ነው። ለነፍስም አይደለም ለስጋም አይደለም። ለህሊና። ለሞራል። ለትግል። ለዚህ ነው ትናንት ለስጋችን የተጫወትነው። ከአብዱ ኪያር ጋር። ዛሬ ደግሞ ለነፍሳችን እንሰራለን። ለነገሩ በነፍስና ስጋ መካከል ያለ ልዩነት እየተጭበረበረብኝ ነው። ነፍስ ስጋ አይደለምን? ስጋስ ነፍስ አይደለችምን? ይሄ ሰማይና ምድርን ፍየልና በግን የሚለያይ የህይወት ፍልስፍና ይጎመዝዘኛል። አይገባኝምም። የሆነ ሆኖ እሱን ላቁምና ወደ ቫንኩቨር ድግስ ልመልሳችሁ። ቫንኩቨር እንቅልፍ የለም። የምንደርስበት እስክንደርስ አንተኛም። የማይተኛ ጠላት አለንና። ዲያብሎስም ሕወሀትም አይተኙልንም። ለዚህ ነው ቫንኩቨርም ለጠላቶቿ ዲያብሎስን መሆን የመረጠችው። ያው ጠላት እንደዚያ ነው የሚያየን እኛ እሱን እንደምናየው።

 

አባቶች፤ እንዳይከፋችሁ እንጂ ትንሽ ቅሬታ አለኝ

አባቶች በተለይ በሲኖዶሱ አስተዳደር ስራ ላይ የተቀመጡ አባቶች እነ አቡነ መርቆሪዎስ፣ እነ አቡነ መልከጼዴቅ፣ እነ አቡነ ኤልያስ፣ በየቤተክርስቲያናቱ እየዞራችሁ በቀላጤም እየጻፋችሁ ህዝባችሁን አንቁ እንላለን። ከዚህ ቀደም እንዳልነው፡ “እነሆ የናንተን ውጊያ እኛ ብቻችንን አንዋጋም። መኖራችሁን የሚያሳይ ስራ ስሩ። ቡራኬ፣ መግለጫ ስጡ። ስብሰባም፤ ጉባኤም ጥሩ። ሰልፍም አሰልፉ አንዳንደዜ። አብዛኛው የኛ ህዝብ የዋህ ነው። ተንኮል አያውቅም። ተንኮል አያስብም። ጥቂቶች ግን መጥተው፡ በገለልተኛ ነን ስም ያምሱታል። ያንን የማመስ ስራ ደግሞ ያሚያስተባብሩላቸው የኛ ሰዎች ናቸው። የኛ ባንድ በኩል ኢህአዴግን አጥብቀን እንጠላለን የሚሉ በሌላ በኩል ግን ከነሱው ጋር በሰበብ አስባቡ የሚተሻሹ ሰዎች። ስለዚህ እባካችሁ ምሩን” ብለን አሳስበን ነበር።

 

ስለአባቶች ከተነሳ አይቀር ከዚህ ቀደም ኮለምበስ ኦሀዮ ሄጄ አንዲት እህት ስለቤተክርስቲያን ጉዳይ ስንነጋገር አባቶች ትንሸ ሞራላቸው ሳይነካና ተስፋ ሳይቆርጡ አይቀርም ብላኛላች። ምክንያቱም ይሄንን ነገር ማድረግ እንችላለን ጠላትንም እናሸንፋለን ብለው በሞራልና በንቃት ያለመታከትና ያለመሰልቸት ዋናውን ተጋድሎ ሲመሩ አይስተዋሉም። ያም ብቻ አይደለም ከሌላ ለቤ/ክ ቅርበት ካለው ወገን እንደሰማሁት ይሄ ፖለቲካችንንም የሚያምሰው እከሌ ከሸዋ ነው እከሌ ደግሞ ከጎንደር የሚለው የመንደር ሽኩቻም ትንሽ ጎድቶናል የሚል ክስ አለ። መቼም የቤታችንን ገመና ባደባባይ አውጥቶ መተርተር ሰድቦ ለሰዳቢ መስጠት ነውና ከዚህ አንጽፈውም። አባቶች ግን መኖራቸው እንዲሰማ አድርገው እየመሩ አይደለም የሚል ክስ አለ። አባቶች እባካችሁን ታዩን።

 

ወደቅዳሜ እንመለስ፡ ከዋዜማው እንጀምር

አርብ ለቅዳሜ አባቶችና በመቶዎች የሚቆጠሩ ምእመናን ከሲያትልና ከካልጋሪ ሌሊቱን ገብተው ያድራሉ። ዝግጅታችን በታላቁ የአንግሊካን ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ ይካሄዳል። ቅዳሜ መስከረም 9 ቀን (ሴፕቴምበር 19) ጠዋት ስርአተ ቅዳሴና የእመቤታችን በዓለ ንግስ ይከናወናል። ምሳ እናደርግና ከሰዓት በኋላ ስለቤተክርስቲያናችንና አገራችን ታሪካዊ አመጣጥና ሂደት የሚያስረዳ ዶኩመንታሪ ፊልም ይታያል። ወጣቶች መዝሙርና ወረብ ያሳያሉ። ያሰማሉም።

