አማኑኤል ዘሠላም This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

ከሦስት ዓመት በፊት ወደነበረው የሀገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ለትውስታ ያህል ልመልሳችሁ። ተቀማጭነታቸው አሜሪካን ሀገር የሆኑ፣ የቀድሞ የሰሜን አሜሪካ የቅንጅት ድጋፍ ማኅበር ጥቂት አመራር አባላት፣ በሆላንድ ሀገር ከኦሮሞ ነፃ አውጭ ግንባር፣ ከኦጋዴን ነፃ አውጭ ግንባር፣ ከኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር እና ከሲዳማ ህዝብ ነፃ አውጭ ግንባር ጋር ትብብር ለነፃነትና ለዲሞክራሲ (ኤ.ኤፍ.ዲ.) የሚባል አካል መሰረቱ። ይህ አካል በተለይም በውጭ ሀገር ትልቅ መከፋፈልን ፈጥሮ እንደነበረ ይታወሳል።

 

ኢትዮጵያ ሪቪው ይፋ ባደረገው በዚህን አካል መግባቢያ ሰነድና መተዳደሪያ ደንብ መሰረት፣ ይህ ኤ.ኤፍ.ዲ. ኢትዮጵያዊነትን በጭራሽ ያላንጸባረቀ፣ የኢትዮጵያን አንድነት ለድርድር ያስቀመጠ አካል ነበር።

 

ቅንጅትን እወክላለሁ ብሎ ከቀረበው ከሰሜን አሜሪካ የድጋፍ ድርጅት ከመጣው የጥቂቶች ቡድን ውጭ፣ በኤ.ኤፍ.ዲ. ውስጥ የነበሩት ሌሎች አራት ድርጅቶች በሙሉ መቀመጫቸው አሥመራ የነበረ ሲሆን፣ ሁሉም በትጥቅ ትግል የሚያምኑ ድርጅቶች ነበሩ።

 

ይህንን አካል ብዙዎች “ኢትዮጵያዊነትን ያላንጸባረቀና ሻዕቢያ ከበስተኋላ የሚቆጣጠረው ነው” በሚል የተቃወሙት ሲሆን፣ ብዙዎች ደግሞ “ቢያንስ ቢያንስ በተቃራኒ ወገን ተሰልፈው የነበሩትን ኢትዮጵያውያንን በትንሹም ቢሆን ማቀራረብ ችሏል” በማለት ደግፈውት ነበር።

 

በአሁኑ ጊዜ ይህ ኤ.ኤፍ.ዲ. የሚባለው አካል የሞተ አካል ነው። አሁን የለም። ነገር ግን በአንድ ጎኑ ከኤ.ኤፍ.ዲ. ተመሳሳይ የሆነ አካል፣ ከጥቂት ቀናት በኋላ መስክረም 30 ቀን 2002፣ በአዲስ አበባ የአንድነት ጽ/ቤት ውስጥ በኦፊሴል ይመሰረታል። የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ (በአጭሩ መድረክ) ይባላል።

 

ይህ መድረክ ከኤ.ኤፍ.ዲ. ጋር የሚያመሳስለው አንድ ትልቅ ጎኑ፣ እንደ ኤ.ኤፍ.ዲ. በተለያዩ አቅጣጫዎች ተሰልፈው የነበሩትን የኢትዮጵያውያን ትልቅ ድንኳን በመሆን ያሰባሰበ በመሆኑ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቁና ጠንካራው የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ፣ በዶ/ር መራራ ጉዲና የሚመራው የኦሮሞ ህዝብ ኮንግረስ፣ በአቶ ቡልቻ ደመቅሳ የሚመራው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ በቀድሞ ከፍተኛ የህወሓት አመራር አባልና የቀድሞ የትግራይ ክልል አስተዳዳሪ አቶ ገብሩ አሥራት የሚመራው የዓረና ትግራይ እንዲሁም ሌሎች አራት ድርጅቶችን ያቀፈ ትልቅ ስብስብ ነው።

 

መድረኩ ከኤ.ኤፍ.ዲ. ጋር ያለው ተመሳሳይነት እዚህ ላይ ያበቃል። መድረኩ ከኤ.ኤፍ.ዲ. ጋር ያለው ልዩነት ግን በጣም የሰፋና የበዛ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ያሉትን ልዩነቶችም በጥቂቱ እንደሚከተለው አቀርባለሁ።

