ከቫንኩቨር እስከ ዳላስ: ከግንቦት ሰባት እስከ ግንቦት ሀያ
የጳውሎስ ማላገጥ፡ የመረራና ብሬ ቁጣ
ሕወሀት ከደርግ አምባገነን አገዛዝ ነጻ ባወጣን (ተረጋጉ፡ አልጨረስኩም)፡ እንደገና ግን ወደ ሕወሀት ቀጣይ የባሰ አምባገነንና ዘረኛ ስርአት በተሸጋገርን ባስራ ስምነተኛው ዓመት፡ ዳላስ፡ ቴክሳስ ውስጥ፡ ከዶ/ር ብርሀኑ ፊትና ጎን ተቀምጠናል። ታሪክ ማጠንጠን ጀመርን።
ከደርግ መውደቅ አስራ አራት አመት በኋላ ስለተከሰተ ታሪክ በመተረክ ጨዋታ ጀመርን። ብርሀኑ ነጋና መረራ ጉዲና (ዶ/ሮች) ከአሁኑ “አባታችን” ቢሮ ቁጭ ብለዋል። አንዱ ቅንጅትን ወክሎ፡ አንዱ ሕብረትን። “ዳመራ ላይ እኮ ሰደቡኝ” አሉ አባ ጳውሎስ ከመንበረ ስላሴ መቀመጫም ከፍ ብሎ በተሰቀለ መቀመጫቸው ላይ ተሰቅለው። ዶ/ር ብርሀኑን፡ ብሬ ነው የምለው። ብሬን ጠጋ ብላችሁ አስተውላችሁታል? የማይጥመውና የማይመስል ነገር ሲነገር ሲሰማ ፊቱን ከስክሶ፡ ከንፈሩንና ግንባሩን አስተባብሮ የሚያይበት የምጸትና የተቃውሞ አስተያየተ አለው። ፊቱን ከሰከሰው። አዞረባቸውም። እነሆ ከብሬ ጋር ተጫወትን። ከዶ/ር ብርሀኑ ጋራ ጨዋታ አይጠገብም። እድል ካልተሰጠው በስተቀር፡ ብዙ አይናገርም። ያዳምጣል። ከኛ የተሻለ ሊያውቀው በሚችለው ነገር ላይ እንኩዋን “እስኪ ዶ/ር ምን ትላለህ?” ካላልነው በስተቀር ለመናገር አይንቀለቀልም።
አስተያየት ሲሰጥም ሚዛናዊ ሆኖና ከልምድ፡ ከግኝት ከእውነት ተነስቶ ነው። በትክክል የዛሬ አራት አመት፡ ሕወሀቶች ለመስዋእትነት ሊያቀርቧቸው ሲሰናዱ፡ ለሽምግልና ይሁን ለምን፡ በደንብ ላልሰማሁት ጉዳይ፡ አባ ጳውሎስና ሌሎች የሀይማኖት መሪዎች ባሉበት ስብሰባ ተቀምጠው ነው፡ በላይኛው ክስ ሀሳባቸውን የጀመሩት። አባ ጳውሎስ፡ አባ ገብረመድህን፡ ከዳመራ መልስ። “ዳመራ ላይ ሰደቡኝኮ” ። “ርሰዎ ይሄን ያህል ሰው ሲደገል፡ ይሄንን ያህል ሰው ሲታሰር፡ ይሄንን ያህል ሰው ሲታፈን ምንም ሳይሰማዎትና ሳይናገሩ፡ እንዴት ዳመራ ላይ ስለሰደቡዎት ይሰማዎታል?” አይነት መልስ መለሰላቸው። ዶ/ር መረራም ዶ/ር ብርሀኑም ተቃወሟቸው። የሰው ሞት ያልተሰማቸው፡ የራሳቸው መሰደብ ተሰማቸው። ባለካባው፡ ባለወንበሩ፡ ባለአዞው ቆዳ፡ አባ ጳውሎስ።
ያንዳንድ ሰው ቆዳ፡ ለቆሙለት ዓላመ የአዞ ነው። ድንዝዝ። ውሀም እንባም ሰርስሮ አይገባውም። ለስጋቸው ግን ይሳሳል። በተለይ የሀይማኖት ሰዎች? ዶ/ር ብርሀኑ ለሰው ልጅ ነጻነትና ድህነት ሞተ በሚለው ክርስቶስ ተጋድሎ የሚኮራውን ያህል፡ ክርስቶስን ወይም ሌላ ሰማእትን ወይም ነቢይን ወይም አምላክ የሞተለትን ዓላማ ወክለው ቆመው፡ ነገር ግን ከቆሙለት ነገር በተቃራኒ የሚሰሩ ሀሰተኞች የሀይማኖት መሪዎችን ሲያስብ እጅግ በጣም ይቆጣል። ቁጣው ፊቱ ላይ ሲንቀለቀልና ለነዚህ አይነት ሰዎች ያለው ንቀት ቦግ ሲል ይታያል። አሁን “ማናቸው እኚያ፡ ከምርጫው በኋላ ሕወሀት ያቋቋመው መርማሪዎች ኮሚሽን ውስጥ፡ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ወክለው የተቀመጡት ሰው፡ መጀመሪያ ኮሚሽኑ ብቻውን ቁጭ ብሎ አገዛዙ አመጹን ለማፈን ከመጠን ያለፈና አላስፈላጊ ሀይል ተጠቅሟል ወይ ብለው ድምጽ ሲሰጡ፡ አዎ ብለው ሲያበቁ፡ ኋላ ላይ ፓርላማ ቀርበው፡ “የለም መንግስት አግባብ ያለው ሀይል ነው የተጠቀመው፡ አስፈላጊ እርምጃ ነው የተወሰደው” ብለው የተናገሩት? አሁን እነዚህ የሀይማኖት ሰዎች ናቸወ?” አይደሉም፡ አሳፋሪዎች እነጂ፡ ጉዶች ናቸው”። ብሬ ተቆጣ። ወደቁጣውና ትዝታው እመለሳለሁ። በዚህ ጽሁፍ የብሬን ትዝታ እናጠነጥናለን። የብሬንም ትንቢት እንሰማለን። ከዚያ በፊት ግን፡ መግቢያ።
