ልጅ ተክሌ - ከካናዳ

ትንቢተ ሮማኒያ፤ መልእክተ ኢትዮጵያ

1989 ዓ.ም. ነው እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር። ታህሳስ፡ 1981 ዓ.ም. እንደ ኢትዮጵያ። በዚያ የሆነው በ20?? የሚሆነውና ያሳያል እነሆ በሮማኒያ የተከሰተውን ታሪካዊ ክስተት ማተት ፈቀድን። በዚያም ጊዜ እንዲህ ይሆናል። ከዚያ አስቀድሞ በሆነ ግዜም፤ ኒኮላ ቾቼስኮ አላደመጠም ነበር።

 

ነቢያት ሁሉ ሲተነብዩ የሚሰማ መሪ የሚያደምጥ አምባገነን የለም። ኤሌናና ቾቼስኮም አላደመጡም ነበርና ያ አስቀድሞው የሮማኒያ ወይንም ሌሎች ነቢያት የተነበዩት በነሱ ደረሰ። የሮማኒያ ፍርድ ለኢትዮጵያ ትንቢት ነው። ለማይሰሙት መለስና ሀዜብ እንዲሁም ተከታዮቻቸው ይሆን ዘንድ እነሆ የሮማኒያን ፍርድ።

 

የ1989 ልደት ለሮማኒያ ህዝብ እውነተኛ ልደት ነበር። የታህሳስ 21 አመጽ ለ15 አመታት እና ከዚያም በላይ አምባገነን ሆኖ የኖረውን ኒኮላ ቾቼስኮን ገልብጦ ጣለ። ኒኮላ መለስ ነበር። ኒኮላ ገዳይ ነበር። ኒኮላም አፋኝ ነበር። ኒኮላ አምባገነን ነበር። ሚስቱም ኤሌና እንደዚያው። ሀዜብ ነበረች። አታውቅም። ግን አለባበስ እውቀት የሚመስላት፣ ከታጋዮች ሻይ አፍይነት ወደ ቤተመንግስት እመቤትነት ያደገች ጥጋበኛ ነበረች። በነ እቴጌ ጣይቱና በነ ምንትዋብ ወንበር የተቀመጠች አምባገነን ሴት ነበረች። የሮማኒያ ህዝብ መረረው። ታህሳስ 1989 አመጽ ተነሳና ገለበጣቸው። አመጹን ሌላ ግዜ እንመለስበታለን። አሁን ግን የኒኮላና ሚስቱን የፍርድ ሂደት እንመለከታለን። ያ ለኛ ትንቢት ነውና።

 

ባንድ የጦር ፍርድ ቤት ዝግ ችሎት ኒኮላና ጠበቆቹ እንዲሁም አቃብያነ ህግ ተቀምጠዋል። ጥቂት ተመልካቾችም ነበሩ መሰል። ችሎቱ ዝግ ይሁን እንጂ የተወሰነው የችሎቱ ሂደት በቀጥታ በቲቪ ይተላለፋል (http://www.ceausescu.org/ceausescu_texts/revolution/trial-eng.htm) ።

 

አቃቤ ሕግ፡ “መልስ እንጂ? መልስልን?”

ኒኮላ ዜናዊ ወይም መለስ ቻውቼስኮ፡ “አልናገርም። እኔ የማውቀው የተወካዮችን ምክርቤት ብቻ ነው። ለተዋካዮች ም/ቤት ወይንም ለጠቅላይ ፍ/ቤት እንጂ ለሌላ ለማንም ቃሌን አልሰጥም። ከተወካዮችና ከፌዴሬሽን ም/ቤት ፊት ብቻ ነው ልቀርብ የምችለው። ማንም በኔ ላይ ስልጣን የለውም? አልናገርም።” አለ።

 