 

በነገራችን ላይ አጋጣሚ ሊሆን ይችላል የአንግሊካን ቅዲስ ሚካኤል ቤ/ክ ማለት ከዚህ ቀደም አንድ ካናዳ በጥገኝነት አልቀበልህም ያለችው ኢራናዊ ለሶስት ዓመት የተሸሸገበትና በኋላ ፖሊስ ለሌላ ጉዳይ ገብቶ ሲይዘው ህዝቡ እንዴት ምን ሲደረግ ብሎ ወጥቶ ካናዳ በጥገኝነት እንድትቀበለው ያደረገበት ቤ/ክ ነው። ስሙ አሚር ካዝሚያን ይባላል። የካናዳ ኢሚግሬሽን ባለስልጣን የጥገኝነት ጥያቄውን አልቀበልም ቶሎ ካናዳን ለቀህ እንድትወጣ ሲለው በ2004 ዓ.ም. ከዚያ ቤ/ክ ገብቶ ይጠጋል። አይገርማችሁም? ፖሊስ ወይንም የሚመለከታቸው ባለስልጣናት ከቤ/ክኑ ገብተው እንዳይዙት የሚያግድ ምንም አይነት ህግ የለም፤ በካናዳ። ግን የፍ/ቤት ማዘዢያ እያለ ራሱ ፖሊስ ለሶስት ዓመታት ሳይነካውና የቤተክርስቲያኑን ቅጽር ግቢ አክብሮ ቆየ።

 

በጓደኞቼ በ2001 ዓ.ም. በቅድስት ማሪያም ቤ/ክርስቲያን አምስት ኪሎ ለዚያውም በአባ ጳውሎስ ግቢ ስር የደረሰው ግን ተቃራኒው ነው። ሶስት ሺህ አምስት መቶ ጓደኞቼ ባአባ ጳውሎስ አፍንጫ ስር ታፈሱ። በወርሃ የካቲት 2007 ዓ.ም. ይሄው ኢራናዊ እርዳታ ፈልጎ ፖሊስ ይጠራል። ፖሊሱ ስሙን ከኮምፒውተር ላይ ሲያጣራ የተቆረጠበትን የእስር ማዘዣ ያገኝና አስሮ ይወስደዋል። በኋላ አገር እሪ አለ። ምን ሲደረግ? ቤ/ክን ተደፈረች ተባለና ሰልፍ ተወጣ። በዚያው አጋጣሚ ይሄ ኢራናዊ መባረሩ ተሰረዘና ቀደም ሲል የተከለከለውን ጥገኝነት አገኘ።

 

እንግዲህ በዚህ ታሪካዊ ቤ/ክ ቅጽር ግቢ ነው ቅዳሜ የምናመልከው። የምንሰባሰበውም። በልዩ ሁኔታ መስከረም 9 ቀን። በዘወትር ደግሞ ቅዳሜ ቅዳሜ። ግን ታውቁታላችሁ፡ የቅዳሜን ነገር። አብዛኛው ሰው እሁድን ነው የሚያርፈው። ስለዚህ አገልግሎታችንን ከቅዳሜ ወደ እሁድ ማዛወር፡ እንደምንም ደግሞ አንድ አገልጋይ ቄስ ማግኘት አለብን ብለን ቆርጠን ተነስተናል። እስካሁን አልፎ አልፎ ከሲያትል ደግ አባታችን ሲመጡልን እንጂ በካሴት ነው የምንቀድሰው። ለዚያውም በድሮው ካሴት። አናሳዝንም? ስለዚህ እርዱን። እዚህ በአካባቢያችን ያላችሁ በመምጣትና በመሳተፍ እርዱን። እዚያ ሩቅ ያላችሁም፡ በተለያየ መልኩ ልትረዱን ትችላላችሁ። ለምሳሌ፡ መገኘት ባትችሉም የተዘጋጀውን የመግቢያ ትኬት ብትገዙን ትልቅ እርዳታ ነው። የሚያሳዝነው ነገር የተዘጋጀውን ብፌ ምግብ አትቋደሱም። ግን ባላችሁበት የበረከቱ ተካፋይ እንዳትሆኑ የሚያግድ ነገር የለም። እንግዲህ መምጣት የምትችሉም የማትችሉም ምእመናን የናንተን እርዳታ እንሻለን። የምትመጡ ኑ። የማትመጡም እርዳታችሁ ይምጣ። እጃችሁን ስደዱ።

 

ስለዚህ የእርዳታ እጃችሁን ለግሱልን። ለ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. or This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ኢሜል ብታደርጉ የሚመለከታቸውን የቤ/ክ ሰዎች ልናገናኛችሁ እንችላለን። ግን ልብ አድርጉ ይሄ የኛ ቅስቀሳ እንጂ የቤተክርስቲያኗ አስተዳደር እጅ የለበትም። ስለዚህ እኛ የምንሰጣችሁ መረጃ ብቻ ነው።

 

ቸር እንሰንብት። መልካም በዓል። ዛሬ ዲያቆን ተክሌ ነኝ። ወይም አለቃ ተክሌ።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