እንደመግቢያ፡ እንደ መነሻ፡ ታሪክ ሲጠነጠን
መስቀልንና ዳመራን እንዳወጣሁ፡ ለቀጣዮቹ ሁለት ወራት ብእር ላላነሳ ምዬ ነበር። መሀላዬ ፈረሰ። ደግነቱ አልተገዘትኩም። መሀላም ግዝትም ቢፈርስ አይበጅም ነበር። የኢትዮጵያ ነገር መሀላዬን አስፈረሰኝ። ለነገሩ ያለለት ሰው ጠብ-መንጃ ያነሳል፡ እኔ ብእር ላለማንሳት ማልኩ። ግን መሀላዬን ጣስኩት። ኢትዮጵያ መስቀልን አውጥታ መቸገርና መቃጠል አታቆምማ። ኢትዮጵያ ተክሌ ፈተናና ትምህርት እስኪጨርስ ችግሯ ጋብ አይልማ። ንግዳችን እስኪያተርፈን፡ ልጆቻችን እስኪያድጉ፡ ሞርጌጃችን ተከፍሎ እስኪያበቃ የኢትዮጵያ ችግር አያበቃም እንደማለት ነው። ሌላስ፡ ለምን መሀላዬን ሰብሬ ብእር አነሳሁ? ጊዜ የማይሰጥ፡ ቋንጣ የማይሆን ርእስ ገጠመኝና። በዚህ ቋንጣ በማይሆን፡ በግንቦት ሰባት የዳላስ ስብሰባ ለመሳተፍ ተጉዤ፡ በዳላስ ቆይታዬ ከብሬ ጋር (ዶ/ር ብርሀኑ) ባደረግኩትና.ባደረግነው ጨዋታ ላይ መቆየት አሰኘኝ። ስብሰባችንን በድል አጠናቀን፡ እነሆ አንድ አስር የምንሆን ወንዶች ሰዎች፡ ዝርዝር ለመነጋገር ተቀመጥን። ጥያቄዎች ከያቅጣጫው መሰንዘር ጀመሩ። ስለ ምርጫ መጣ።
“በነገራችን ላይ መጽሀፍህም ላይ ገልጸኸዋል የጠበቀ ወዳጅነት እንደነበራችሁ። ግን ከበረከት ጋር የት ነው የምትተዋወቁት? እንደው ሃሰባቸውን ጥለው ምርጫውን ለቀቅ እንዲያደርጉስ የሰራችሁት የማሳመንና የማግባባት ስራ ነበር?” እንዴት ተሸወዱ?” ሀሳቡን ለመስጠት ሲጀመር፡ እኛ ከመቸኮላችን የተነሳ፡ አንዳችን ጫካ ነው የሚተዋወቁት፡ ሌላችን ደግሞ የለም በታምራት ነው፡ የለም በእንቶኔ በኩል ነው። የሰውን ልጅ ማን ይሉታል ሲል፡ አንዳቸው ኤልያስ፡ አንዳቸው ነቢዩ እንቶኔ ሌላኛው ደግሞ እንትና እንዳሉት አይነት ነገር መሆኑ ነው። ብሬ ሁላችንም እስክንጨርስ ጠበቀ።
ያኔ ደርግ ሊወድቅ አካባቢ አባቱ አይናቸውን ሊታከሙ ዲሲ አካባቢ መጥተው ነበር። ብሬ ለብዙ አመታት ከአገሩ ተለይቶ ቆይቶ ስለነበር፡ ባንድ በኩል የሚመጣው አይታወቅምና ይህቺን አገር መጎብኘት አሁን ነው ብለው አባት ምክር ስለሰሰጡ፤ አቶ ነጋ፤ በሌላ በኩል ደግሞ አባቱም ብቻቸውን ከሚመለሱ አንድ ሰው አብሯቸቸው ቢመለስ መልካም ነው ብሎ ቤተሰብ ስለመከረ፤ ብሬ አባቱን አጅቦ ቦሌ ደረሰ። ቦሌ ላይ አንድ ሁለት ሰዓት ታገተ። ያኔ ገቢ ወጪው ቦሌ ላይ ይታገት ነበር መሰል። እኔ ያስራ ሶሰት አስራ አራት አመት ታዳጊ ነኝ ያኔ፡ እና እንኩዋን ቦሌን ቦላሌም አላውቅ። በኋላ ላይ ብርሀነ ገብረክርስቶስ መጣ። (ብርሀነ ኋላ ላይ አምባሳደር አድርገው ለጥቂት ዓመታት ዲሲ አስቀምጠውት ነበር። የመለስ የቅርብ ሰውና የፖለቲካ ጋሻ ጃረግሬ ነው። ብርሀነ ማለት አንድ ቦታ ተጽፎ እንዳየሁት ከሚስቱ ሲፋታ፡ በፍቺው ሰዓት ድርጅታቸው ሕወሀት በሚሊዮን የሚቆጠር በስሙ ያስቀመጠውን የኢትዮጵያ ሀብት አካፍለኝ ብላ ጎሮሮውን የያዘችው ነው ተብሎ ተጽፎ አንብቤያለሁ)። በሙሉ እውነት ነው ውሸት? እኔ እንጃ። ግማሽ እውነት ነው በርግጠኝነት። ብዙ ውስጥ አዋቂዎች ተናግረውታል። ባለፈው አውሮፓ ብረሀነና ወዳጆቹ ስብሰባ ሲያደርጉ፡ ይሄንኑ አንስቶ ወዳጄ መስፍን አማን ሲጋፈጠው፡ ብርሀነ እሪ ብህግ አምላክ ሲል ተሰምቷለወ። ወደ ብሬ እንመለስ።
የሽግግር መንግስት፡ በረከት፡ ብርሀኔ፡ ብርሀኑ፡ ታምራት