አቃቤ ህግ፡ “ትናነት ከህዝቡ ጋራ አልነጋገርም ብሎ እምቢኝ እንዳለው ዛሬም ከኛ ጋር ልነጋገርም ብሎ ማመጹ ነው።” (ይቅርታ፡ በሮማኒያንኛ አንቱታ የለም መሰል። በኢትዮጵያንኛ ግን አንቱታ አለ። እኛ እንደመለስ አይደለንም። ማለቴ መለስን ጥለን የምናቋቁመው ፍ/ቤት የነመለስ አይነት ዘርጣጭና ባለጌ አይደለም። አንቱታ የሚያውቅ ነው። አንተና አንቺ ብቻ ያለበት የታጋዮች ፍ/ቤት አይደለም)

 

አቃቤ ሕግ ቀጠለ፤ “ስለዚህ አቶ መለስ ትናንት ህዝቡን እምቢ እንዳሉት ዛሬም እኛን እምቢ አልናግርም ማለታቸው ነው። ራሳቸውን የህዝቡ አንደበት አድርገውና ለህዝቡ እንደሚናገሩለት የተወደዱ የህዝብ ልጅ እንደሆኑም አድርገው ነበር የሚያክቱት። ግን ህዝቡን ሁሌም እንደጨቆኑ ነበር። በዓል በመጣ ቁጥር በቤተ መንግስትዎ ቅልጥ ያለ ድግስ ይደግሱ ነበር። ዝርዝሩን አገር ያውቀዋል። የተከበረው ፍ/ቤት እነዚህ ሁለት ሰዎች በህዝብ ገንዘብ፣ ከውጭ አገር የማያመጡት ውድ ልብስና ምግብ አልነበረም። በዚህ ረገድ ከቀድሞው የሮማኒያና የኢትዮጵያ ነገስታት የባሱ ነበሩ። ባንድ በኩል ህዝቡ በቀን ከሁለት መቶ ግራም ያልበለጠ ሬሽን ነበር የሚሰጠው። እነዚህ ሁለት ሰዎች ግን ኒኮላና ኤሌና፤ መለስና ሀዜብ እንደማለት ነው፡ ህዝቡን ዘረፉት። ቀሙት። ያ ሁሉም ሆኖ ዛሬ ተናገሩ ሲባል መልስ አይሰጡም። ቦቅቧቆች ናቸው። ስለያንዳንዱ ወንጀላቸው ማስረጃ አለን። ቀጥሎ ጠቅላይ አቃቤ ህጉ የክሱን መዝገብ እንዲያነብልን እጋብዛለሁ።”

 

ጠቅላይ አቃቤ ህግ፡ “የተከበሩ ሰብሳቢ ዳኛ ዛሬ በነዚህ የሚከተሉትን ወንጀሎች በፈጸሙት ሁለት ወንጀለኞች ላይ (ይቅርታ ሁለት ተጠርጣሪዎች ላይ፤ እኛ ወንጀለኞች አንልም። ፍርድ ቤቱ ወንጀለኛ ይበላቸው። እኛ በነሱ ቋንቋ አንናገርም። እነሱ ናቸው ሰውን አስቀድመው ወንጀለኛ የሚያደርጉት። ከሰው፣ ፈርደው፣ ገድለው፣ ፍርድ ቤት ያቀርባሉ) ፍርድ መስጠት አለበት። ከሰው ልጅ ክብርና ማህበረሰባዊ አስተሳሰብ ጋር የማይጣጣም ወንጀል ፈጽመዋል። እንመራዋለን የሚሉትን ህዝብ አጥፍተዋል። ወንጀል ፈጽመውበታል። ጨቁነውታል። ገድለውታል። አስረውታል። በድለውታል። አገር ከፋፍለዋል። ሉአላዊነታችንን ሸርሽረዋል። ኢትዮጵያን ክደዋል። በዚህ በህዝብና በአገር ላይ በፈጸሙት ወንጀል ምክንያት፡ በተበዳዮቹና በአገሪቱ ስም እነዚህ ሁለት ሰዎች በሞት እንዲቀጡልን እንጠይቃለን። (ኖ ኖ እኛ ቀድመን አንቀጣም። መጀመሪያ ጥፋተኞች መባል አለባቸው። ካመኑ መልካም ካላመኑም እናስመሰክርባቸዋልን። መረጃ ይቀርባል።