 

የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነት መድረኩ ለድርድር አያቀርብም

ኤ.ኤፍ.ዲ. በጭራሽ ኢትዮጵያዊነትን ያንፀባረቀ አልነበረም። የኤ.ኤፍ.ዲ. የመግባቢያ ሰነድ እንዲሁም ኤ.ኤፍ.ዲ. ያወጣቸው የተለያዩ መግለጫዎች በእንግሊዘኛ እንጂ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቋንቋ በሆነው አልተጻፈም።

 

በኤ.ኤፍ.ዲ. ምስረታ ላይ እንዲገኙ የተጋበዙትና የኤ.ኤፍ.ዲ. አካል አንሆንም ብለው የወጡት የሕብረት ተወካዮች፣ የኤ.ኤፍ.ዲ. ስም “ኢትዮጵያ” ወይንም “አንድነት” የሚሉት ቃላት እንዲገባበት ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ ኤ.ኤፍ.ዲ. በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የጠራ አቋም ስላልነበረው በስሙ ውስጥ “ኢትዮጵያ ወይንም “አንድነት” የሚል ሳይገባ ቀርቷል።

 

መድረክ እውቅና ለማግኘት ለምርጫ ቦርድ ባስገባው ሰነድ ግን “የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ” የሚል ስያሜ ነው የያዘው። ወደ ዝርዝር ሳንሄድ መድረኩ ወይንም በመድረኩ ውስጥ ያሉ ስምንት ድርጅቶች በኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት የማያወላውል አቋም እንዳላቸው እናያለን።

 

የአንድነት ድጋፍ ድርጅቶች እንዲወያዩበት የተላከውና በቅርቡ ይፋ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው የመድረኩ ማኒፌስቶ በግልጽ እንደሚያስቀምጠው፣ መድረኩ የሀገራችን አንድነትን በተመለከተ አቋሙ የፀና እንደሆነና ኢትዮጵያዊነትን በተመለከተ መድረኩ፣ ቅንጅት ያኔ ከነበረው አቋም በምንም ያልተናነሰ አቋም እንደያዘ ለመረዳት ችያለሁ። በመድረክ ማኒፌስቶ አንቀጽ 5 ላይ “የኢትዮጵያ ዳር ድንበር፣ ነፃነት፣ አንድነት እና ሉዓላዊነት የተጠበቀ እና የተከበረ ይሆን ዘንድ በጋራ እንቆማለን” ሲል የመድረኩ የኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት በምንም አይነት መልኩ ለድርድር እንደማይቀርብ በግልጽ አስቀምጧል።

 

ኦነግና ኢህአዲግ አርቅቀው ባፀደቁትና በህዝብ ላይ በጉልበት በጫኑት አሁን ባለው ሕገ መንግሥት ውስጥ፣ በአንቀጽ ሰላሳ ዘጠኝ፣ የብሔር ብሔረሰቦች የመገንጠል መብት እንዳላቸው ይደነግጋል። ይህ አንቀጽ ፀረ-ኢትዮጵያና ፀረ-አንድነት አንቀጽ እንደሆነና በአብዛኛው የሀገራችን ክፍል ትልቅ ተቃውሞ እንዳለው ይታወቃል።

 

መድረኩ በዚህ በመገንጠል መብት ዙሪያ አቁሙን ግልጽ አድርጓል። በማኒፌስቶ አንቀጽ አንድ ላይ “ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት በጽናት እንቆማለን። በቀድሞ የነበሩትና በአሁኑ ጊዜ ያሉትን ኢፍትሃዊና አድሎአዊ አሠራሮች የተወገዱባት በመከባበር ላይ የተመሰረተ አንድነት እንዲፈጠር በጽናት እንቆማለን። በመሆኑም መገንጠልን አንደግፍም” ሲል ዜጎች ልዩነቶቻቸውን አቻችለው የበለጠ የሚቀራረቡበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንጂ መከፋፈልና መለያየትን የሚያመጡ ማናቸውም አይነት መንገዶች መዘጋት እንዳለባቸው ነው መድረኩ ያስቀመጠው።

 

አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የባድመ ጦርነትን ተክትሎ አልጀርስ ላይ የፈረመው ስምምነት ትክክል እንዳልሆነ፣ እንደገና ከኤርትራ ጋር በሠላም መደራደር እንደሚያስፈልግ፣ ማንኛውም የድንበር ከለላ ከመደረጉ በፊት ህዝብና ፓርላማው ማወቅ እንዳለበት እንጂ ጥቂቶች በዘፈቀደ የሀገራችንን መሬት እንደ ግል ንብረታቸው መስጠት እንደማይችሉ፣ ኢትዮጵያ የባህር በር እንደሚያስፈልጋትና አሰብ የኢትዮጵያ እንድትሆን ሕጋዊና ሠላማዊ በሆነ መንገድ ትግል እንደሚያደርግ መድረኩ በማኒፌስቶ በግልጽ አስቀምጧል። ይሄ ሁሉ እንግዲህ መድረኩ ከኤ.ኤፍ.ዲ. ጋር ያለው አንድ ትልቅ ልዩነት ነው።

 

መድረኩ ኢትዮጵያን እንጂ አስመራን ያማከለ አይደለም

ኤ.ኤፍ.ዲ. ሲመሰረት ከበስተጀርባው የኤርትራ መንግሥት እንዳነበረበት ይናገሩ የነበሩ ብዙ ናቸው። የኤርትራ መንግሥት ከበስተጀርባ ባይኖርበትም እንኳን ኤ.ኤፍ.ዲ. ውስጥ ያሉ አራት ድርጅቶች ዋና ጽ/ቤቶቻቸው አስመራ እንደመሆኑ፣ ኤ.ኤፍ.ዲ. በተዘዋዋሪ በሻዕቢያ መጠምዘዙ የማይቀር እንደነበረ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። በአስመራ ላይ የተደገፈ አካል እንደመሆኑም ኤ.ኤፍ.ዲ. የኢትዮጵያን ጥቅም ሊያስጠብቅ ይችል የነበረው የኤርትራን ጥቅም ባልነካ መልኩ ብቻ ነበር።

 

ለምሳሌ በአልጀርሱ ስምምነት ላይ፣ አሰብን የኢትዮጵያ ወደብ በማድረጉ ላይ፣ የኤርትራ መንግሥት አልሻባብን እየረዳ በምሥራቁ የሀገራችን ክፍል አደጋ ለመጣል በሚያደርገው እንቅስቃሴ ላይ፣ አራቱ የኤ.ኤፍ.ዲ. ድርጅቶች የሚናገሩት አልነበራቸውም።

 

ሆላንድ ውስጥ ሳይሆን የሀገራችን ኢትዮጵያ መዲና በሆነችው በአዲስ አበባ ውስጥ በኦፊሴል የሚመሰረተው መድረክ ግን፣ መሰረቱ እዚያው አብዛኛው ህዝባችን በሚኖርበት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ከጀርባ ሆኖ ይህንን አካል የሚያንቀሳቀሰው ህዝቡ እራሱ ነው። ስለዚህም የኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅምና አጀንዳ ብቻ ነው በጠረጴዛው ላይ መድረኩ ያስቀመጠው። ይህ መድረኩ ከኤ.ኤፍ.ዲ. ጋር ያለው ሁለተኛ ሌላ ትልቁ ልዩነት ነው።

 

እዚህ ላይ ስለአስመራ ካነሳው አይቀር አንድ ሌላ ትልቅ ነጥብ እንዳነሳ ይፈቀድልኝ። ኤርትራውያን የመድረክን ፖሊሲዎች መፍራትና መስጋት እንደሌለባቸው የመድረኩ ማኒፌስቶ በአንቀጽ 11.2.2 ሲያስረዳ “ከኤርትራ ጋር እንደ አዲስ በመደራደር ሌላ እና የሁለቱንም ሀገሮች ጥቅሞች እና ስጋቶች ግምት ውስጥ ያስገባ ሁሉን አቀፍ ስምምነት ላይ ለመድረስ አስፈላጊ መሆኑን በማመን ለዚሁ እውን መሆን አጥብቆ ይሠራል” ብሎ፣ በአንቀጽ 11.3.1 ላይ ደግሞ “ኤርትራውያን ከዚህ ጋር በተያያዘ (አሰብ የኢትዮጵያ መሆን እንዳለበት) ሊኖራቸው የሚችለውን ስጋት ለመቅረፍ እና ሁለቱም ወገኖች ተጠቃሚ ሆነው የሚወጡበትን የመፍትሔ አማራጮችን ያፈላልጋል” በማለት ነበር፣ መድረኩ በምንም አይነት መልኩ ከኤርትራውያን ጋር ጦርነት ከፍቶ አሰብን ለመያዝ ሃሳብ እንደሌለውና ከኤርትራ ጋር ባሉት ጉዳዮች ዙሪያ ያሉትን ጥያቄዎች በሙሉ፣ በሠላምና በቅንነት ከኤርትራውያን ወንድሞቻችን ጋር ለመነጋገር የሚያስፈልገውን ሁሉ እንደሚያመቻች ግልጽ ያደረገው።