ወደ ብሬ እንመለስ። ያኔ አዲስ አበባ የዚህ የሽግግር መንገስት ስብሰባ ምናምን የሚሉት ነገር ነበር። እና ብርሀነ ብርሀኑን ታዛቢ ሁን አለው። የምን ታዛቢ? ያኔ እነ ብርሀኑ ነጋ HORN OF AFRICA የሚባል ድርጅት ነበራቸው፡ እና ያንን ወክለህ አለው። እኔ “ሆርን ኦፍ አፍሪካን” ለመወከል ውክልና የለኝም። ለማንኛውም አሁን ቤቴ ልድረስና ኋላ ላይ እንነጋገር አላቸው። ቤት ሄደ። ወደ ማታ ላይ መጡና ሂልተን ሆቴል አስገቧቸው። ስብሰባው አለቀ። ብርሀኔ ንግግር አድርግ ስብሰባውን አስመልክተህ ብሎ ጠየቀው። ዶ/ር ብርሀኑን። “ጥሩ፡ መጀመሪያ ግን አቋሜን እወቁና” አለው። ስለዴሞክራሲ ያወራችሁት በሙሉ ላይ ምንም ችግር የለብኝም። “የኤርትራ ጉዳይ ግን የኢትዮጵያ ህዝብንም ይመለከተዋል ብዬ ነው የምናገረው ከተናገርኩ” አለው። አይሆንም አለና ብርሀነ ገ/ክርስቶስ ሌላ ሰው አቀረበ። በነጋታው በረከት ደወለና ከመለስ ጋር ክረክር ተቀመጡ አለ። ስብሰባ ተደረገና ከውጭ እንድሪያስ እሸቴ፡ ካገር ቤት ደግሞ መስፍን ወልደማሪያምና መኮንን ቢሻው ቀረቡ። ዋናው ነገር፡ በረከትን ያወቀው በዚያ አጋጣሚ ነው። ከዚያ በፊት ምንም ግንኙነት አለንበራቸውም።
ስለታምራትም ተጠየቀ። ታምራት ላይኔ የልጅነት ጓደኛው ነው። ነበር። አራት ዓመት አንድ ወንበር ላይ ተቀምጠው ነው የተማሩት። ማትሪክ አብረው ወሰዱ፡ በ1969፡ እኔ ስወለድ መሆኑ ነው፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገቡ። ታምራት ጎበዝ ተማሪ ነበር። ስለዚህ ጎበዝ ሰባኪ ሊወጣው ይችላል። ይሄንን እኔ ነኝ የጨመርኩት። መቼም የኢትዮጵያ ህዝብ ለጠላቶቹም የሚያዝን ምስኪን ህዝብ ሆኖ እንጂ፡ እንደታምራት ያሉ ሰዎች እንኩዋን ለሌላውም መቀጣጫ እንዲሆኑ፡ ስልጣን ላይ እያሉ ለሰሩትና ለፈጸሙት ወንጀል ሃላፊነት መውሰድና እዳቸውን መክፈል አለባቸው። ይሄ ባለፈው ሰሞን የካናዳ ፍርድ ቤት ከሩዋንዳ አምልጦ የመጣውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ተባባሪ ጥገኝነት ሊያገኝ አይገባውም ብሎ እንደወሰነበት መሆኑ ነው። እዚህ ካናዳ እንደዚያ ነው። በዘር ማጥፋትና በጦር ወንጀል የተሳተፉ ሰዎች የሰለጠነው ዓለም መጥተው ስልጣን ላይ እያሉ ካሰደዷቸው ስደተኞች እኩል ጥገኝነት ሊያገኙ አይገባም ይላል፡ የጥገንነት አገራችን ህግ። ታምራት በድፍኑ ንስሀ ስለገባና ስቅስቅ ብሎ ስላለቀሰ እንተወው የሚለው አካሄድ አይሰራም። ንስሀ ለሰማያዊ ህይወት ነው። ደግሞም በመገናኛ ብዙሀን እኮ አድበስብሶ እንዲያውም ምንም አይነት ፖለቲካዊ ስህተት አልሰራሁም ብሎ፡ ይልቅስ እንደ ተበዳይ ሆኖ ነው የዘላበደው። እዚያ አይኑ ስር፡ ስልጣን ላይ በነበረበት ግዜ፡ ስንት ንጹህ ሲቪል ኢትዮጵያዊን፡ እነ ታምራት ባመጡት ርእዮት ተገድለው፡ አሁን እዚህ መጥቶ ከኛ እኩል ስደተኛ ሊሆን ነው? የታባቱ ያሰደደንም ተሰደደ።
ወደ ብሬ እንመለስ፡ ብሬና ምርጫ 97፡ ብሬና በረከት
አሁንም ወደ ብሬ እንመለስ። ታሜ ከዚህ በኋላ በሰማይ እንጂ በምድር ብዙም አይረባንም። ብሬ አንድ ወር አካባቢ ኢትዮጵያ ቆየና ወደ አማሪካን አገር ተመለሰ። ኋላ ላይ ራሱ እንደተናገረው፡ ይሆናል ብሎ፡ ትንሽ “ጉራጌነቱም ስላላ” ኢትዮጵያ ለመኖር ቆርጦ ገብቶ ነበር። ከብሬ ፊት ስር ተኮልኩለን ጨዋታ መኮምኮማችንን ቀጠልን። በረከትን ማን ትለዋለህ? አልነው። ደግሞስ ምርጫውስ እንዴት ሰመረ? እንዴትስ ለቀቁት? ብሬ በእንግሊዘኛ ነው የገለጸው በረከትን። Bereket is a street Smart person:: ኤንድ He was confident that they would win the election። መጀመሪያ አካባቢ እኛ ስለምናሸንፍ ምርጫውን