 

እኛ መለስን ጥለን መለስ ላይ እንዲፈርድ የምንመኘው ፍርድቤት እንደ መለስ ያለ ፍርድ ቤት አይደለም)። የክስ መዝገባችን የሚከተሉትን ወንጀሎች ይዟል። አንደኛ በአንቀጽ ? ? ? መሰረት የዘር ማጥፋት ወንጀል። አምቦ ይናገር። አኝዋክ ይመስክር። አዋሳ፤ ጌዴዎ፣ አማራው፣ ኦሮሞው፣ ሶማሊው ይናገር። ሁለተኛ በአንቀጽ ? ? ? መሰረት፤ በአገሪቱና በህዝቡ ላይ የጦር ወንጀል በመፈጸም። አመጽ እናስቆማለን ብለው ህዝቡን ተኮሱበት። ገደሉት። (አይገርምም? በሮማኒያና በኢትዮጵያ የሆነውና የሚሆነው አንድ ነው)። ሶስተኛ በአንቀጽ፡ ? ? ? መሰረት የህዝብን ተቋማትና ህንጻዎች በማውደም፤ የአገሪቱን ብሄራዊ ምጣኔ ሀብት በማጥፋት፣ የኢኮኖሚውን ሂደት በራሳቸውና በቤተሰቦቻቸው እንዲሁም በታማኞቻቸው እንቅስቃሴ በማኮላሸት ወንጆለች ተከሰዋል። (አይገርምም ዝቅ ብለን እናየዋለን ግን ሀዜብና ኤሌና፤ መለስና ቾቼስኮ ያደረጉት አንድ ነው። ባዶ ኪሳቸውን አዲስ አበባ የገቡ ምስኪኖች፤ እነሆ ባስር ዐመት ታላላቅ ህብታሞች ሆኑ። ያም ባልከፋ፡ ስንቱን በሰበብ አስባቡ ከስራና ቢዝነስ ውጪ አደረጉት። እነ ኤፈርትን አስቡ። ሀዜብ። ኤሌና።)

 

አቃቤ ህግ ተመለሰ “ክሱንሰማችሁ? ተረዳችሁትስ? (የእኛ ፍ/ቤት እንደናንተ ፍ/ቤት አይደለም። ባልተረዳችሁትና ባልገባችሁ ክስ አይፈርድም። ባይገባችሁም፡ እንዲገባችሁ ለማድረግ ጥረት ያደርጋል። ያንን ነው የመሪያችን የብርቱካን መንፈስ እንድናደርግ የሚያዘን። እነሆ በ20??፡ እነ መለስ ለፍርድ ሲቀርቡ ብርቱካን በሕይወት ላትኖር ትችላለች። ይገድሏታል። ያ እንዲሆን የምንመኘው አይደለም። እነዚህ ሰዎች ግን እንደ ብርቱካን ያለ ጀግና አይናቸው ስር እንዲያድግና በአመታት እስር ገኖ፣ ከብሮ እንዲወጣ አይሹም። ስለዚህም ያጠፏታል)። ወደ ፍርድ ቤቱ እንመለስ።

 

መለስ ቻውቼስኮ፡ “መለስ አልሰጥም። አልናገርም። መናገር የምፈልገው ከአብዩ ብሄራዊ ሸንጎ ፊት ብቻ ነው። ይሄንን ፍ/ቤት አላውቅም። ክሱ ሀሰት ነው። ስለዚህም አንድም መልስ አልሰጥም። (አይገርምም ለዚህ ፍ/ቤት እውቅና አልሰጥም። እናንተ መቼ ነው የህዝብ እውቅና ያገኛችሁት? ያለእውቅና አይደለም እንዴ ይሄንን ያህል ዓመታት የገዛችሁን? አረ ይሄ አያስኬድም። ስልት ለውጡ።)”