 

ፕሮፌሠር ተስፋጽዮን ያቀረቡት የኮንፌዴረሽን ወይንም የዶ/ር ዳንኤል ክንዴ የፌዴሬሽን አማራጭን በመዘርጋት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል፣ ኤርትራ ነፃ ሳትወጣም ሆነ ነፃ ወጥታም የነበረውን የጦርነትና የደም መፋሰስ ባህል አስቁሞ፣ በቅንነት የሁሉንም ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ፣ ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት የሚቻልባቸውን አማራጮች፣ ለምሳሌ መድረኩ ሊያስተናግዳቸውና ሊሰራባቸው የሚችላቸው አማራጮች ሊሆኑ እንደሚችሉ አስባለሁ።

 

የመድረክ ማኒፌስቶ በምስጢር የተዘጋጀ አይደለም

የመድረኩ ጉዳይ በመድረክ ያሉ አባላትና ደጋፊዎች በሰፊውና በግልጽ ከአንድ ዓመት በላይ የተወያዩበት ጉዳይ ሲሆን፣ ኤ.ኤፍ.ዲ. ግን በጥቂት ግለሰቦች በምስጢር የተቋቋመ ነበር።

 

ለምሳሌ የሰሜን አሜሪካን ቅንጅትን ወክለው በኤ.ኤፍ.ዲ. ሰነድ ላይ የፈረሙት ሁለት ይሁን ሦስት የሚሆኑ ጥቂት የቀድሞ የሰሜን አሜሪካ ቅንጅት አመራር አባላት፣ ጉዳዩን እንኳን ለሰሜን አሜሪካ ቅንጅት ጠቅላላ ጉባዔ ቀርቶ ለሰሜን አሜሪካ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴም እንኳን አላቀረቡትም ነበር።

 

የአንድነት አመራር አባላት ግን ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመድረክ ውስጥ የሚያደርጉትን ውይይት በየጊዜው ለድርጅቱ ብሔራዊ ምክር ቤት እያቀረቡ፣ በየክልሉ ከህዝቡ ጋር እየተመካከሩ ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለበት መልኩ ነው ይህን የመድረክ ማኒፌስቶ ያዘጋጁት። አባል ከሆንኩበት የአንድነት ድጋፍ ማኅበር ቻፕተር በተለያዩ ወቅቶች ሁለት ጊዜ የመድረኩ ማኒፌስቶ ቅጂ ደርሶኝ አንብቤ፣ አስተያየቶቼን አቅርቢያለሁ። (በ.ኤ.ኤፍ.ዲ. ያላገኘሁትን ዕድል)

 

ይህ የመድረክ ማኒፌስቶ ጥቂቶች ተስማምተው የሚጭኑብን ሳይሆን ከጅምሩ ሁላችንም ሃሳባችንን የሰጠንበት ጠቃሚና ወደፊት ሊያራምድ የሚችል ታሪካዊ ማኒፌስቶ ነው። ይሄ ከኤ.ኤፍ.ዲ. ጋር መድረኩ ያለው ሌላ ሦስተኛ ትልቁ ልዩነት ነው።

 