ከማጭበርበር የጸዳ እናደርገዋለን የሚል ተነሳሽነትና ሀሳብ ነበራቸው። ከዚያ በኋላ ከበረከት ጋር በየአስራ አምስት ቀኑ እንገናኝና ሻይ እንጠጣ ነበር። መጽሀፉ ላይ ውስኪ ነው የሚለው። ምንም ለውጥ የለውም። ያንን ግንኙነት ቅንጅት አውቆት ይጠቅመናል ተብሎ ነው የተደረገው። ያንንን መጽሀፉ ላይ ገልጾታል ዶ/ር ብርሀኑ። ያ ግንኙነትና በረከትም ብዙ ረድቶናል፡ ረድተውናል። ለምሳሌ ገጠር ለምርጫ ቅስቀሳ ሄድን ካድሬዎቻቸው ካድሬዎቻችንን ሲያስሩብን ወይም ሲያንገላቱብን፡ ስልኬን በረከት ጋር ጭርር ነው። ይተዉናል።
በረከት “ለኢትዮጵያ ጥሩ የምናስብ እኛ ብቻ ነን ብሎ ያስባል።” በተጨማሪም፡ “መለስ ማለት ለበረከት እግዚአብሄር ነው።” እንዲህ እንደዛሬው እስከመጨረሻው እስክንለያይና እሱም ሸሆናዬን ሊነክስ፡ እኔም እንደእባቡ አናት አናቱን ልቀጠቅጠው እስክሰናዳ ድረስ፡ ከበረከት ጋር ሁለት ግዜ ብቻ ተጣልተናል። ሁለቱንም ግዜ የተጣላነው በመለስ ምክንያት ነው። ሁለቱንም ግዜ መለስን ወረፍኩት፡ “ምን እሱ እኮ ዝም ብሎ ነው፡” አልኩት። በረከት እብድ ሆነ። የሆነ ሆነና ምንም ያኔ ከቅንጅት ታላቅ ሰልፍ በፊት፡ መለስ እንዳለውም “ምንም ሳናጭበረብር ምርጫውን እናሸንፋለን” ብለው ስላሰቡ ነው ትንሽ ለቀቅ ያደረጉልን። እኔም ከበረከት ጋር ስንገናኝ ብዙ ጊዜ “ታሸንፋላችሁ” እያልኩ እነግረው አረጋጋው ነበር። “ያው እኛም ትንሽ እናገኛለን። በላንድ ስላይድ ግን አታሸንፉንም።” አይነት ነገር ይለው ነበር። በየትኛውም ዴሞክራሲያዊ አገር ግን 55 ወይም ስልሳ ከመቶ ላንድ ስላይድ ነውና በዚያ ልክ ካሸነፋችሁን በቂ ነው፡ ምንም አታጭበርብሩ ብዬ አረጋጋው ነበር። በተለይ እነሱ የሚተማመኑበት ግብርናው ነበር። እኔም ያንን ተከትዬ ገጠሩና ገበሬው የናንተ ነው ምናምን እያልኩ አረጋጋው ነበር። ታጋይ በረከትም ያንን ታሸንፋላችሁ የሚለውን አምኖ ምርጫውን ፍትሀዊ ለማደረግ ቀን ተሌት ይተጋ ነበር። በመጨረሻ ግን ደነገጡ። ያልታሰበው ሆነ።
የ1500 ብር ሰልፍ፡ ሚያዚያ ሰላሳና የበረከት መሸወድ፡
እና የበረከት አሁን መክፋት ከዚያ የመነጨ ነው? አዎ፡ በሌሎቹ ይወቀስ፡ ራሱንም ይወቅስ ነበር። ይሄ ሁሉ የደረሰው በሱ ምክንያት እንደሆነ በማመን ያንን ለማካካስ ነው ከምርጫው ወዲህ የነበረው የአጭበርባሪነትና የሀይል አካሄድ ሁሉ ያተኮረው። እና አሁን ለተቃዋሚዎች ያንን አይነት እድል አይሰጧቸውም ነው የምትለን? በምንም መልኩ። አይታሰብም ነው የሚለው ብሬ። ያኔ እኮ እናሸንፋለን ብለው ከማሰባቸው የተነሳ፡ የማያፍሩ ጉዶች፡ ከተማ እንገነባለን ብለው ያፈናቀሉት የካዛንቺስ ህዝብ መካከል ስብሰባ ጠርተው ሄዱ። ለዚያውም አርከበን በእጩነት አቅርበው። የካዛንቺስ አካባቢ ተወዳዳሪ አንዲት ሴት ነበረች መሰለኝ። እነ ዶ/ር ብርሀኑን ስብሰባ ጠራቻቸውና ካዛንቺስ ከሷ ጋር ሊሰበሰቡ ሄዱ። ይሄማ ውርደት ነው ካዛንቺስ፡ እንደው ሞተሃላ፡ የንቀታቸው ብዛት ሌላ ሰው እንኩዋን ቢያመጡ መልካም፡ ይሄንን ያፈናቀለህን አርከበን እንዴት ያመጣሉ? በዝረራ ተሸነፈ። አርከበ።