 

አቃቤ ሕግ “የተከበሩ አቶ መለስ ቻውቼስኮ፤ በክስ መዝገብ የሰፈሩትን ክሶች አልቀበልም ብለዋል።”

 

ቻውቼስኮ ቀጠለ። ምንም አይነት ሰነድ አልፈርምም።

 

አቃቤ ሕግ ብትፈርሙስ ባትፈርሙስ ምን ለውጥ አለው። “ይሄ አገር ያወቀው ጸሀይ የሞቀው ነው። አገሪቱ የገባችበት መቀመቅ ዓለም ያውቀዋል። (ፈረምክም አልፈረምክም ለውጥ የለውም። ይቅርታ አንተ አልኩኝ። እርሰዎ። ክቡርነትዎ።) መራባችንን አገር ያውቀዋል። በያመቱ አስር ሚሊዮን ሕዝብ የምግብ ርዳታ ካልተሰጠው እንደማይኖር ሕጻናትና ሴቶች በምግብ እጦት እንደሚያልቁብን ማን የማያውቅ አለ። እስከ ታህሳስ 22 ጠንክሮ ይሰራ የነበረ የሮማኒያ ዜጋ ሁሉ መድሀኒትና ምግብ እንዳልነበረን ኤሌክትሪክና ሙቀት እንዳልነበረንና በዚህም ብዙ ሺህ ህጻናትን እንደጨረሳችሁ የታወቀ ነው። ሰቆቃችንን እኛ ብቻ አይደለንም ዓለምም ያውቀዋል።”

 

(ይሄ ሁሉ በቲቪ ይተላለፋል። ኒኮላና ኤሌና፤ ሀዜብና መለስ መሆናቸው ነው፤ ይንሾካሾካሉ የለም ይሄንን ክስ አንቀበልም ይላሉ። ኖ ኖ ጭራሹኑ አንመልስም ነው እንጂ። ሌላም ጥያቄ ቀረበላቸው? የቲምሶራን ደም መፋፈስ ያዘዘው ማነው? የናዝሬትን ግድያ ትእዛዝ ያስተላለፈው ማነው እንደማለት ነው። ወይንም የአምቦን። ወይም የአዋሳን። የድሬዳዋን። የባህርዳርን። የመቀሌን ለጊዜው ማስረጃ የለንም። ምናልባት ግን እዚያም “ሳይለንት” ግድያ ይኖር ይሆናል።) ሁሉንም ካዱ እነ ቻውቼስኮ። እነ ዜናዊ።

 

አቃቤ ህግ መጣ ለምሳሌ ማነው የቡካሬስቱን ግድያ ያዘዘው? (ቡካሬስት የሮማኒያ አዲስ አበባ መሆኗ ነው። አመጹ ሲቀሰቀስ ብዙ ሺዎች ወይም መቶዎች ወይም አስሮች ተገድለዋል። ቁጥር ምን ለውጥ ያመጣል። 193? 1093? አንድስ ነፍስ ቢሆን?)። እና ማነው ያዘዘው፡ ጦሩን በሕዝቡ ላይ እንዲተኩስ? (አግአዚን መሆኑ ነው)”

 

መለስ ቻውቼስኮ፡ አሁንም መልስ አልሰጥም አለ። ገና ወደፊትም ይላል። መልስ አልሰጥ እንዳለም፡ የጁን ያገኛል። አቃቤ ሕግ ግን ደግሞ ጠየቀው፤ እኛ እንደነሱ አይደለንምና። “ማነው ወደ ሕዝቡ እንዲተኮስ ትእዛዝ የሰጠው።” (ነገሩ እኮ ግልጽ ነው። ትዝ ይላችኋል? በምርጫ 97 ማታ መለስ ቻውቼስኮ የጦር ሰራዊቱና የፖሊስ ሰራዊቱ ባንድ እዝገብተው፡ በቀጥታ በኔ ቁጥጥር ስር ይሆናል ሲል። ከነገ ጀምሮ ምንም አይነት ሰልፍ አይደረገም ሲል። ሌላ ቀን ደግሞ ወላጆች ተጠንቀቁ፡ ልጆቻችሁን ጠብቁ፤ ልጆቻችሁ በፈንጂ ወረዳ ክልል ውስጥ ከገቡ እንገድላለን ሲል። ነገሩ ግልጽ ነው። ግን ትክክለኛ ሕግ እንደዚህ ነው የሚሰራው ሁሉም ነገር በማስረጃ በደንብ መረጋገጥ አለበት። እናም ግልጽ ቢሆንም እናስመሰክራን ማስረጃም እናቀርባለን) (ያ ብርቱካን የተሰዋችለት የምትሰዋለትም ፍትህ አካሄድ ነው)።