“ማኒፌስቶ ውስጥ ያሉ ነገሮች በሙሉ 100% (መቶ በመቶ) የምንስማማባቸው ናቸው ወይ?” የሚል ጥያቄ ቢቀርብ መልሴ “አይደለም” የሚል ነው። መድረኩ ስምንት በተለያዩ መስመሮች ይሄዱ የነበሩ ድርጅቶች በአንድ ላይ መጥተው የተሰባሰቡበት መሆኑንም መዘንጋት ያለብን አይመስለኝም። ስለሆነም የኛ የሆኑ አንዳንድ ነገሮችን የምንጥላቸው ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን ዋና ዋና የሚባሉና በኢትዮጵያውያን ዘንድ አንገብጋቢ የሆኑ ጉዳዮች የአብዛኛውን ኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት ባንፀባረቀ መልኩ በመድረኩ ውስጥ በግልጽ የተስተናገዱ እንደሆነ ለማወቅ ችያለሁ። በመሆኑም ያኔ ኤ.ኤፍ.ዲ.ን እንደተቃወምኩት አሁን መድረክን አልቃወምም።

 

ከዚያም አልፌ እሄዳለሁ። መድረኩ የኢትዮጵያን አንድነት የሚያረጋግጥ ስለሆነ፣ ከኤርትራውያን ወንድሞቻችን ጋር የሁለታችንን ጥያቄዎች በመለሰ መልኩ በሠላም ችግሩን ለመፍታት አማራጮች ስለሚፈልግ፣ በሠላምና በውይይት ሁሉንም ባቀፈ መልኩ ሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር እንዲኖርና ችግሮችን በጠመንጃ የመፍታት ባህል እንዲወገድ ለመጣር ስለወሰነና ማዕከሉ በውጭ ሀገር ሳይሆን በኢትዮጵያ ውስጥ በመሆኑ መድረክን አለመቃወም ብቻ ሳይሆን እደግፈዋለሁ።

 

መድረኩን በመቃወም የሚጽፉ፣ የአንድነት ፓርቲ በመድረክ ውስጥ በመንቀሳቀሱ የቅንጅት መንፈሥን እንዳጠፋ የሚከሱ ጥቂት ኃይላት እንዳሉ ከሚጽፏቸው አንዳንድ ጽሑፎች አስተውያለሁ። እነዚህ ኃይላት በብዛት በውጭ ሀገር የሚኖሩና አብዛኞቹ ደግሞ ከዚህ በፊት ቀድሞ ኤ.ኤፍ.ዲ.ን ሲደግፉ የነበሩ ናቸው። እኛ ያኔ ኤ.ኤፍ.ዲ.ን ስንቃወም “የተለያዩ አስተያየት ያላቸው ቡድኖች በአንድ ላይ መምጣታቸው የሥልጣኔ ምልክት ነው። ለሀገር ይጠቅማል።” በማለት ነበር ሊያሳምኑን ይሞክሩ የነበሩት።

 

ታዲያ አሁን የአንድነት ፓርቲ እንደ ኦነግ የአንድን ጎሣን እንወክላለን ብለው ይንቀሳቀሱ የነበሩትን በኢትዮጵጵያዊነት ጥላ ሥር ማሰለፉና የተለያዩ ድርጅቶች በአንድ ድንኳን ሥር እንዲመጡ ማድረጉ የሠለጠነ ፖለቲካ መሆኑን እንዴት ማየት አቃታቸውና አሁን አንድነት ከመድረክ ጋር መሥራቱን ይቃወማሉ? እነዚህ ኃይላት ሌላ ተልዕኮ ኖሯቸው ወይንም መድረክን የሚቃወሙበት ሌላ ድብቅ ምክንያት ከሌላ በቀር (ምናልባት ግለሰቦችን የመጥላት ችግር) ኢ.ኤፍ.ዲ.ን ያኔ እንደደገፉ መድረክን የማይደግፉበት ምንም ምክንያት የለም ባይ ነኝ።

 

የቅንጅት መንፈሥን በተመለከተ

የቅንጅት መንፈሥ የኢትዮጵጵያዊነት መንፈሥ ነው። የቅንጅት መንፈሥ ኢትዮጵያውያንን አብሮ ለአንድነታቸውና ለነፃነታቸው ማሰባሰብ ነው። ኢትዮጵያዊነትን አንፀባርቆ የወጣው መድረክ የቅንጅትን መንፈሥ የሚያጠፋ ሳይሆን የቅንጅት መንፈሥ የወለደው፣ የምርጫ ዘጠና ሰባት ውጤት ያመጣው ክስተት ነው።


አማኑኤል ዘሠላም This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

መስከረም 27 ቀን 2002 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