መቼም በዚያ ታሪካዊ ምርጫ ወቅት በየስብሰባው ስለሚገኘው ሰዉ ብዛት ሲናገር ያፈዛል። መጀመሪያ ትንሽ ነበር አለ። በኋላ ግን እያደር የሰዉ ብዛት ስፍር ቁጥር አልነበረውም። ሁልግዜ አዳራሹ ጠቦ፡ ግቢዎቹ ሁሉ ይጨናነቁ ነበር። አሁን ለሚያዚያ ሰላሳው ስብሰባ/ሰልፍ እኮ፡ እንደው ለተለያዩ ወጪዎች ብለን እኛ የመደብነው 1500 ብር ብቻ ነው። ለመፈክሮች፡ ለጄኔሬተር፡ ለማይክራፎን፡ ምናምን 1500 ብር ብቻ። 3 ሚሊዮን ህዝብ በ1500 ብር ሊስተናገድ። ስብሰባውን የጠራነው ከሰዓት 2 ላይ ነበር። በቃ ገና ጠዋት 11 ሰዓት ሰዉ መስቀል አደባባይን ሞላው። እኔ ወደ ወልቂጤ መሰለኝ ለቅስቀሳ ሄጃለሁ። ጋሽ መስፍን ስልክ ደውሎ “እናንተ ሰው ጠርታችሁ ወዴት ሄዳችሁ ነው?” ብሎ ጮኸብኝ። ምን እኛ ሰው የጠራነው 2 ሰዓት ነው፤ በዚህ ሰዓት ሰው ይመጣል ብሎ ያሰበ ማን አለ? ብሬ ስለዚያ ስብሰባ ሲናገር፡ “እኛ በቃ፡ የችልነውን ያህል ጥረናል፡ እንግዲህ ዘመቻው እንደው በ”ፌስቲቭ ሙድ” ይጠናቀቅ ብለን፡ በቃ የሙዚቃ ባንድ ነገር ምናምን ተከራይተን እንዲሁ በጨዋታ ልናሳልፈው እንጂ ለዚያ አይነት መዓት አልነበረም የተዘጋጀነው” አለ። እውነቱን ነው። ብሬ አ.አ.ዩ. እያለሁም ፈተና ሲያበቃ ተማሪዎችን ሰብስቦ ሰሜን ሆቴል ወስዶ በገንዘቡ እንደዚህ የሚያደርገው ነገር አለው። አቤት ያ ቀን። ያ ጊዜ።
የፍርድ ቤት ትእዛዝ ማንበብ የማይችል ሚኒስቴር
ስለሚያዚያ ሰላሳው ስብሰባ በስሱ ጨረስን። ስለልደቱና ስዩም መስፍንም ተናግሯል ብሬ። የልደቱ ነገር ስለማይሆንልኝ የሱን አላነሳውም። ስለራሴ የምወደው ነገር ይሄ ነው። ሌሎች ጠሉት ብዬ ከመናገር ወደኋላ አልልም። የወደቀም እንጨት ላይ ምሳር አላበዛም። የልጁም የቅርብ ጊዜ አካሄድና አነጋገር አልተመቸኝም። የሆነ ሆኖ ዶ/ር ብርሀኑም ይሄ “ልደቱ በወያኔ የተተከለ ነው” የሚለውን ተራ ክስ አይቀበለውም። ባጠቃላይ “ልጁ አደገኛ ነው” ነው ያለው። ያ ደግሞ ልክ አቶ ሀይሉ ሻውል እንደሆኑት ማለት ነው። ወይ በየነ ጴጥሮስ። ብቻ የልደቱ ይቅር። የስዩም ግን ይጠቀስ። የ 2005 የመጨረሻው ክርክር ላይ ነው መሰልኝ። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያዘጋጀው መድረክ። እንግዲህ ኢህአዴጎቹ፡ ቀደም ሲል በነበሩት ክርክሮቹ ሁሉ ላይ አልተሳካላቸውም። ዛሬ ሲሉ ሳይሆን ሲቀር። የሚቀጥለውን ሲሉ፡ ሳይሳካ ሲቀር። አንድ ቀን ጁነዲን ሳዶ መጣ። ዘራፍ ታግለን ምናምን ብሎ ሊዘፍንባቸው ሞከረ። እነ ብሬ ላይ። “ኤድያ አንተ ደግሞ፡ በረከትና እኔ እንኩዋን ብንል ያምርብናል፡ ድንጋይ ወርውረናል፡ አንተ ደግሞ የት ነበርክ?” ጁነዲን መሳቂያ ሆነ። ፓርቲያቸውም እንደዚያው። በመጨረሻ፡ መለስ ይመጣል ተባለ። አ.አ.ዩ. ያዘጋጀው ስብሰባ ላይ። አስራ አምስት ደቂቃ እስኪቀረው ድረስ መለስ እንደሚመጣ ነበር የሚታወቀው። “መለስ ተናጋሪው፡ አሳማኙ፡ የቀራቸው ጥይት፡ የመጨረሻው ባሩድ።” አስራ አምስት ደቂቃ ሲቀረው፡ በቅንጅት በኩል ማነው የሚቀርበው ብሎ ጠየቀና ዶ/ር ብርሀኑና ዶ/ር ያእቆብ መሆናቸውን ሲያውቅ፡ ጎመን በጤና ብሎ ቀረና ስዩምን ላከው፡ ስዩም መስፍን። መቼም ጋሽ ስዩም እድሜ ልኩን መላላክ ነው ስራው። በ2000/1 ዓ.ም. መሰለኝ የሕወሀት ማእከላዊ ምክር ቤት ሲከፋፈሉም መቀሌ ላይ ስዩም መስፍንን አቶ ስዬ ሂድና እከሌን ጠርተህ ና ሲለው እኔ የሀምሳ ሁለት አመት ሰው ነኝ በስተርጅና አልላላክም ብሎ እንደተቆጣ ተጽፎ አንብቤያለሁ። ሪፖርተር ላይ።
ሞኝ የሞኝ ምለእክተኛ። ስዩም መስፍን ሳይሆን ስዩም ብኩን ቢሉት ይሻል ነበር፡ ኢህአዴግን ወክሎ አ.አ.