 

በዚህ መሀል ያቺ ሙጢ ኤሌና መጣች። ለኒኮላ ሹክ አለችው። ሀዜብ መሆኗ ነው። “ባክህ እርሳቸው ከነዚህ ጋር ማውራት እርባና የለውም”) አለች። ሚስት ብሎ ዝም። ዛሬም አያርማትም።

 

አቃቤ ሕግ ቀጠለ “ለጦር ሰራዊቱ ወደ ሕዝቡ እንዲተኩስ ስለተሰጠው ትእዛዝ የምታውቀው ነገር የለም? አሁንም ከውጭ ተኩስ ይሰማል። እነዚህ ያንተ ቅጥረኞች አሁንም ወደ ሕዝቡ እየተኮሱ ነው። ሲተኩሱ አይመርጡም። ሕጻናት፣ ሴቶች፣ ወደመኖሪያ ቤቶች፤ ዝም ብሎ ማንደቅደቅ። ማናቸው ለመሆኑ? የህዝብ ናቸው ወይንስ አንተ ቅጥረኞች።”

 

መለስ ቀጠለ “አልመልስም። ምንም አይነት ጥያቄ አልመልስም። አንድም ጥይት ከቤተ መንግስት አደባባይ አልተተኮሰም። ማንምም በጥይት አልተመታም። (እኔ አላውቅም አይነት ነገር ነው። አልመልስም ይላል። ግን ይመልሳል።)”

 

አቃቤ ሕግ “እስካሁን 34 ሰው ሞቷል። (ያ ግን ሮማኒያ ነው። ያ ኢትዮጵያ አይደለም።) የኤሌና መልስ ግን ያናድዳል። ግን ብልጥነቷንም ያሳያል እንዲህ አለች ለቻውቼስኮ። ሀዜብ ለመለስ መሆኑ ነው። አቃቤ ሕግ “እስካሁን 34 ሰው ሞቷል” ሲል ኤሌና በሹክሹክታ “ተመልከት፡ ያንን የዘር ማጥፋት ወንጀል ይሉታል።” (አይገርምም፡ እስካሁን መልስ ሳትሰጥ አሁን ክፍተት አገኘች። እሷ ያስጨነቃት የሰላሰ አራት ሰው መሞት አይደለም። የ34 ሰው ሞት የዘር ማጥፋት መባሉ ነው። እና ስለተኩስ ሲጠየቁ ሳትመለስ ክፍተት ስታገኝ ክሱን ለማጣጣል ብቻ ተነሳች። የዘር ማጥፋት ሙከራና የዘር ማጥፋት የማይለይ ችኩል ስርአት ስለ ዘር ማጥፋትና ሰው ማጥፋት ሲከራከር አይገርምም። እነ መለስ፡ የቅንጅትን አመራር በዘር ማጥፋት ወንጀል ሲከሱ፡ “ አረ ተዉ ይሄ ነገር አያዋጣም ባይሆን “ሙከራ” በሉት እንጂ ብሎ የመከራቸው አንድ የአሜሪካ ምሁር ነው። እና ዛሬ ስለዘርማጥፋት ወንጀል ሌክቸር ሊሰጡ ነው።)

 

አቃቤ ሕግ ቀጠለ “በሁሉም ከተሞችና ወረዳዎች ተኩስ እንደቀጠለ ነው። ሕዝቡ በባርነት ቀንበር ተይዞ ኖረ። የሀገሪቱ ምሁራን ሁሉ ተሰደዱ። ማንም ከናንተ ጋር መስራተ አልፈለገም።” እነሆ አመጽ ፈነዳ። ተሸነፋችሁ። ህዝብ አሸነፈ።

 

አንድ ያልታወቅ ጠያቂ ጣልቃ ገባ “የተከበሩ ፕሬዚዳንት አንድ ነገር ማወቅ እፈልጋለሁ። ተከሳሹ እነዚህ ሕዝብ ላይ የሚተኩሱ ቅጥረኞች እነማን እንደሆኑ? ማን እንደሚከፍላቸውና እንዴት ወዳገሪቱ እንደገቡ እንዲነግርን እፈልጋለሁ።”

 

አዎ ልክ ነው። መልስልን ተከሳሽ። መልስልን አለው አቃቤ ህግ። ቻውቼስኮ ግን ያንኑ የመጀመሪያውን መልስ ደገመ። “አልመልስም ከአብዩ ብሄራዊ ሸንጎ ፊት ብቻ ነው የምናገረው” አለ። ቾቼስኮ እንደ ጅብም አደረገው። እሰው አገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ አይነት ነገር። እነደ ቃሪያም አደረገው፤ በሁዳዴ ተግዝታ ሁልግዜ ሁዳዴ እንደሚመስላት። ኤሌናም ማንሾካሾኳን ቀጠለች። ሾካካ።

 

አቃቤ ሕግ በሀዜብ ሹክሹክታ ተበሳጨ መሰል ይሄንን አለ። ኤሌና ቁርጥ ሀዜብን ነው። ሀዜብ መስፍን ጎላ።

 

“ኤሌና ድሮም ምንም የማታውቅ ቀባጣሪ ነች። እኔ ራሴ፡ ምንም በቅጡ ማንበብ እንኳን የማትችል ነገር ግን ራሷን እንደ ዩኒቨርሲቲ ምሩቅ የምትቆጥር ሴት መሆኗን አስተውያለሁ። አቃቤ ሕግ ከዚያ ቀጥሎ ወ/ሮ ኤሌና አለኝ የምትለውን የዲግሪ መአት ደረደረው። (የሀዜብና የኤሌና መመሳሰል ግርም ይለኛል። ወ/ሮ ሀዜብ ታጋይ ነበረች። ሻይም ታፍላ ጠላ ትጥመቅ፤ ባንድ ወቅት ከታጋዮች ጋር የኖረች ታጋይ ነች። እስኪ አስቡት ይህቺ ታጋይ የኢትዮጵያ ጸረ-ኤድስ ምናምን ፕሬዚዳን፣ የኤፈርት ምክትል ስራ አስኪያጅ፣ የዚህ ድርጅት ሀላፊ፣ የተዋካዮች ም/ቤት አባል፤ እሷም እንደነ መለስ የተልእኮ ድግሪ ትያዝ አትያዝ አላውቅም። ግን ማይ ይከለክላታል። ገንዘብ ካለ…. እነሆ ሀዜብ ለመለስ በጆሮው ታንሾካሹካለች።)

 

ኤሌና መስፍን የዚህ አገር ምሁራን በኛ ላይ የምታቀርበውን ክስ እየሰሙ ነው። ይታዘቡሀል አይነት ነገር ተናገረች።

 

አቃቤ ሕግ፡ ቀጠለ፡ “አቶ ኒኮላ ዜናዊ ጥያቁያችንን ለምን እንደማይመለስ ሊነግረን ይገባል? ምንድነው ምክንያቱ?”