ዩ. ለሚደረገው ክርክር ቀረበ። “ሕወሀት ጉልበት እንጂ ብልጠት የለውም አለ ብሬ። እኔና ያእቆብ በደንብ ተዘጋጅተናል አለ። እነሱ ቀድመው ለመምታት እንጂ ስለመዝጊያ ሀሳብ ምንም አያውቁም። እና፡ እኛን ቀድማችሁ ተናገሩ አሉ። መልካም፡ መክፈቻው ላይ ከቀደምን፡ መዝጊያውን እኛ መጨረሻ ነን አልን። ይሁን አሉ። ተናገርን። ስዩም ቀጠለና፡ “ኢንተርሀምዌ” አውጀው፡ የዘር ማጥፋት ያመጣሉ ብሎ ሊከሰን ተነሳ። ዶ/ር ያእቆበ ምላሽ ሊሰጥ ተከተለ። ሁለት ደቂቃ ብቻ አስቀርልኝ አልኩት ዶ/ር ያእቆብን። ከላይ እንደልኳችሁ እኚህ ሰዎች ጅልና የመሀይም ጥርቅም መሆናቸው እንጂ፡ የሩዋንዳው ዘር ማጥፋት ላይ አቃቤ ህግ የሆኑትን ዶ/ር ያእቆብን ከፊት አስቀምጠው ቅንጅትን፡ እሳቸውን ዶ/ር ያእቆብን በኢንተርሀምዌ ሊከሷቸው ባልተገባ ነበር። ዶ/ር ያእቆብ እንደው በጣም ተሰምቷቸው ስለኢንተርሀምዌ ምንነትና እነሱም ያንን እንዳላራመዱ ለማስረዳት መከራቸውን አዩ። ደግሞ እንዲህ ያለ ሰው እኮ ችግሩ በቀላሉ አይገባውም። ሁለት ደቂቃ ቀረ። ዶ/ር ብርሀኑ መጣ። “ያእቆብ አንተኮ ዝም ብለህ ነው፡ የፍርድ ቤት ትእዛዝ ማንበብና መረዳት ከማይችል ሰው ጋር ምን ብለህ ነው ይሄንን ያህል የምትደክመው?” ስዩም አበደ። ፊቱ ተለዋወጠ። “ደግ አረግኩ፡ እንኩዋን። እሰይ” አለ። በወቅቱ ኢትዮጵያ የነበረና ክርክሩን በቴሌቪዥን የተከታተለ ሰው አሁን ድረስ የስዩም እብደትና የፊቱ መለዋወጥ ትዝ እንደሚለው ይናገራል።
ብሬን ሳውቀው፡ ቀድሞም የወደድኩት የለውጥ መልእክተኛ
ሄግ የሚገኘው አለማቀፍ ፍ/ቤት ያኔ ባድመን ለኤርትራ ትገባለች ብሎ ቢወስንም፡ ውሳኔውን ሊሰማ የተገኘው አቶ ስዩም ግን ፍ/ቤቱ ውሳኔውን እስኩ ኢትዮጵያ እስኪመለስ እንዳይለቀው ጠይቆ የኢትዮጵያን ህዝብ ሊያጃጅል ይሁን አይታወቅብኝም ብሎ ባድመ ለኛ ተፈረደልን ብሎ በቴሌቪዥንና በሬድዮ ዘባረቀ። ነገሩና ውሳኔው ግን ተቃራኒው ነበር። ስዩም መስፍን ነበር የቀረው እሱም በክርክር ከነ ድርጅቱ ተመታ። ብቻ በዚያም ክርክር አልሆነላቸው። በግረብርናው፡ በኢኮኖሚው፡ በፖለቲካ ጉዳዮች በሁሉም ክረክር አልተሳካላቸውም። በመጨረሻ በረከት፡ እኛ እና እናንተ ብቻ፡ ኢህአዴግና ቅንጅት መሆኑ ነው፡ ያለንበት ክርክር ማድረግ አለብን ብሎ ተነሳ። “ምን ችግር አለ። ግን በቀጥታ ለህዝብ የሚተላለፍና ህዝቡ ማየት በሚችልበት ዋና ሰዓተ ላይ ከሆነ ነው አልናቸው አለ ብሬ።” እሺ ብሎ በረከት መሬው አለቆቹን ሊያናግር ሄደ። ግን አለቆቹ በጀ አላሉም። በቀጥታ አይተላለፍም። እንደለመዱት ሊቆራርጡት። ያ እንኩዋን አይሆንም። ወያኔ በጫካ ብቻ አይደለም፡ ከተማም ከገቡ ቆረጣ አልተዉም። ሰው ይቆርጣሉ። ፊልም ይቆርጣሉ። ታሪክ ይቆርጣሉ። ይኸው ቅንጅትንም ቆረጡት። የቴሌቪዥን ክርክሩም አልተደረገም። ብሬም አገሩን ኢትዮጵያን የማበልጸግ ተልእኮው ተቋርጦ ተሰደደ። ባንድ በኩል አዘንኩ። ይሄ ሰው ድጋሜ ሊሰደድ፡ የምትፈልገውን አገሩን ሊለቃት ሆነ። በሌላ በኩል ግን ከመሞት መሰንበት መልካም ነውና ዳግም ከቅንጅት መሪዎች ጋር ሲያትል ሳገኘው ደስ አለኝ። 2007 ዓ.ም. መሆኑ ነው። ጥቅምት።
ከብሬ ጋር መዋል፡ መቀመጥ ደስ ይላል። ብሬን የማውቀው የዛሬ አስርና አስራ አንድ ዓመት አካባቢ አ.አ.ዩ. የስነ-ምጣኔ ሀብት (ኢኮኖሚክስ) መምህር ሆኖ ሳለ ነው። ያኔም የሚያስቀና መምህር ነው። የህግ ፋክልቲ ከሌሎቹ አነስ ስለሚልና በቅርበት ከመምህራኑ ጋር ስለምንተዋወቅ የተሻለ ግንኙነት ቢኖረንም፡ የኢትዮጵያ መምህራን እንደምታውቋቸው ናቸው። ወግ አጥባቂዎች። አያስጠጉም። ዶ/ር ብርሀኑ ግን ከተማሪዎቹ ጋር ያለው መቀራረብ እጅግ በጣም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ፡ ብዙዎቻችን ባስተማረን እያልን እንጓጓ እንቋምጥ ነበር። ብሬ ሀሳቡን እንደልቡ የሚናገር ደፋር ሰውም ነበር። በ1993 ዓ.