 

መለስ ቻውቼስኮ ለምን መልስ እንደማይመለስ እንዲህ ሲል መለሰ። “ማናቸውንም ጥያቄ እመልሳለሁ ግን ከሰራተኛው መደብ ተወካዮች ከታላቁ ብሄራዊ ሸንጎ ፊት ከሆነ ነው። ለሕዝቡ ሁሉንም ጥያቄውን እንደምመልስ ንገሩት። ዓለም እዚህ ምን እየተሰራ ምንስ እየተደረገ መሆኑን ማወቅ አለበት። የማውቀው የሰራተኛውን መደብና የብሄራዊ ሸንጎውን ብቻ ነው፤ ሌላ ማንንም አላውቅም።” (አራት ነጥብ አላለም እንደ መለስ። ያ በቻይና ቴክኖሎጂ እየታገዘ አገሪቱን አፍኖ የገዛና መተንፈሻ ያሳጣ፣ ያ መገናኛ ብዙሀንን ዘግቶ የራሱን ልሳን ብቻ የከፈተ አምባገነን፣ ያ ዓለም ረሀባችንና መታረዛችንን እናዳያውቅ ያደረገ ስርአት መሪ ዛሬ በወደቀ በሶስተኛው ሌሊት እዚህ ኢትዮጵያ የሚደረገውን ዓለም ይወቀው ይላል። አይገርምም። እኛም እሱን መለስንና ፓርቲውን ያወቅነው በግድ ነው። መርጠን አይደለም። ወደንም ፈቅደንም አይደለም። እነሆ ያ ጊዜ መጣ፤ እሱም እኛን በግድ የሚያውቅበት)። አቃቤህጉም አለው ለመለስ ቻውቼስኮ “ዓለም በዚህ በሮማኒያ የሆነውን አውቋል።” በኢትዮጵያም እንደዚያው። ስለዚህም መለስ አድምጥ፡ አለም እኛን አላዳነንም፡ ዓለም አንተንም አያድንህም።

 

መለስ ቻውቼስኮ በብስጭት እንዲህ አለ “እናንተ አመጸኞችና ሴረኞች፣ መንግስት ገልባጮች፤ ለናንተ መልስ አልሰጥም።”

 

አቃቤ ሕግ “ብሄራዊ ሸንጎው ፈርሷል”።

 

መለስ ቻውቼስኮ፡ “ይህ ሊሆን አይችልም፤ ማንም ብሄራዊ ሸንጎውን ሊያፈርሰው አይችልም።” (አይገርምም የአምባገነኖች ሁሉ ጸባይ አንድ ነው። መንግስታችን በአለት ላይ የታነጸ ነው። የሲኦልም ደጆች ሊያናውጿት አይችልም አይነት አነጋገር። ለሰማያዊ ፈጣሪ ብቻ የተሰጠውን ቋንቋ ለራሳቸው ይጠቀሙበታል። መለስ ሕገ መንግስታችንን ማንም ሊነጥቅ አይችልም እንደሚለው መሆኑ ነው። ከፊታቸው ነጥቀው የመጡትን ሕገ መንግስታት ይዘነጋሉ። ተመልከቱ፡ አምባገነኖች ልብና አእምሮ ይነሳቸዋል ካልተባለ በስተቀር መለስ የደርግን፤ ደርግም የጃንሆይን ህገ መንግስት አፍርሰው እዚህ እንደደረሱ ካልረሱ በስተቀር እንደምን ማንም ሊነቀንቀን አይቻለውም ብለው ይናገራሉ?) የሆነ ሆነና ቾቼስኮ እንደዚያ አለ። እንደ መለስ።

 

አቃቤ ሕግ፡ “ያ ሆነ፤ ብሄራዊ ሸንጓችሁ ፈረሰ። የተወካዮች ምክር ቤት የፌዴሬሽን ምክርቤት የሰራተኛ ምደብ የገበሬው ግንባር ኢህአዴግ ምናምን የምትሏቸው አካላት ሁሉ ተበተኑ። አሁን ሌላ መሪ አካል አለ። የብሄራዊ መድህን ግንባር ነው አገሪቱን የሚመራው”።

 

መለስ ቻውቼስኮ፡ “ማንም ያንን የሚቀበል የለም። ለዚህም ነው ሕዝቡ ባገሪቱ ሁሉ የሚፋለመው። ጋንጎች ናቸው ይህን መፈንቅለ መንግስት ያስተባበሩት። ይሄ ጋንግ ይደመሰሳል።” (አሁንም የአምባገነኖች ሁሉ ቋንቋና ጅልነት አንድ አይነት ነው። እየሞቱ ሁሉ እየወደቁ ቋንቋቸውን አይለውጡም። ምንም ነገር የህዝቡ ነው ብለው አያምኑም። የጣልቃ ገቦች፣ የአመጸኞች፣ የዱርዬዎች፣ የምናምኖች …..። መለስም ያለው ይሄንን ነበር። የቦዘኔዎች፣ የዱርዬዎች፣ የተቃዋሚዎች። ቢሆንስ? እነሱስ ባንድ ወቅት ሽፍቶች አልተባሉም? ወንበዴዎች አልተባሉም? ቤተ መንግስት መግባታቸውና ልብስ መቀየራቸው፤ ከቁምጣ ወደ ሱፍ፡ ማደግ ሁሉንም ነገር ይለውጣል ማለት ነው?

 

አቃቤ ሕግ፡ “ህዝቡ የሚዋጋው እናንተን ነው፤ ሕዝቡ የሚዋጋው አዲሱን መንግስት አይደለም።”

 

መለስ፡ “ኖ ሕዝቡ የሚዋጋው ለነጻነቱ ነው። የሚዋጋውም አዲሱን አመራር ነው። ይሄንን ፍርድ ቤት አላውቅም።

 

አቃቤ ሕግ፡ “ይቅርታ እስኪ ድገምልኝ፤ ዛሬ ሕዝቡ የሚዋጋው ለምን ይመስልሀል? እስኪ ምን ታስባለህ?” (ምን ያስባሉ አቶ መለስ? በሕገ መንግስቱ የተረጋገጡለትን መብቶች ለማስጠበቅ ነው እንደሚሉ ነው አቶ መለስና ቤተሰባቸው። መቼም ልጆቻቸውን አንጨምርም አዚህ። ግን በሕግ መንግስቱ የተረጋገጡትን መብቶች የሚጥሱት ህገ መንግስቱን የሰጡት ሲሆኑስ?)

 

ቻውቼስኮ ዜናዊም መለሰ “ቀደም ብዬ እንዳልኩት፤ ሕዝቡ የሚዋጋው ለነጻነቱና ይሄንን መፈንቅለ መንግስትና የስልጣን ንጥቂያ ተቃውሞ ነው።” ቻውቼስኮ የሚለው ይሄ መፈንቅለ መንግስት የተቀናበረው በውጭ ሀይሎች ነው አይነት ነገር ነው። (ይሄ ተለመደ ነው። የህዝብንና የተማሪዎችን አመጽ የተቃዋሚዎችና የዱርዬዎች አድርጎ መሳል የነመለስ የዘወትር ስልት ነው። ግን ያ አይሰራም። ማንም ይቀሰቅሰው ማን፡ ዋናው ነገር ማሸነፍ ነው። ካሸነፍን ፍርድ የኛ ነው። ከተሸነፍን፣ ከተነቃብንም፣ ይፈረድብናል። እንዲህ እንዲህ እያለ ክርክሩ ይቀጥላል …….. ይቀጥላል። የፍርድ ሂደቱም በቀጥታ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ይተላለፋል። ትንቢተ ሮማኒያ ይቀጥላል …..

 

ይህ ጽሁፍ፡ ከዚህ http://www.ceausescu.org/ceausescu_texts/revolution/trial-eng.htm የተወሰደና ለኢትዮጵያ ሁኔታ እንዲስማማ ትንሽ ማስተካከያ የተደረገበት ነው። ቀጣዩን ክፍል ሰሞኑን ይዠ እቀርባለሁ።

 

ታህሳስ 2009፤

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