ም. እንደ አበሳ ወይም እንደ አበሻ አቆጣጠር፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሀምሳኛ አመቱን ሲያከብር፡ ካዘጋጃቸው የውይይት መድረኮች በአንደኛው ላይ ተማሪዎችን ወክዬ ንግግር አቅራቢ ሆኜ ተገኝቼ ነበር። ዶ/ር ብርሀኑ ስለትምህርት ነጻነትና በአ.አ.ዩ. ስላለው አፋኝ ሁኔታ ከአሜሪካው ተሞክሮ ጋር እያመሳከረ ሀሳቡን በልበ ሙሉነት ሲሰጥ ሰምቻለሁ። ምናልባት ዘመዱን ተማምኖ ነው እንል የነበርን ሰዎች ካለን፡ ያኔ ታምራት ላይኔ ታስሮ ስለነበር ብሬ ይሄ ነው የሚለው ከእስር የሚያድነው ዘመድ አልነበረውም። እንደው ሲፈጥረው ደፋርና ታጋይ ሆኖ እንጂ። ከዚያ ቀጠለና፡ በመጋቢት ሁለት ሺህ 1 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ድርጅት ጋር በመተባበር ባዘጋጀነው ስብሰባ ላይ ከፕሮፌሰር መስፍን ጋር ሆኖ ንግግር እንዲያደርጉ ጋብዘናቸው ወርቅ የሆነና በተዘዋዋሪም ቢሆን ተማሪዎችን ለመብታቸው እንዲናገሩ ና እንዲታገሉ ያነሳሳ ንግግር አድርጓል። ከዚያ በፊት ብሬ፡ ሕወሀት ከኤርትራ ጋር ያንን ትርጉም የለሽ ጦርነት ሲያደርግ፡ በየእለቱ ለጦርነቱ የሚወጣውን ገንዘብና ድህነታችንን እያስተያየ የጻፈው የምርምር ወረቀት አይረሳኝም። ብቻ ብሬ እንዲህ እንደዛሬው በቅርበት ስላወቅኩት ብቻ ሳይሆን፡ ያኔም በሩቁ ራሱ ኢትዮጵያ በስም ሳውቀው ሰራተኛ፡ ደፋር፡ ለአገሩ ቅን አሳቢ፡ አንባቢና ተመራማሪ ሆኖ ነው።
እንደ ማሳረጊያ፡ እንደ አደራ፡ እንደ ብርቱካን ደግሞ እንደ ብሬም
ይሄ ለሚመለከታችሁ ብቻ ነው። ቅስቀሳ ነው። የማይመለከታችሁ ከዚህ መለስ ያለውን ተዉት። ይሄ የስደት ትግል ብዙም አይዋጥልኝም ነበር። ፈታኝ ነዋ። ብሬና ጓደኞቹ ግን፡ ያልተገናኘውን አገናኝተው የተገናኘውንም አስተባብረው፡ የበኩላቸውን ሊሰሩ ደፋ ቀና ይላሉ። ፖለቲካችን ካሰብንበት የሚያደርስ እንጂ ወስዶ ገደል የማይከሰክስ ፓይለት ካስፈለገው ከብሬ የተሻለ ሰው አይታኝም። ብርሀኑን ሳይ ብርቱካንን አያለሁ። ሁላችንም ግንቦት ሰባት ነን ነው ያልኩት በቀደም። ራሴን መጥቀስ እወዳለሁ። ሰው ቀድሞ ራሱን ካልጠቀሰ ሌላውንማ የት አውቆት ይጠቅሳል። ግንቦት ሰባት ሀሳብ ነው። ግንቦት ሰባት እምነት ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ተናግሯል። መርጧል። ስለዚህ ምርጫው ይከበር ነው። መሳሪያ ያዘ ወረቀት፡ ያ ለውጥ አያመጣም። ሁላችንም የምናነሳው የቆምንበት መሬት የፈቀደልንን መሳሪያና ስልት ነው። እኔ የብርቱካንን ስልት አልመርጥም። ብርቱካንስ መንገዷን መረጠች። የመረጠችውን መንገድ አደንቃለሁ። አንዳንድ ሰዎች ግንቦት ሰባትን መርዳት አንድነትን እንደመክዳት፡ የዚህኛው የትግል ስልት አብቅቶለት ሌላ የትግል ፈትል መፍተል ይመስላቸዋል። እንደኔ እንደኔ አስተያየት፡ አስተያየቴ ብቻም አይደለም፡ በርግጥም የምጓዘው ሁሉም መንገዶች ያስፈልጉናል ብዬ ነው። እነዚህ ሰዎች የኢትዮጵያውያን እስራት ምሳሌ የሆነችውን ብርቱካንን በእስራት ጽልመት ከተው ሲኖሩ፡ እንደ ግንቦት ሰባት ያለ ድርጅት መጣሁ እያለ በላያቸው የሚያፏጭ ማስፈራሪያ ብቻ አይደለም ማንበርከኪያ ተገን ያስፈልገናል። ግንቦት ሰባት ያንን ክፍተት ይሞላል። ለዚህም ነው፡ ግንቦት ሰባት ግን እኛን ነው፡ እኛም ግንቦት ሰባትን ያልኩት።
ከግንቦት ሰባት ጋር መሰለፍ የግድ አገር ቤት ያሉ ድርጅቶች የሚከተሉት ስልት አብቅቶለታል ማለት አይደለም። ለዚህም ነው ነገ፡ እነስዬና እነ መድረክ “ምርጫ” ገባን ብለው ቢነሱ በርቱ ግፉበት ብየየ የምጽፈው። ከላይ እንዳልኩት፡ እኛ ትግላችንንና ስልታችንን መምረጥ በምንችልበት ቀዬ ነን። እነሱም ምርጫ በሌለበት ደብር ያለውን ብቻ መርጠው መጓዛቸውን በምንም መልኩ መተቸት አንችልም። ዋንኛውን ጠላት ወያኔን መቃወሙን ወደ ሰልመና ጠብመንጃ በሚመርጡ ሀይሎች መካከከል እንደሚደረግ ፍክክር ቆልምመን አንጓዝም። ይሄንንም ያንንም ማስኬድ እንችላለን። እንግዲህ፡ ይሄ የሆነውን ነው የሚመለከተው፡ ያልሆነውን አይመለከትም። ብሬ፡ የግንቦት ሰባት ስብስብም ሰው የሰው ስብስብ ነውና እንደ ሰው እኛ ሌሎቻችን ላይ ያለ ድክመትና ህጸጽ ሁሉ ሊገኝበት ይችላል። በተለይ ለምንቀመጥ ሰዎች በቀላሉ ሊታይ የሚችል ብዙ ህጸጽ አያጣውም።
በመሰረቱ ድክመትን እየነቀስን ለመጓዝ የተዘጋጀን አናሶች ሳይሆን፡ ድክመትን እየቀነስን የምንጓዝ ታላላቆች ነው መሆን ያለብን።የሌሎች ድክመት እኛ መስራት ያለብንን እንዳንሰራ አያደርጉንም። ትግል “ሪስክ ቴኪንግ” ነው ይለናል ዶ/ር ብርሀኑ። እኔም ዳላስ ላይ ባቀረብኩት ወረቀት ላይ ያልኩት ይሄንኑ ነው። ትግል ሙከራ ነው። ሰዎቹ ሞከሩ፡ ተሳካላቸው። ሕወሀት። ሕይወት ራሱ ሙከራ ነው። ፓርኪንግ ያላዋጣው ሰው፡ በቃ አልሆነልኝም ብሎ ራሱን ፓርክ አያደርግም ወይም አይሞትም። ደግሞ ታክሲ ስራ ይሞክራል። ንግድ ያልሆነለት እንደዚያው። ትዳር ሙከራ ነው። ስለዚህ ሙከራቸው ያልተሳካ ይፋታሉ። ኢዴፓ ያላዋጣው በመኢአድ ይሞክረው። ስለዚህ ግንቦት ሰባትንም እንሞክረው። ከሆነ ሆነ። ዶ/ር ብርሀኑ በርግጠኝነት ደግሞ ደጋግሞ ይሆናል ነው የሚለን። እንደ ብርሀኑ ነጋ ያሉ ሰዎች የሚያግዛቸውና የሚደግፋቸው ሰው አጥተው ተስፋ ቆርጠው ከትግሉ አውድማ ቢወጡና ፖለቲካውን ባፍጢሙ ቢደፉት ግን፡ ሌላ ብርሀኑ ማግኘት ቀላል አይደለም። ደግሞ ብርሀኑ፡ ጎንደርም ሸዋም ለሱ እኩል ነው። አያሰጋም። ይሄ ለሚመለከታችሁ ነው። የማይመለከታችሁ አይመለከታችሁም።
እውነትም መንገድም ግንቦት ሰባት ብቻ አይደለም። ይሄንን ግንቦት ሰባትም አላለም። እናንተም የራሳችሁን ግምገማና ድምዳሜ ማድረግ መቻላችሁ እንደተጠበቀ ሆኖ፡ በዚህ ኢትዮጵያ በሐወሀት አፍራሽ ርእዮትና አጥፊ አገዛዝ በምትናጥበት ወቅት፡ ቤትና ንብረታቸውን፡ ትዳርና ልጆቻቸውን ንግድና ስራቸውን በድለውና ሰውተው ለኢትዮጵያ የሚበጀውን ለመስራት፡ ላጽልመትን ወደ ብርሀን ለመለወጥ ሌት ተቀን ከሚለፉት፡ በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች ውስጥ ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ አንዱና ዋንኛው ነው። ስለዚህም፡ ሰልፋችንን ከሱና ከድርጅቱ ጋር ማሳመር የምንችል እሰየው፡ ባንችልም ግን ይሄ ጥሪ በተለይ ለሚመለከታቸው ቢሆንም፡ የማይመለከታችሁም በመረጣችሁት ሌላ መንገድ የምትሰሩትን ስሩ። እንስራ። ይሄው ነው። ግንቦት ሰባት ላይ የህሊናም የገንዘብም የቁስም መዋእለ ንዋያችንን ብናፈስ አንከስርም። ቅስቀሳዬን ጨረስኩ። ለዛሬ ማለቴ ነው። እነሆ ሕይወት ግን ይቀጥላል። ዛሬ መድረክ ይሰበሰባል።
መድረክ ከውስጥ ይሰራል። እኛም ካለንበት የምንችለውን እናደርጋለን። ኢትዮጵያ አንድ ብሄር፡ አንድ ቋንቋ ፡ አንድ ድርጅት፡ አንድ አዳኝ፡ አንድ ሀይማኖት፡ አንድ ታሪክ ብቻ ሳይሆን፡ የብዙ አዳኞች ቅይጥ የሚያድናት አገር ናት። ወይም መሆን አለባት። እነሆ በዚህ ላለነው፡ ግንቦት ሰባት አለ።
አርብ መስከረም 29 ቀን፡ 2009 ዓ.ም. ቫንኩቨር፡ ካናዳ ለመመየል፡ በThis email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ላይ አግኙኝ።



